1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ተስፋዬ ዲንቃ ዜና እረፍት

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2009

ኢትዮጵያን ከሚኒስትር ዴታ እና ሚኒስትርነት አንስተዉ፣ ከ1981 እስከ 83 ሚያዝያ ወር በዉጭ ጉዳይ ሚኒስርነትና ከ19 83 ሚያዝያ እስከ ግንቦት 1983 ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አቶ ተስፋዮ ዲንቃ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ ተሰማ።

https://p.dw.com/p/2U2U3
Symbolbild Kerze
ምስል Fotolia/ stokkete

Tesfaye Dinka Obituary - MP3-Stereo

ከ1983ዓ,ም መጨረሻዎቹ ወራት አንስቶ በስደት በዉጭ ሃገር የቆዩት አቶ ተስፋዬ ከሦስት ቀናት በፊት ማረፋቸዉን በድረገጽ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ኢትዮጵያን በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ በመሆን ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት አገልግለዋል። በእሳቸዉ የወጣትነት ዘመን ዘመናዊዉን ጥሩ ትምህርት የቀሰሙ እና ሀገሪቱን በለዉጥ ጎዳና ለማራመድ ከሞከሩ አብዛኞቹ ተምረዉበታል የሚባለዉ የጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ፍሬ ናቸዉ። አምቦ ከተማ የተወለዱት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸዉን በዩናይትድ ስቴትስ ባይሩት እና ሲራከስ ዩኒቨርሲቲዎች ሠርተዋል። በብሔራዊ ሃብት ልማት ተጠባባቂ ሚኒስትርነት፤ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚኒስትር ዴታነት እስከ ሚኒስትርነት፣ በገንዘብ ሚኒስትርነት፤ በእርሻና ኢንዱስትሪ ልማት ባንክም በኃላፊነት፣ ያገለገሉት አቶ ተስፋዬ፣ በዘመነ ደርግ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆንም ሠርተዋል።

በኢትዮጵያ የአጭር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸዉ የሚታወቁት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ በደርግ ዘመን የመጨረሻዎቹ ቀናት በትጥቅ ትግል ሥርዓቱን ለመጣል ሲታገሉ ከነበሩት ዛሬ አስመራ እና አዲስ አበባ ላይ በትረ መንግሥቱን ከጨበጡት ኃይሎች መሪዎች፤ እንዲሁም ዛሬም በትጥቅ ትግል መቀጠሉ ከሚነገርለት ኦነግ ጋር በተካሄደዉ ያልተሳካ ድርድር መንግሥታቸዉን ወክለዉ ወደ ለንደን ከተጓዙት አንዱ ነበሩ። አብረዋቸዉ ባይማሩም በሥራ እንደሚያዉቋቸዉ የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ ዲንቃን ከሚያዉቋቸዉ መካከል በዚሁ ዘመን በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለአጭር ጊዜ ያገለገሉት ስመ ሞክሼያቸዉ አቶ ተስፋዬ አቶ ተስፋዬ ታደሰ በጣም የበሰሉ ሰዉ በማለት ያስታዉሷቸዋል።

አያይዘዉም ለቤተሰቦቻቸዉም መፅናናትን፤ ለሟቹም ነፍስ እረፍትን ተመኝተዋል። አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከሄዱ በኋላ ከዓለም ባንክ እና ከተለያዩ የዉጭ ተቋማት ጋር መሥራታቸዉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በ77 ዓመታቸዉ ማክሰኞ ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ባለትዳር እና ለአራት ልጆችና የልጅ ልጆች አባት ነበሩ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ