1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ሕብረት ዉሳኔና ሩሲያ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2000

የአዉሮጳ ሕብረት የሚያደርገዉ ያልተዘጋ በር ከማንኳኳት የሚቆጠር ነዉ

https://p.dw.com/p/FA2z
ኒኮላ ሳርኮዚምስል AP

02 09 08


የአዉሮጳ ሕብረት ዉሳኔና ሩሲያ

በካዉካሰስ ግጭት ላይ ለመምከር ትናንት የተሰየመዉ የአዉሮጳ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ግጭቱ በሠላም እንዲፈታ ጠየቀ። ሩሲያ ከጆርጂያ ለተገነጠሉት ለደቡብ ኦሲቲያና ለአብኻዚያ ግዛቶች የነፃ መንግሥትነት እዉቅና መስጠቷን ጉባኤዉ ተቃዉሞታል።የሩሲያ ጦር ከጆርጂያ ግዛት አልወጣም የሚሉት ጉባኤተኞች ጦሩ ሙሉ በሙሉ እስኪወጣ ድረስ ሕብረቱ ከሩሲያ ጋር የትብብር ዉይይት አቋርጦታል።የሕብረቱ ከፍተኛ የልዕኳን ቡድን ወደ ሞስኮ እንዲሔድም ጉባኤዉ ወስኗል።ዉሳኔዉ ሩሲያንም፥ ጆርጂያንም አላስደሰተም።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ

የጉባኤዉ ጥቅል-ዉሳኔ አገም-ጠቀም አይነት ነዉ።በርግጥም ሩሲያን ብዙ አስቀይሞ ሕብረቱ ብዙ ከሚጠቀምባት ግዙፍ ሐገር ጋር መማረሩን አይሻዉም።የዚያኑ ያክል ጆርጂያን ጭራሽ ሊተዋት አልፈለገም።ለዳግም ግንባታ ገንዘብ ሊያዋጡላት ተስማምተዋል።የትናንቱ ጉባኤተኞች ሩሲያ ከጆርጂያ ለተገነጠሉት ለደቡባዊ ኦሲቲያና ለአብካዚያ የነፃ መንግሥትነት መስጠዋትን በተናጥል እንዳወገዙት ሁሉ ትናንትም በድጋሚ ግን በጋራ አዉግዘዉታል።

ጉባኤተኞች የሩሲያ ጦር የጆርጂያን ግዛት አሁንም እንደያዘ ነዉ-ባዮች ናቸዉ።ሩሲያ ጆርጂያን ሙሉ በሙሉ ለቅቃ እስከትወጣ ድረስ ሕብረቱ ከሩሲያ ጋር ያደርግ የነበረዉን የሥልታዊ ትብብር ዉይይት ያቋርጣል።የሕብረቱን ተዘዋዋሪ የፕሬዝዳትነት ሥልጣን የያዙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒኮላ ሳርኮዚ ከሞስኮ ለመወዳጀት ወዳጅ አጣን ይላሉ።

«የአዉሮጳ ሕብረት የከሩሲያ እዉነኛ ወዳጅነት ለመሆን ይመኛል።ይሁንና ወዳጅነት ለመመሥረት ሁለት ወገን ያስፈልጋል።የአዉሮጳ ሕብረት ከሩሲያ ጋር ያለዉን ግንኙነትን ያጎለዉ ይሕ ቀዉስ የሚወገድበትን ሁኔታ ያጠናል።

ቀዉሱ የሚወገድበትን ሁኔታ ለማጥናት ይሁን የትናንቱን ጉባኤ ለሩሲያ መሪዎች በቀጥታ በቃል ለማስረዳት፣ ሳርኮዚ የሚመሩት የሕብረቱ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በመጪዉ ሳምንት ሰኞ ወደ ሞስኮ ይሔዳል።ከሳርኮዚና ከሕብረቱ ኮሚሽነር ፕሬዝዳት ከሆዜ ማኑኤል ባሮሶ ጋር ወደ ሞስኮ የሚሔዱት የሕብረቱ የዉጪ ግንኙነት የበላይ ሐቪየር ሶላና እንደሚሉት ጉባኤዉ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ለጆርጂያ በጣም ጠቃሚ ነዉ።


የጆርጅያ ቢያንስ የርዕሠ-ከተማይቱ ሕዝብ ግን ሕብረቱ ካሰበለት በላይ ማድረግ ነበረበት ባይ ነዉ።የሕብረቱ መሪዎች ብራስልስ ጉባኤ በተቀመጡበት ወቅት የቲቢሊ ነዋሪዎች ደግሞ ርዕሠ-ከማይቱ ዉስጥ ለአደባባይ ሠልፍት ታድመዉ ነበር።ፕሬዝዳት ሚኻኤል ሻአካሽቪሊ በተካፈሉበት ሠልፍ የተገኘዉ አብዛኛዉ ሰዉ ከሰልፈኞቹ አንዷ ሐኪም ኤለን ፒልፓኒ እንዳለችዉ የአዉሮጳ ሕብረት በሩሲያ ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል የሚል ተስፋ ነበረዉ።

«ተጨባጭና ጠንካራ ይሆናል የሚል ተስፋ ነበረኝ።ለምሳሌ ማዕቀብ።የአዉሮጳ ሕብረት ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል ይሕ ቢቀር አዉሮጳ በግልፅ ቃላት ትናገራለች የሚል ተስፋ ነበረኝ።አሁን ግን እንደሚመስለኝ በማንም በምንም ተስፋ ማድረግ የለብንም።»

ከምሥራቅ አዉሮጳ ሕብረቱን በቅርቡ የተቀላቀሉት አዳዲስ አባላት የትናንቱ ጉባኤ ሩሲያን ይበልጥ የሚጫን ዉሳኔ ማሳለፍ አለበት የሚል አቋም ነበራቸዉ።ነባሮቹ የሕብረቱ አባላት ግን በሩሲያ ላይ ከተወሰነዉ በላይ እርምጃ መዉሰድ አፀፋዉ አደገኛ ይሆን ባዮች ናቸዉ።ያም ሆኖ ጉባኤዉ ትናንት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ሞስኮን ለማስቆጣት በቂ ነዉ።በአዉሮጳ ሕብረት የሩሲያዉ አምባሳደር ሺሽሆቭ እንዳሉት ጉባኤዉ በተለይ የሩሲያ ጦር ከጆርጂያ ይዉጣ ማለቱ ክፍት በር እንደ ማንኳኳት ነዉ።



«በዚሕ ዉሳኔ እና ወታደሮች (ከጆርጂያ) በመዉጣታቸዉ መካካለዉ ያለዉ ርቀት የአዉሮጳ ሕብረት የሚያደርገዉ ያልተዘጋ በር ከማንኳኳት የሚቆጠር ነዉ።የሩሲያ ወታደሮች በሙሉ ከጆርጂያ ግዛት ለቀዉ ወጥተዋል።ሜድቬዴቭና በሳርኮዚ በተስማሙበት እቅድ መሠረት ለፀጥታ በተከለለዉ አካባቢ ብቻ አነስተኛ የሠላም አስከባሪ ሐይል አለ።»

ጆርጂያና ሩሲያ በፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ ሽምጋይነት ባደረጉት ስምምነት መሠረት ሩሲያ የተወሰነ ጦርዋን ደቡብ ኦሲቲያ አጠገብ የማስፈር መብት አላት።