1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአኩሪ አተር ፈርጀ ብዙ ጥቅም

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2008

አኩሪ አተርን በተለያየ መንገድ ለምግብነት በርካቶች ይጠቀሙበታል። ከምሥራቅ እስያ አካባቢ መገኘቱ የሚገርለት ይህ የእህል ዘር በፕሮቲን የበለፀገ በመሆኑ ለተለያዩ የተመጣጠኑ ምግቦች ዝግጅት ሲዉል ዓመታት ተቆጥረዋል።

https://p.dw.com/p/1HRro
Äthiopien Sojabohne Zubereitung
ምስል Ethiopian Institute of Agricultural Research

የአኩሪ አተር ፈርጀ ብዙ ጥቅም

ከ20ኛዉ ክፍለ ዘመን አንስቶ በተለይ አሜሪካን ዉስጥ ወርቃማዉ ወይም ተዓምረኛዉ እህል የሚል ስያሜ አግኝቷል። አኩሪ አተር በፕሮቲን እና ቅባት ምንጭነቱ የሚወዳደረዉ የእህል ዘር የለም። ባለሙያ ካገኘም ለመጠጣትም ለመበላትም የሚችል የእህል ዘር ነዉ። ስለአኩሪ አተር ሲወሳ ብዙዎች የሚያስታዉሱት ለሕፃናት አካል ግንባታ ጠቃሚ መሆኑ ብዙ ጊዜ የተነገረለትን የአኩሪ አተር ወተት ሊሆን ይችላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በኢትዮጵያዉያን የምግብ ጣዕም ለዛ ተላብሶ በተለያየ ምግብነት መቅረብ እንደሚችል እየታየ ነዉ።

አኩሪ አተር ወደኢትዮጵያ የገባዉ በ1950ዎቹ መሆኑን ነዉ በእህሉ ላይ ምርምር የሚያደርጉት ባለሙያዎች የሚያስረዱት። በአኩሪ አተር ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደረገዉ ዝርያ የማዉጣት ምርምርም 22 ዓይነት ዘሮች እስካሁን ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ የአኩሪ አተር ብሔራዊ ምርምር ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ትዕዛዙ ደጉ ስድስት ዘርፎች ያሉት የምርምር ፕሮጀክት እህሎቹን እርስ በርስ በማዳቀል የሚፈለገዉን የጥራት ደረጃ እንዲይዝ ማድረግ፤ ምርትና በሽታ መቋቋም ላይ ያተኮረ ምርምርም ያካሂዳል። አኩሪ አተርን በሀገር ዉስጥ በ12 የምርምር ማዕከላት ላይ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በሚያገኙ፤ መካከለኛ የዝናብ መጠን በሚያገኙ እና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ምርምሩ ይካሄዳል። ምርምሩ በዚህ አያበቃም ሰብል ክብካቤን በሚመለከት መቼ መዘራት አለበት የሚለዉ እና የአመራረት ሥርዓት ማለትም አኩሪ አተር ከየትኛዉ እህል ጋር ተፈራርቆ ይዘራ፤ ከየትኛዉስ ጋር ተሰባጥሮ ይዘራ የሚለዉ ጥናትም የፕሮጀክቱ አንድ አካል ነዉ። አኩሪ አተርን ሰብልን ሊያጠቁ የሚችሉ አረም ሆነ ተባይ ወይም በሽታ የቱ እንደሆነም ክትትል ይደረጋል። ስለአኩሪ አተር ጥቅም የሚዘረዝሩ ዘገባዎች የመኖራቸዉን ያህል በተፈላጊነቱ ምክንያት በተለይ ደቡብ አሜሪካ ዉስጥ ደኖች እንዲጨፈጨፉ ምክንያት ሆኖ በሥነምህዳሩ ላይ ጫና እስካተለ የሚያወሱም አሉ።

Äthiopien Sojabohne Zubereitung
ከአኩሪ አተር የተዘጋጁ ምግቦችምስል Ethiopian Institute of Agricultural Research

አኩሪ አተር ሀገር ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተዉ በቤንሻንጉል ጉምዝ እና በኦሮሚያ ክልል ነዉ። አኩሪ አተርን በብዛት ከሚያመርቱ ሃገራት ዩናትድ ስቴትስ፤ ብራዚል እና አርጀንቲና ቀዳሚዎቹ ናቸዉ። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም በአኩሪ አተር ላይ አመራረትም ሆነ ምግብ ዝግጅት ላይ ምርምር ሲያካሂድ የቆየ መሆኑን የገለፁት በግብርና ምርምር ተቋሙ የምግብ ሳይንስ ተመራማሪ እና የብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ቢላቱ አግዛ አኩሪ አተር በኢትዮጵያ በምግብነት ያን ያህል አልተለመደም ይላሉ።

Äthiopien Sojabohne Zubereitung
ከአኩሪ አተር የተቀላቀለበት ኬክምስል Ethiopian Institute of Agricultural Research

ከአኩሪ አተር ወተት ለማዘጋጀት ሲታሰብ እህሉን ከአንድ ቀን በፊት ለቅሞና አጥቦ ለ15 ደቂቃ ያህል መቀቀል ያስፈልጋል። ከዚያም አዉጥቶ ተዘፍዝፎ ያድራል። ከዚያም የራሰዉን አኩሪ አተር ልጣጩን በሚገባ በዉኃ አስለቅቆ በትንሽ በትንሹ እየቆነጠሩ ፈጭቶ እንደእህሉ መጠን ዉኃ ጨምሮ መቀቀልና መጭመቅ ነዉ። እንደባለሙያዉ ከሆነም ለአንድ ኪሎ አኩሪ አተር ስምንት ሊትር ዉኃ ያስፈልጋል።

ተፈጥሮን ተከትሎ የማይበቅል እህልም ሆነ በተፈጥሮ ሥርዓት ያላደጉ እንስሳትን መመገብ ለጤና አደገኛ መሆኑን በተግባር የተረዳዉ ምዕራቡ ዓለም በአሁኑ ጊዜ ፊቱን ከእንስሳት ተዋፅኦ ወደተክሎችና ሰብሎች አዙሯል። በዚህ ምክንያትም ከአኩሪ አተር የሚገኙ የምግብ ተዋፅኦዎች ተመራጭነትን እያገኙ ነዉ። ከአኩሪ አተር ወተት እና አይቡ እንደሚገኝ ሁሉ የአኩሪ አተር ሥጋም አለዉ።

Äthiopien Sojabohne Zubereitung
የአኩሪ አተር አይብምስል Ethiopian Institute of Agricultural Research

በአኩሪ አተር ዘር እና አመራረት ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርምር ሲደረግ ረዥም ዓመታት አስቆጥሯል። የምግብ ዝግጅቱን ተመለከተ የሚካሄደዉ ምርምር ብቻም አስር ዓመታት እንደቆየ አቶ ቢላቱ ገልጸዋል። የግብርና ምርምር ተቋሙ የአኩሪ አተርን ምግብነት ለማላመድ በጀመረዉ እንቅስቃሴ ለአምራቹቹ ብቻ የምግብ ዝግጅት ሥልጠና ከመስጠት የተቋሙ ሠራተኞችም አዉቀዉት ሙያዉን በማስፋፋት በኩል አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በሚል አሰልጥኗል።

አቶ ቢላቱ እንደገለፁልን ኢትዮጵያ አኩሪ አተርን ብታመርትም ለዉጭ ገበያ ነዉ። በአንፃሩ የተዘጋጁትን የአኩሪ አተር ምርቶች ወደሀገር ታስገባለች። ከዚህም ሌላ በተለያዩ አካላት የአኩሪ አተር ምግብ አዘገጃጀትን የማስተዋወቁ ሥራ እንደሚከናወን ያመለከቱት የምግብ ምርምር ባለሙያ ይህ ወጥነት እንዲኖረዉ እየተሠራ መሆኑንም ሳይገልፁ አላለፉም። አኩሪ አተር ላይ የሚደረገዉ ምርምርም ሆነ የምግብ አዘገጃጀቱ ጥናት ዋና ዓላማ እህሉ ሀገር ዉስጥ ጥቅሙ ታዉቆ ኅብረተሰቡ ከሚገዙ ምርቶቹ ይልቅ በየቤቱ በቀላሉ ማዘጋጀቱን ለምዶ እንዲጠቀምበት ማድረግ እንደሆነ ነዉ ባለሙያዎቹ ያስረዱት። በተጨማሪም ከዉጭ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለም አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ