1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብና የአል ቃኢዳ ግንኙነት፣

ሐሙስ፣ ኅዳር 19 2006

ባለፈው መስከረም በኬንያ መዲና በናይሮቢ ፤ የሶማልያው አክራሪ እስላማዊ ድርጅት (አሸባብ)WESGATE በተሰኘው ዐቢይ የገበያ አዳራሽ፣ አደጋ በመጣል ከ 60 በላይ ሲቭሎች መግደሉ የሚታወስ ነው። እ ጎ አ በ 2006 የሶማልያ የሸሪያ ፍርድ ቤቶች ሕብረት

https://p.dw.com/p/1AQEW
ምስል picture-alliance/AP

ከፈረሰ በኋላ የተመሠረተው አሸባብ፣ በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኀን አገላለጽ ፤ ከአል ቃኢዳ ጋር ቁርኝት ያለው እንዲሁም ከአንድ ማዕከላዊ የበላይ አመራር ትእዛዝ የሚቀበል ነው የሚመስለው። ዩናይትድ ስቴትስ በተለይ፤ ይህን መሰል አመለካከት ነው ያላት። ስለድርጅቱ አሠራር ምርምር ያደረጉት፣ በበርሊን የጀርመን የሳይንስና ፖለቲካ ተቋም ባልደረባ፤ ጊዶ ሽታይንበርግ ግን ድርጅቱ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኑነት ቢኖረውም ራሱን ችሎ ፣ በራሱ የሚመራ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።

የናይሮቢው ጥቃት ከተፈጸመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፤ «አቆስጣዎች»(SEALS) በመባል የታወቁ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ የጦር ኃይል አባላት፣ የጥቃቱ እቅድ አውጭ ተብሎ የተጠረጠረውን ኬንያዊ የአሸባብ ጦር መሪ ለመግደል በደቡብ የሶማልያ የወደብ ከተማ ባሮዌ፣ ሙከራ አድርገው መክሸፉ የሚታወስ ነው። እንደ አሜሪካውያኑ ግንዛቤ፤ አሸባብ፤ በሶማልያ መንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች ሃገራትና ከዚያም ባሻገር ሥጋት የደቀነ አሸባሪ ድርጅት ነው። ጊዶ ሽታይንበርግ ፤ ድርጅቱ እስከዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊመደብ የሚችል አለመሆኑንና በራሱ አቅድ እንደሚመራ ነው የሚናገሩት።

Mombasa Anschlag auf radikal islamischen Prediger Ibrahim Ismail
ምስል Getty Images/AFP

«ባጠቃላይ በዩናይትድ ስቴትስ ፣ ስለ አል ቃኢዳ ቅርንጫፎችን የተዛመተውን ነባቤ ቃል በጥርጣሬ ነው የምመለከተው። እንደሚመስለኝ፤ የተለያዩት የታወቁት ድርጅቶች፣ በዐረቡ ዓለምና በአፍሪቃ ያሉትን በአንድ ዓይነት መዋቅር ሥር እንደሚገኙ አድርጎ ማስቀመጥ አይቻልም። አንድ ድርጅት አለ። በሌላ ድርጅት ሥር ያለ! ይህም ለተቀባዮች ትእዛዝ የሚሰጥ ነው። እናም፣ እዚህ ላይ የየመኑን የኢራቁንና የአልጀሪያውን አል ቃኢዳ መጥቀስ ይቻላል። »

የአሸባብ ተዋጊዎች በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ 3,000 ይህል ሲሆኑ ፤ እነርሱም በሚገባ ሥልጠና የተሰጣቸው በውጊያም ልምድ ያገኙ መሆናቸው ነው የሚነገረው። በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ሶማልያ ከገባ በኋላ፣ አሸባብ ሲደራጅ ከውጭ በተለይም ከየናይትድ እስቴትስ፤ ከብሪታንያና ከአስዊድን በተመለሱ በዛ ባሉ ሶማሌዎች ተጠናክሮ ነበር። እ ጎ አ በ 2007 እና 2008 ከተጠቀሱት አገሮች «ነጮች » የጂሃድ ጦረኞች ከዐረቡ ዓለምና ከፓኪስታን ጭምር በተናጠል እየገቡ መቀላቀላቸው አልታበለም።

አሸባብ ከአልቃኢዳ ግንኙነት ይኑረው እንጂ ትእዛዝ ተቀባይ አይደለም ያሉበትን ምክንያት ጊዶ ሽታይንበርግ ሲያብራሩ--

«የአል ቃኢዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ከተገደሉ በኋላበዛ ያሉ ሰነዶች ተገኝተዋል። የተለያዩት የአልቃኢዳ ቅርንጫፎች እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ሐሳባቸውንያሠፈሩበት ሰነድ ጭምር! ይሁንና የተለያዩት ድርጅቶች ለዚህ በተግባር ቀጥተኛ ምላሽ እንዳልሰጡ የአልቃኢዳ ከፍተኛ አመራር አባላትን ትእዛዝም ሆነ መመሪያ እንዳልተከተሉ መገንዘብ ያቻላል። ይህም፤ ዐረባውያን ኧል ቃኢዳ ድርጅቶችና በተለይም የሶማልያውን ቅርንቻፍ ማለትም አሸባብን ይመለከታል። በአሸባብ አጠቃላይ ስልታዊ እንቅሥቃሴና ታክቲክ የአልቃኢዳ ከፍተኛ አመራር አባላት ተጽእኖ አለ ብሎ በፍጹም ማረጋገጥ አልተቻለም። »

Somalia Mogadishu Explosion Restaurant 15 Tote
ምስል Reuters

ከ 3 ዓመታት በፊት በዩጋንዳ ፤ ባለፈው መስከረምም፣ በኬንያ ብርቱ ጥቃት የሠነዘረው አካባቢያዊው አክራሪ ድርጅት ለአፍሪቃው ቀንድ ጠንቀኛ ነው ተብሎ ከታመነበት መቋቋሚያው ዘዴም ሆነ መላው ምን ይሆን/? አሸባብ ፤ ከዩጋንዳና ኬንያ ቀጥሎ፤ 3ኛዋ ሀገር ኢትዮጵያም በሶማልያ ጉዳይ ጣልቃ ገብ ናት በማለት አሸባብ አደጋ ለመጣል ከመሞከር እንደማይቦዝን ሽታይንበርግ በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢው ነው ብለዋል። በሌላ በኩል፤ ራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ሰብአዊ መብትን ይበልጥ ለማረቅና የተቃውሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መፈናፈኛ ለማሳጣት ወይም በጥብቅ ለመከታተል ነው ቁጥጥሩን የሚጠቀምበት የሚሉም አሉ። ጊዶ እሻታይንበርግ ጉዳዩን እንዴት እንደሚመለከቱት ተጠይቀው ቀጠል በማድረግ---

«እኔም እንዲሁ እንደተባለው ነው የምመለከተው። ራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው ጉዳዩን የሚያቀርበው፣ ሥጋት ተደቅኖአል በማለት! ይሁን እንጂ፤ የአሸባብ አደጋ የመጣል ፍላጎትም ሆነ ጥረት፣ መሠረት የሌለው ነው ማለት አይቻልም። እ ጎ አ ከ 2006 አንስቶ አሸባብ ዕድል ካገኘ ኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን የሽብር ተግባር ለማከናወን መጣሩ አይቀርም።

Somalia Anschlag Maka Al-Mukarama Mogadischu
ምስል Reuters

እንደሚመስለኝ ፤ ሁለት የተለያዩ ዐበይት ጉዳዮች አሉ። አንደኛው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ጭቆናን በተሣካ ሁኔታ ማጠናከሪያ ዘዴ ነው ፤ ከሌሎች ለምሳሌ ያህል ከዩጋንዳ በላቀ ሁኔታ! 2ኛ፤ እንደኔ ግምት (በዚያ በኩል ዕውቀቱ አለኝ አልልም፤)እንደሚሰማኝ ግን አሸባብ በኬንያ የዘረጋው ስንቅና ትጥቅ የማሸጋገሪያ ችሎታው ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያ መጠን ሊያከናውነው የሚቻለው ጉዳይ አይደለም። አዎ ፤ በኢትዮጵያ ላይ እጅግ ከፍ ያለ የጠላትነት ስሜት ነው ያለው። አጋጣሚም ሆነ ዕድል ካገኘ ኢትዮጵያም ውስጥ አደጋ ከመጣል አይመለስም። ስለዚህ ሥጋቱ መሠረት የሌለው አይደለም። »

የአሸባብ ተቀዳሚ ግቦች፤ የሶማልያን የሽግግር መንግሥት አስወግዶ፣ በሸሪያ የሚተዳደር የሶማልያ መንግሥት መመሥረት፤ ከዚያም ታሪካዊ ጠላትና የክርስቲያኖች ሀገር እያሉ ብዙዎች ሶማሌዎች በሚጠሏት ኢትዮጵያ ላይ ማትኮር ይሆናል እንደ ተመራማሪው ጊዶ ሽታይንበርግ አገላለጽ!

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ