1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንጎላ ፕሬዚደንት እና ዘመድ አዝማድ የመጥቀሙ አሰራራቸው

ቅዳሜ፣ ሰኔ 4 2008

የአንጎላ ፕሬዚደንት ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ የሴት ልጃቸውን በመንግሥት እጅ የሚገኘው የትልቁ የሀገሪቱ የነዳጅ ዘይት ተቋም ኃላፊ አድርገው ሾሙ። በአንጎላ የሚገኙ ሌሎች ብዙዎቹ ተቋማትም በፕሬዚደንቱ ዘመዶች ነው የተያዙት።

https://p.dw.com/p/1J4sq
Angola Sitz der Erdölfirma Sonangol
ምስል DW/N. Sul d'Angola

[No title]

የአንጎላ ፕሬዚደንት ሴት ልጅ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ ገና በልጅነታቸው በአንጎላ መዲና ሉዋንዳ በ "ኮንጎሌንሴስ" መንገዶች እንቁላል ይሸጡ እንደነበር ለአንድ የብሪታንያ ጋዜጣ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረው ነበር። የአንጎላ የርስ በርስ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት በዚሁ ጊዜም ቢሆን ለንግድ ልዩ ዝንባሌ ነበራቸው። የ43 ዓመቷ ወይዘሮ ዛሬ በአፍሪቃ ሀብታሟ ሴት ሆነዋል። «ፎርብስ» በተባለው የአሜሪካውያኑ የኤኮኖሚ መጽሔት ግምት መሰረት፣ የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽን ሀብት 3,3 ቢልዮን ዶላር ይደርሳል። የአንጎላ ፕሬዚደንት ልጅ ከሚቆጣጠሩዋቸው ወይም ከሚሳተፉባቸው ተቋማት መካከል « በምህፃሩ «ቢ አይ ሲ» የተባለው የአንጎላ ባንክ፣ «ሶዲያም» የአልማዝ ማዕድን ተቋም፣ እንዲሁም፣ በሀገሪቱ የተለያዩ የግንባታ ተቋማት እና «ዩኒቴል» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው በአንጎላ ትልቁ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተቋማት ይገኙባቸዋል።
ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ በተሰማሩበት የስራ ዓለም ውስጥ ባለፈው ሳምንትም ትልቅ የሚባለው ደረጃ ላይ ደርሰዋል፣ ይኸውም «ሶንአንጎል» የተባለውን የአንጎላ መንግሥት የነዳጅ ዘይት ተቋም ኃላፊነትን ስልጣን ይዘዋል። አንጎላ፣ ከናይጀሪያ ጎን በአፍሪቃ ትልቋ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገር ስትሆን፣ ከመንግሥቱ ጠቅላላ ገቢ መካከል ብዙውን የሚሸፍነው ከዚሁ የኤኮኖሚ ዘርፍ፣ ማለትም፣ ሀገሪቱ ይህንኑ ከዚሁ የተፈጥሮ ሀብት በንግድ ወደ ውጭ በመላክ የምታገኘው ገቢ ነው። ይህንኑ ከፍተኛ ስልጣን ለኢዛቤል የሰጡት ሀገሪቱን የሚመሩት አባታቸው ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ ናቸው። እጎአ ከ1979 ዓም ወዲህ አንጎላን በመምራት ላይ ያሉት ፕሬዚደንት ዶሽ ሳንቶሽ አፍሪቃ ውስጥ ከኢኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ቀጥለው ለረጅም ዓመታት በስልጣን ላይ የሚገኙት አፍሪቃዊ መሪ ናቸው።
ብዙ የአንጎላ ዜጎች ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ አንጎላን እንደ አንድ የቤተሰብ፣ ብሎም የግል ተቋም ነው እንደሚመሩ ነው የሚሰማቸው። ለምሳሌ፣ እጎአ በ2013 ዓም ፕሬዚደንቱ ወንድ ልጃቸውን ኾዜ ፊሎሜኖ፣ በቅጽል ስማቸው «ዜኑ»ን የአንጎላ መንግሥት «ሶቨሪን ዌልዝ ፈንድ» የተባለው፣ ከአምስት ቢልዮን የሚበልጥ ዶላር የሚያስተዳድረው መስሪያ ቤት የተቋቋመው ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ የሀገሪቱን ልማት ለማሳደግ እና ሕዝቡንም ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመው መስሪያ ቤት ኃላፊ አድርገው ሾመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአንጎላ ቁልፍ የሚባሉ ግምሩክን፣ የውኃ እና የኃይል ማመንጫ ተቋማትን የመሳሰሉ መስሪያ ቤቶች በጠቅላላ የሚመሩት በፕሬዚደንቱ ዘመዶች ነው። የታወቁት አንጎላዊ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ካርሎስ ሮዛዶስ ፕሬዚደንቱ ልጃቸውን ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽን የ«ሶንአንጎል» ኃላፊ አድርገው የሾሙበትን የሰሞኑን ውሳኔ የተሳሳተ ሆኖ አግኝተውታል።
« የ«ሶንአንጎል»ን ተቋም የሚመራውን ግለሰብ የመምረጡ ውሳኔ የኔ ቢሆን ኖሮ፣ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ የመጨረሻዋ ምርጫዬ በሆኑ ነበር። የአንጎላ ፕሬዚደንት ብሆን እና ሴት ልጅ ብትኖረኝ ኖሮ፣ ይህን ዓይነት ውሳኔ በፍፁም አልወስድም ነበር። ይህ ውሳኔአቸው በአንጎላ ብዙ ሰዎችን እጅግ አስቆጥቶዋል። »
እንደ ሮዛዶስ አስተያየት፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባሁኑ ጊዜ በዓለም ገበያ በወደቀበት እና በሰበቡ በተከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ ፣ «ሶንአንጎል » ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ተቋሙን ትርፋማ በማድረጉ ስራ ላይ የሚያደርግ ኃላፊ ነው የሚያስፈልገው። የነዳጅ ዘይቱ ተቋም ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ የተቋሙ ገቢ እጎአ ከ2014 ዓም ጋር ሲነፃፀር በ2015 ዓም በ34% ቀንሶዋል። ተቋሙ ከ50 ቢልዮን ዶላር ካፒታል እንዳለው ቢያመለክትም ፣ ተቋሙ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ የገለጹ የምጣኔ ሀብት ይህ የተጋነነ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
«ሶንአንጎል» የትልቁ የፖርቱጋል ባንክ «ቢ ሲ ፒ» አክስየን መካካል 18% ያለው ሲሆን፣ ትልቁ ባለአክስዮን ነው። ከዚህ ሌላም፣ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ በሌሎች ተቋማት አማካኝነት የፖርቱጋል ኢንቬስትመንት ባንክ ሁለተኛዋ ባለአክስየን ናቸው። ይኸው ሹመታቸው ባስከተለው የጥቅም ውዝግብ የተነሳ በሊዝበን አክስየን ገበያ ላይ የባንክ አክስየን ዋጋ ባለፉት ቀናት በጉልህ ዝቅ እንዲል አድርጎ እንደነበር ተገልጾዋል።
የአንጎላ ፕሬዚደንት ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ የሚከተሉትን ዘመድ አዝማድን የመጥቀም አሰራርን አስመልክተው አንጎላዊው የመብት ተሟጋች ጠበቃ ዴቪድ ሜንዴስ በሰጡት አስተያየት፣ ሀገራቸው ወደ አንድ ሰው ፍፁም አገዛዝ እያመራች መሆኗን ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ ዴቪድ ሜንዴስ ከሌሎች አንጎላውያን ጠበቆች ጋር ባንድነት በመሆን በሰሞኑ የፕሬዚደንቱ ውሳኔ፣ ማለትም፣ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽን በሾሙበት ርምጃ አንፃር ክስ ለመመስረት እያሰላሰሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እጎአ በ2010 ዓም በወጣ አንድ የአንጎላ ሕግ መሰረት፣ የመንግሥት መስሪያ ቤት ስልጣንን ለአንድ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ወቅት የጥቅም ውዝግብ ሊገጥመው ለሚችል ግለሰብ መስጠት የተከለከለ ነው። የአንጎል ፕሬዚደንቱ ልጅ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽም የመንግሥቱን ተቋም «ሶንአንጎል»ን ጥቅም የሚፃረሩ ብዙ የግል ጥቅሞች እንዳሉዋቸው ነው የሚነገረው። ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ በ«ሶንአንጎል» ተቋም ኃላፊነታቸው በመጠቀም የራሳቸውን ተቋማት የሚረዱ ርምጃዎች ሊወስዱ ይችላሉ በሚል መስጋታቸውን ነው ዴቭድ ሜንዴስ የገለጹት።
የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ የ«ሳንአንጎል» ኃላፊ ሆነው መሾም ዜና አንጎላ ውስጥ ሳይሆን ፣ የፕሬዚደንቱ ልጅ የግል ባንኮች፣ የቴሌኮምዩኒኬሽን እና የነዳጅ ዘይት ተቋማት ትልቅ ባለአክስየን በሆኑባት በቀድሞ የአንጎላ ቅኝ ገዢ ፖርቱጋልም ብዙ ያነጋገር አሳሳቢ ርዕስ መሆኑን የፖርቱጋላውያኑ የኤኮኖሚ ጋዜጣ፣ «ጆርናል ደ ኔጎሲዮስ» ጋዜጠኛ እና የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽን የህያወት ታሪክ የሚጽፈው ሴልሶ ፊሊፔ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
« የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ መሾም ያለመተማመን መንፈስ ፈጥሮዋል። ኢዛቤል የፕሬዚደንቱ ልጅ እንደመሆናቸው መጠን፣ ሹመቱ ወትሮም በፖርቱጋል የሚታየውን ያለመተማመን ሁኔታ እንዲባባስ ምክንያት ሆኖዋል። »
ፖርቱጋላዊው የኤኮኖሚ ጠበቃ ርዊ ቬርዴም ሹመቱ በፖርቱጋል ኤኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይገምታሉ።
« የፖርቱጋል ፍርድ ቤት ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ በ«ሶንአንጎል» ስም የሚያካሂዱትን ማንኛውም ንግድ፣ ባለአክስየን የሆኑበትን ባንክ ጥቅም ሊነካ ይችላል በሚል ምክንኢት፣ ተቀባይነት አይኖረውም በሚል ውድቅ ሊያደርገው ይችል ይሆናል። »
የፖለቲካ ተንታኞች እንዳመለከቱት፣ የአንጎላ ፕሬዚደንት በተለይ በቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ እንደማይወዳደሩ እና ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ካስታወቁ ወዲሃ ይበልጡን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ አጠናክረው በመከተል ላይ ናቸው። ይህንን አነጋገር የሚጠራጠሩት ብዙ ተንታኞች የነዳጅ ዘይቱ ገቢ መቀነሱ እንደማይቀር ስለማይቀር ቀነሰ በመሄዱ በገበያ ዋጋ የተነሳ ፣ ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ የስልጣናቸውን መሰረት ለማጠናከር ቁልፍ ቦታዎችን ለዘመዶቻቸው ለመስጠት መሞከራቸው እንደማይቀር ይገምታሉ። አንጎላውያን የሀገሪቱን የስልጣን ኮርቻ ከተቆናጠጡ ከሶስት አሰርተ ዓመት በላይ በሆናቸው በሀገሪቱ ፕሬዚደeንት አሰራር መሰላቸታቸውን የገለጸው ጋዜጠኛው እና የመብት ተሟጋቹ ራፋየል ማርኬስ «ማካንጎላ» በተሰኘው የኢንተርኔት ድረ ገጹ ባሰፈረውአንድ ጽሑፍ፣ ፕሬዚደንቱ ቢቻላቸው ከዘመዶቻቸው አልፈው ስልጣኑንን ለቤት እንሰሶቻቸውም ለመስጠት ይሞክሩ ነበር ሲል ተሳልቆባቸዋል።
አንቶንዮ ካሽካሽ/አርያም ተክሌ
እሸቴ በቀለ

Isabel dos Santos (Buchcover)
ምስል DW/J. Carlos
Präsidentschaftskandidat Jose Eduardo dos Santos Angola
ምስል picture-alliance/dpa
Isabel dos Santos
ምስል picture-alliance/dpa