1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«አታላንታ» ተልዕኮ አምሥተኛ ዓመት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2006

የአውሮጳ ህብረት ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ተልዕኮ ለማካሄድ የወሰነው በአፍሪቃ ቀንድ የሚታየውን የባህር ላይ ውንብድናን ለመታገል ቆርጦ በተነሳበት ጊዜ ነበር። « አታላንታ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው እና ከአምሥት ዓመት በፊት የተጀመረው ይኸው የኅብረቱ ፀረ የባህር ላይ ወንበዴዎች ተልዕኮ የተሳካ ውጤት ማስገኘቱ ነው የሚነገረው።

https://p.dw.com/p/1AcjA
Operation Atalanta Marine Soldaten Einsatz gegen Piraterie
ምስል Bundeswehr/FK Wolff

በዚሁ አካባቢ ከሶማልያውያን የባህር ላይ ወንበዴዎች ጋር ከሞላ ጎደል ግጭት የለም። በአሁኑ ጊዜ በሶማልያ የባህር ጠረፍ በሚንቀሳቀሰው የአውሮጳ ህብረት የ«አታላንታ» ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉት ወታደሮች አካባቢውን ከባህር ወንበዴዎች ጥቃት ነፃ ለማድረግ በየዕለቱ የሚያካሂዱትን ተግባራቸው ብዙ ጊዜ በሰላም ነው የሚያከናውኑት። ተልዕኮው ሲጀመር ግን እንዲህ አልነበረም። ከባህር ላይ ወንበዴዎቹ ብዙ ፈተና ነበር የገጠመው።

Pirat Somalia
ምስል AP Photo/Farah Abdi Warsameh

እአአ በ2008 ዓም ብቻ የባህር ላይ ወንበዴዎች በአፍሪቃው ቀንድ 42 መርከቦችን ባገቱበት ጊዜ ነበር ህብረቱ በሶማልያ የባህር ጠረፍ በአንፃራቸው ርምጃ መውሰድ የሚያስችለውን ተልዕኮ ለመጀመር ውሳኔ ያሳለፈው። የአውሮጳ ኅብረት የጦር መርከብ በሶማልያ የባህር ጠረፍ የቁጥጥር ተልዕኮውን የጀመረው በዚያዉ በ2008 ዓም በታህሳስ ወር ነበር። በዚሁ የመጀመሪያው ተልዕኮው ወቅት አንድ የግብፅ ዕቃ ጫኝ መርከብ በባህር ላይ ወንበዴዎች ሊታገት የነበረበትን ስጋት በሄሊኮፕተሮቹ በወሰደው ርምጃው በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ማስቆም ችሎዋል።

የአውሮጳ ህብረት ወታደሮች ቀዳሚ ተግባር እርግጥ በ2008 ዓም ከሶማልያ ሕዝብ መካከል ለአንድ ሦስተኛው የምግብ ርዳታ ያመላልሱ ለነበሩትን የተመድ የምግብ ድርጅት መርከቦች ከለላ መስጠት ነበር። ይህንኑ ተግባር በባህሩ እና ተልዕኮውን በመምራቱ ረገድ ከፈረንሳይ፣ ግሪክ እና የፖርቱጋል ወታደሮች ጎን 1,400 የጀርመን ብሔራዊ ጦር ወታደሮችም ያከናውኑ ነበር።

Somalia Anti-Pirateneinsatz Atalanta
ምስል AP

በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት የመከላከያ ኮሚቴ መሪ የሆኑት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ካትያ ኮይል የ«አታላንታ» ተልዕኮ የተሳካ መሆኑን አረጋግጠዋል።

« ተልዕኮው ከተጀመረ ወዲህ ከ200 የሚበልጡ መርከቦች ከለላ አግኝተዋል። ወደ አንድ ሚልዮን ቶን የሚጠጋ የምግብ ርዳታ ወደ ሶማልያ ደርሷል። የባህር መተላለፊያውን አስተማማኝ የማድረጉ ሁለተኛው ተግባርም ተሳክቶ በዚያ በአውሮጳ ኅብረት ወታደሮች ህልውና ብቻ የተነሳ እንኳን የባህር ላይ ወንበዴዎች ጥቃት በጉልህ ሊቀንስ ችሎዋል።»

ይሁንና፣ አውሮጳውያኑ ተልዕኮውን የጀመሩት ለሶማልያውያኑ የሰብዓዊ ርዳታ የሚደርስበትን መንገድ ለማረጋገጥ ብቻ እንዳልሆነ ኮይል አስረድተዋል። በኤክስፖርት ላይ ጥገኛ የሆነችው ጀርመን ዋነኛውን የንግድ መርከቦች መተላለፊያ የሆነውን የኤደን ባህረ ሠላጤን አስተማማኝ የማድረግ ጥቅሟን የማስጠበቅ ፍላጎትም አላት። ከዚህ በተጨማሪም ተልዕኮው ለባህር ላይ ውንብድና መንሥዔ ለሆነው ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ ያላፈላለገ ነው በሚልም ተቺዎች ወቀሳ ሲያቀርቡ ይሰማሉ።

በአውሮጳ ህብረት እዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የ«አታላንታ» የጦር ተልዕኮ ቻይናን እና ሩስያን ከመሳሰሉ ሃገራትም ጋ በቅርብ ተባብሮ መሥራቱ በብራስልስ እንደ ትልቅ ስኬት ታይቷል። ይሁን እንጂ፣ በብሪታንያ የጥናት ድርጅት «ቻታም ሀውስ» የባህር ላይ ውንብድና አጥኚ ወይዘሮ አጆአ አኒማዱ ፀረ ባህር ላይ ወንበዴዎች ተልዕኮ ለተሳካበት ድርጊት ድርሻ ያበረከተው የ«አታላንታ» እና የአጋሮቹ ትብብር ብቻ አይደለም ባይ ናቸዉ።

«ፀረ ባህር ላይ ወንበዴዎች ትግል የተሳካው በአውሮጳ ህብረት «አታላንታ» ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ በሕንድ ውቅያኖስ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን «ኔቶ» እና ዩኤስ አሜሪካ የሚመሩዋቸው ሌሎቹ ሁለት ተልዕኮዎችም ባበረከቱትም ድርሻ ጭምር ነው።»

ሉድገር ሻዶምስኪ/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ