1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአኤሮፕላን ኃይለኛ ድምፅና ጤንነት

ረቡዕ፣ የካቲት 24 2002

ባለፈው ሳምንት ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ በቤንዚን ኃይል ከሚበሩ የህዝብ ማመላላሽ አኤሮፕላኖች፣ ይልቅ ፣ በኤሌክትሪክ ሞተር የሚንቀሳቀሱት

https://p.dw.com/p/MIuN
ምስል AP

ይበልጥ አስተማማኝነት እንዳላቸው ጠቃቅሰን እንደነበረ የሚታወስ ነው። እንዳወሳነው፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ ሞተር 95 ከመቶ ያህል እጅግ አስተማማኝ መሆኑ ሲነገርለት፣ ፣ በነዳጅ ኃይል የሚሠራው፣ አስተማማኝነቱ ፣ ከ 18 እስከ 23 ከመቶ ብቻ ነው።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ አኤሮፕላኖች፣ ወደፊት አስፈላጊነታቸውም ሆነ ጠቀሜታቸው፣ በአመዛኙ ፣ በበረራ እንከን አያጋጥማቸውም ተብሎ ፣ ጉዳዩ ከደኅንነት አኳያ ብቻ ታይቶ ሳይሆን፣በቤንዚን የሚጠቀሙት አኤሮፕላኖች፣ ተንኮብኩበው በሚነሱበትም ሆነ፣ ለማረፍ ዝቅ ብለው በሚበሩበት መሥመር የሚገኙ ከተሞችም ሆኑ መንደሮች ኑዋሪዎች ጤንነትም ስለሚታወክ መሆኑ የሚያጠራጥር አልሆነም። የጀርመን ፌደራል መንግሥት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉዳይ መ/ቤት ፣ በተለይ በኮሎኝና በቦን አኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ አካባቢ በሚገኙ ንዑሳን ከተሞችና መንደሮች ዙሪያ ፣ ከ 1,20 በላይ የሚሆኑ ኑዋሪዎችን ጠይቆ ባጠናቀረው የጥናት ውጤት እንዳስረዳው ከሆነ፣ ጆሮን የሚሠነጥቀው፣ እጅግ ኃይለኛው የአኤሮፕላን ድምፅ ማለታችን ነው፣ ለጤና ጠንቅ ነው። በተለይ ሰዎችን ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሰው በሌሊት የሚከናወነው በረራ!

የጀርመን የአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች የሥራ ማኅበር ግን፣ የጥናቱ ውጤት የተሟላ ሳያንሳዊ ምርመራ መካሄዱን አይጠቁምም በማለት ለማጣጣል ሞክሮአል። ጥናቱን ያካሄደው መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው፣ በአኤሮፕላን ድምፅ እንደሚታወኩ የገለጡት 5 ሚሊዮን ዜጎች ናቸው። ከተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት፣ ጥናቱን የመሩት ዶ/ር ኤበርሃርድ ግራይሰር እንደገለጡት፣ ኃይለኛ የአኤሮፕላን ድምፅ የልብና የዑደተ- ደም ችግር ላለባቸው ሰዎች ይበልጥ ጠንቀኛ መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ከዚህም ሌላ፣ ጥናቱ በተጨማሪ፣ በሴቶች ላይ መንፈስ የሚያውክና አንገት የሚያስደፋ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ጠቁሞአል። በአብዛኞቹ ያውሮፓ የአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶችም፣ ኃይለኛው የአኤሮፕላን ድምፅ፣ በሰው ልጅ ጤንነት ላይ የተለያዩ ጠንቆችን እንደሚያስከትል ነው የሚጠቁሙት። ራልፍ ባይዘል የተባሉት የጀርመን አኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ መሥሪያ ቤቶች ዋና የሥራ መሪ ግን በገለልተኛ ድርጅት ጥናቱ ካልተካሄደ እምብዛም አስተማማኝ አይደለም ባይ ናቸው። ኃይለኛ የአኤሮፕላን ድምፅ በጤንነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሳንክ የተገነዘቡ፣ የጀርመን የአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ኩባንያዎች፣ አኤሮፕላኖች በሚያርፉባቸውና ተንኮብኩበው በሚነሱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ችግር ለማቃለል፣ ባለፉት 10 ዓመታት 470 ሚሊዮን ዩውሮ መርኀ-ግብር አውጥቶ ሥራ ላያ ያዋለ ሲሆን፣ ወደፊትም ከ 400-600 ሚሊዮን ዩውሮ ለማውጣት አቅድ ያላቸው መሆኑ ተነግሮአል።

ስለቺሌው የምድር ነውጥ በአጭሩ---

በጨረቃ ሰሜን ዋልታም የተጋገረ በረዶ መኖሩ ተረጋገጠ፣

የዩናይትድ እስቴትስ የኅዋ ምርምር መሥሪያ ቤት ከሰሞኑ እንዳስታወቀው፣ በህንድ መንኮራኩር «ቻንድራያን-1 » የላከው ንዑስ የምርምር ራዳር፣ ከ 1,6 እስከ 15 ኪሎሜትር ስፋት ያላቸው ከ 40 በላይ የሚሆኑ ሰርጓዳ ቦታዎች፣ ውሃ በቋጠረ የተጋገረ በረዶ የተሞሉ መሆናቸውን አረጋግጧል። በእያንዳንዱ ሰርጓዳ ቦታ የሚገኘው የበረዶ ክምችት መጠን የሚለያይ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ቢያንስ 600 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ውሃ የቋጠረ በረዶ እንደማይታጣ ይገመታል።

የህንድ ሳይንቲስቶች፣ አምና፣ በጨረቃ ምድር ውሻ መኖሩን ለማረጋገጥ ቻለናል ሲሉ በሳይንስ መጽሔት ማብራሪያ አቅርበው እንደነበረ አይዘነጋም። እስከዚያ ጊዜ ድረስ፣ ሳይንቲስቶች፣ ጨረቃ፣ ምናልባት ከስርጓዳ ተራሮቿ ሥር የረጋ በረዶ ይኖራት ካልሆነ በስተቀር፣ ሙሉ-በሙሉ ደረቅ ናት የሚለውን ነባቤ ቃል ነበረ ያስፋፉት። የረጋ በረዶ በሰሜንና ደቡብ የጨረቃ ዋልታዎች መገኘት፣ የገንዘብ እጥረት ካልገታ በስተቀር፣ ከ 41 ዓመት ገደማ በፊት ዩናይትድ እስቴትስ ሰውን ጨረቃ ላይ ማሳረፍ ከቻለችበት እርምጃ ባሻገር ፣የዘመኑ የኅዋ ተመራማሪዎች ለላቀ ዓላማ መነሳሳታቸው አይቀሬ መሆኑ የሚያነጋግር አይደለም።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ