1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ርምጃና የተመድ ዉግዝት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 19 2004

ከእርምጃዉ ጀርባ ያለዉ ምክንያት ምንም-ሆነ ምን ዉሳኔዉ በአካባቢዉ ለሚኖረዉ ሕዝብ ጥቅም ሲባል ይለወጣል የሚል ተስፋ ነዉ-ያለን።አሁን ባለንበት ደረጃ እርምጃዉ በርዳታ ፈላጊዎች ላይ ሥለሚያደርሰዉ ተፅዕኖ ለመናገር ገና ነዉ።ትናንት ነዉ የተፈፀመዉ

https://p.dw.com/p/RzCe
ምስል AP

29 11 11

የሶማሊያ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አ-ሸባብ ደቡባዊ ሶማሊያ የሚሠሩ የርዳታ ድርጅቶችን ማገዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አወገዘ።የአ-ሸባብ ታጣቂዎች ትናንት ደቡባዊ ሶማሊያ ዉስጥ ይሰሩ የነበሩ የተባበሩት መንግሥታትና የተለያዩ የርዳታ ድርጅቶች ንብረትን ዘርፈዋል፥ ቢሯቸዉንም ሰበብረዋል።እርምጃዉን ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፉ ድርጅት ባለሥልጣናት አዉግዘዉታል።የድርጅቶቹ መታገድና መዘረፍ ለረሐብ ለተጋለጠዉ የሶማሊያ ሕዝብ የሚሠጠዉን እርዳታ ያስተጓጉለዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።ነጋሽ መሐመድ ናይሮቢ የሚገኘዉን የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ ርዳታ ማስተባባሪያ ፅሕፈት ቤት ባልደረባን አነጋግሮ ያጠናቀረዉ ዘገባ አለ።ናይሮቢ ሆነዉ-ለሶማሊያ ሕዝብ የሚላከዉን ርዳታ የሚመሩና የሚያስተባብሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከትናንት በፊት ለድርጅታቸዉ የደረሰ ማስጠንቀቂያ-ማሳሰቢያ ማስታወሺያም የለም።ትናንት ሁሉም ሆነ።

«ታዉቃለሕ፥ የበርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፅሕፈት ቤቶች የሚገኙባቸዉ ቅጥር ግቢዎች፥ ንብረቶች፥ የርዳታ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች ሳይቀሩ ተመዘበሩ።ከዚሕ በተጨማሪ አሸባብ በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች መስራት አይችሉም የተባሉ ድርጅቶችን የሚያስረዳ ደብዳቤ ተሰጠቸዉ።»

ረሰል ጌኪይ።መንበሩን ናይሮቢ-ኬንያ ያደረገዉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባባሪያ ቢሮ የሶማሊያ ጉዳይ ቃል አቀባይ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፥ የሕፃናት መርጃ ድርጅት፥ የአለም ጤና ድርጅት፥ የኖርዌና የዴንማርክ የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች ፅሕፈት ቤቶች ዉስጥ የነበሩ ኮምፒዉተሮች፥ ለተረጂዎች ሊከፋፈሉ የተከማቹ መድሐኒቶችና ሌሎች ቁሳቁሶች ተያዙ።ፅሕፈት ቤቶቹ ተዘጉ።ሁለት ድርጅቶች ግን ከዘረፋ-እገዳዉ አምልጠዋል።የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ኮሚቴ እና ድንበር የለሽ ሐኪሞች ብቻ።

አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ትናንት ባወጣዉ መግለጫ መሠረት አስራ-ስድስት የርዳታ ድርጅቶች ድርጅቱ በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች መንቀሳቀስ አይፈቀድላቸዉም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ፓን ጊ ሙን የአሸባብን ርምጃ አዉግዘዋል።የድርጅቱ የሰብአዊ ርዳታ ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ ቫለሪ አሞስ እንዲሁ።አሞስ እንደሚሉት የአሸባብ እርምጃ ለረሐብ የተጋለጠዉን ሕዝብ ሕይወት ለማዳን የሚደረገዉን ጥረት የሚያደናቅፍ ነዉ።እና መቀልበስ አለበት።

የሚቀለበስበት ብልሐት-እርምጃ ግን ላሁኑ አይታወቅም።ረስል ጌኪይም ከተስፋ-ሌላ ሌላ የሚሉ የሚያቁትም የለም።

World Food Programme Nahrungsmittellieferung Somalia
ርዳታምስል AP

«ከእርምጃዉ ጀርባ ያለዉ ምክንያት ምንም-ሆነ ምን ዉሳኔዉ በአካባቢዉ ለሚኖረዉ ሕዝብ ጥቅም ሲባል ይለወጣል የሚል ተስፋ ነዉ-ያለን።አሁን ባለንበት ደረጃ እርምጃዉ በርዳታ ፈላጊዎች ላይ ሥለሚያደርሰዉ ተፅዕኖ ለመናገር ገና ነዉ።ትናንት ነዉ የተፈፀመዉ።ያም ሆኖ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ድርጅቶች ባካባቢዉ ሥላለዉ ዉኔታ አያጠኑ ነዉ።»

ዘንድሮ የአፍሪቃ ቀንድን በመታዉ ድርቅና ረሐብ ክፉኛ የተጎዳዉ የሶማሊያ ሕዝብ ነዉ።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሶማሊያ ዜጎች የርዳታ እሕል-መድሐኒት ጥገኞች ናቸዉ።ጌኪይ እንደሚሉት አሸባብ ዕርዳታ በሚያቀርቡት ድርጅቶች ላይ የወሰደዉ እርምጃ የእርዳታ ፈላጊዎችን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጡ ነዉ-አሳሳቢዉ።

«ያሁኑን ጨምሮ እንዲሕ አይነቱ ሥራን የሚያጉል እርምጃ ለችግረኛዉ ሕዝብ የሚሰጠዉን ርዳታ ማቋረጡ በጣም ያሳስበናል።በተለይ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀዉስ ባለበት በደቡባዊ ሶማሊያ ለሚገኘዉ ሰወስት ሚሊዮን ሕዝብ በተለይ ደግሞ ለከፋ ረሐብ የተጋለጠዉ ሁለት መቶ ሐምሳ ሺሕ ሕዝብ ርዳታ በጣም መሠረታዊ በሆነበት በዚሕ ወቅት እንዲሕ አይነት እርምጃ መወሠሰዱ በጣም አሳሳቢ ነዉ።»

አሳሳቢ ነዉ።የአሽባብ መሪዎች ግን እስካሁን ከአቋማቸዉ ፈቅ አላሉም።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ