1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ኅብረትን ያሰጋዉ የአፍሪቃዉያን ስደት

ሐሙስ፣ ኅዳር 14 2010

አፍሪቃ ዉስጥ በቀጣይ 80 ዓመታት አሁን ካለዉ የሕዝብ ብዛት በአራት እጥፍ የሚበልጥ ሕዝብ እንደሚኖር ከወዲሁ የሚወጡ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በዚህ ወቅትም በተለይ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸዉ ተስፋ እንዲኖረዉ ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸዉ ይታመናል። የአዉሮጳ ኅብረት አፍሪቃ ዉስጥ ተገቢዉን ትምህርት በማስፋፋት የተሰዳጁን ቁጥር ለመቀነስ አልሟል።

https://p.dw.com/p/2o9AN
Uganda Bürgerkrieg und Hunger im Südsudan treiben Menschen zur Flucht
ምስል Getty Images/D. Kitwood

ትምህርትን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ተነግሯል፤

«በዩጋንዳዉ የእኛ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ትምህርቱ በድንኳን ዉስጥም ሆነ በዛፍ ጥላ ስር ይካሄዳል።በቂ ትምህርት ቤቶች የሉም።» ትላለች ከአራት ዓመት በፊት ከነቤተሰቧ ከደቡብ ሱዳን ወደ ጎረቤት ዩጋንዳ የተሰደደችዉ ናታሊያ ማቢሲሞ ፒስ። «ከዚያን ጊዜ ወዲህ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻልኩም።» አከለች የ20 ዓመቷ ወጣት ፒስ። እናም አሁን የጀመረችዉ ሙያዊ ስልጠና ሕይወቷን ወደፊት ያራምድልኛል የሚል ተስፋ ሰንቃለች። በአዉሮጳ ኅብረት መቀመጫ ብራስልስ ተገኝታም የእሷ እና የትዉልዷ ችግር ይሰማ ዘንድ በኅብረቱ እና በተመድ ወኪሎች ፊት ድምጿን አሰምታለች። ትምህርት እና ሙያዊ ስልጠና ለወጣቱ ጠቃሚ መሆኑን ነዉ አፅንኦት የሰጠችዉ። እንዲያም ሆኖ ግን ትምህርት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉም ልጆች ተመችቷቸዉ ለመማር የማይችሉበት ጊዜ ይበዛል። ምክንያቱ ደግሞ ወይ ዉኃ በመቅዳት አለያም በቤት ዉስጥ ሥራ በመሳተፍ ቤተሰቦቻቸዉን መርዳት ስለሚኖርባቸዉ ነዉ። በተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት ማለትም ዩኒሴፍ  ዉስጥ የልጆችን ሥራ ከሚመለከተዉ ዘርፍ፤ መሐመድ ማሊኪ ፋል ፒስ የምትለዉ እዉነት መሆኑን ያረጋግጣሉ። ይህ ደግሞ ዩጋንዳ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በራሳቸዉ ትዉልድ ሀገር ናይጀሪያም የሚታይ ችግር ነዉ። ልጆቹ ሴቶች ከሆኑ ደግሞ አልፎ ተርፎም ገና በለጋ ዕድሜያቸዉ ተገደዉ ይዳሩ እና ሶስት አራት ልጆችን ወልደዉ በትንሽነታቸዉ የቤተሰብ ኃላፊነትን ቀንበር እንደሚሸከሙም ይገልጻሉ። ይህም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትምህርቱ ዓለም እንዲርቁ ያደርጋቸዋል።

Flüchtlinge in Melilla
ምስል Reuters

በቀጣይ ዓመታት የሕዝብ ቁጥሯ እያደገ ለሚሄደዉ አፍሪቃ ትዉልዷን በትምህርትና ስልጠና ከማስታጠቅ የበለጠ መፍትሄ እንደማይገኝላት ነዉ የሚነገረዉ። የተመድ ከወዲሁ እንደገመተዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2100ዓ,ም የአፍሪቃ ሕዝብ ከአራት ቢሊየን ይበልጣል። ከሁለት አንዱ ደግሞ ከ15 ዓመት በታች የሆነ አዳጊ ወጣት ነዉ። በአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን የሰብዓዊ ርዳታ እና የቀዉስ መከላከል ኮሚሽነር ክሪስቶስ ስቲሊያንዲስ እንደሚሉት፤ ለአፍሪቃ ልጆቿ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ  ወሳኝ ነዉ። በእሳቸዉ እምነትም በትምህርት አማካኝነት ብቻ ነዉ አፍሪቃዉያን ልጆች በሀገራቸዉ መጻኢ ዕድላቸዉን ማመቻቸ እንደሚችሉ እና ለእነሱም ሆነ ለቤተሰባቸዉ ተስፋ እንዳላቸዉ ማሳየት የሚቻለዉ። ለዚህም ደግሞ ለትምህርት የሚሆነዉን የእርዳታ በጀት በስምንት እጥፍ ከፍ ማድረጋቸዉንም ይገልጻሉ። ያም ቢሆን ግን በቂ ነዉ እያሉ አይደለም። ወጣቶች አፍሪቃ ዉስጥ ዕድልና ተስፋ ማየት ሲሳናቸዉ ምን እንደሚከተል ሲሌ ካያንጌ ያዉቃሉ።  የጣሊያን የዉሕደት ሚኒስትር እና ለዓመታት ወደጣሊያን ሲገቡ ለነበሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተሰዳጆች ተጠሪ በመሆን ያገለገሉት ካያንጌ አሁን የአዉሮጳ ኅብረት የምክር ቤት አባላት እና የአፍሪቃ የጋራ ትብብር ተጠሪ ናቸዉ። የትምህርት እና የስልጠና ዕድል ማመቻቸት የሚለዉ ብቻ ብዙም እንደማያራምድ ይናገራሉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም «ወጣቶቹ ከአፍሪቃ የሚሰደዱት በፖለቲካ፣ በመብት እና በኤኮኖሚ ችግሮች ምክንያት በወደፊት ሕይወታቸዉ ተስፋ ሲያጡ ነዉ።»

Flüchtlinge in Melilla 24.02.2014
ምስል picture-alliance/dpa

በዚህም ምክንያት የስደታቸዉ መንስኤ ከተለያየ አቅጣጫ መፍትሄ እንዲያገኝ ትግል ያስፈልገዋል። ወጣቶች በያሉበት ቦታ የሥራ ዕድል ማግኘት አለባቸዉ፤ ለዚህም መሠራት አለበት። አፍሪቃ ዉስጥ በንቃት የሚሳተፉ የአዉሮጳዉያን ስጋትም ይኸዉ እንደሆነ ካያንጋ ያስረዳሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በቀጣይ በአፍሪቃ እና በአዉሮጳ መሪዎች መካከል የሚካሄደዉ ጉባኤ የተሻለ ዉጤት አምጥቶ፤ በሕገወጥ የስደት መንገድ ሕይወታቸዉን ለአደጋ የሚያጋልጡ ወጣቶች ቁጥር ይቀንሳል የሚል ተስፋ አላቸዉ። ለመፍትሄዉም አፍሪቃራሷም ኃላፊነቱን መዉሰድ እንዳለባት ያስገነዝባሉ።

«አፍሪቃ በሆነ ደረጃ የራሷን ጉዳይ ራሷ ማስተካከል አለባት። ከቅኝ ግዛት ነፃ ከሆነች በኋላ ራሷን ችላ አፍሪቃ መንቀሳቀስ ያለባት ወቅት አለ፤ ያም ወቅት አሁን መጥቷል። የአፍሪቃ ሕዝብ ኃላፊነት የሚወስድበት ጊዜ ነዉ፤ ለምሳሌ አምባገነኖችን በማስወገዱ በኩል።»

በዚህ ሃሳባቸዉ የዩኒሴፉ መሐመድ ማሊኪ ፋልም ይስማማሉ።  በዚህ ሂደት ግን በፍጥነት መፍትሄ ለማግኘት በሚል ስህተት እንዳይፈጸምም ያሳስባሉ።

ሸዋዬ ለገሠ- ዶሪስ ፑንዲ

አርያም ተክሌ