1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአረቦቹ ዉዝግብ ዉስጥ አስገራሚዉ የሶማሊያ አቋም፤

ሐሙስ፣ ነሐሴ 18 2009

ሳዑድ አረቢያ እና ተባባሪዎቿ አራት የአረብ ሃገራት ቀጠርን የማግለል ርምጃ ሲወስዱ፤ ከሳዑዲ ጋር የቅርብ ትስስር ያላት የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀገራቸዉ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ አድርገዋል።  እንዲያም ሆኖ የፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆች መንግሥት አስተዳደር ዉስጥ እሳቸዉ የወሰዱትን አቋም የሚቃወሙ ፖለቲከኞች አሉ።

https://p.dw.com/p/2inKy
Somalia Mohamed Abdullahi Farmajo
ምስል Getty Images/AFP/M. Haji Abdinur

የሶማሊያ አቋም እነሳዉዲን አስደንግጧል፤

ፕሬዝደንት መሐመድ ከሪያድ ጎን አለመቆማቸዉ የተረጋጋ መንግሥታቸዉን አደጋ ላይ እንዳይጥለዉ ስጋት አለ። ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ፤ በአረብ ሐገራት  ዉዝግብ  መንግስታቸዉ ገለልተኛ አቋም እንዲይዝ ማድረጋቸዉ ብዙዎችን አስገርሟል። አስተዳደራቸዉም ወንድማማቾቹ ሃገራት ልዩነታቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። ይህም  በአካባቢዉ ፤ በተለይም በሶማሊያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ላላቸዉ ለሳዑዲ እና ለተባበረዉ አረብ ኤሜሬቶች አስደንጋጭ ሆኗል።

ሳዑዲ አረቢያ የሶማሊያ ዋነኛ የንግድ አጋር ናት።ፕሬዝደንት ፎርማጆ በየጊዜዉ ለሶማሊያ ጠቀም ያለ ገንዘብ የምትለግሰዉን እና በተመረጡ ማግሥት ታማኝነታቸዉን ሄደዉ ያረጋገጡባትን የሪያድን ወዳጅነት ጥያቄ ላይ የሚጥል ርምጃ ለመዉሰድ እንዴት ደፈሩ? ሶማሊያዊዉ ጋዜጠኛ እና የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ ሙሐይዲን አህመድ ሮብሌ፤

«እንደሚመስለኝ ለሶማሊያ መንግስት የዉጭ ፖሊሲ ዉሳኔ በምሁራኑ ፍላጎት እና የመረዳት ሁኔታ ላይ የመረኮዘ አይነት ነዉ። በተለይም በተወሰነዉ ጊዜ እና ዓመት ያሉት የሀገሪቱ መሪዎች የግል ፍላቶች ጉዳይ ነዉ። ይህም ጉዳይ ከዚያ የተለየ አይደለም። የአሁኑ ፕሬዝደንት ቀጠር በዚህ ዓመት ምርጫ ሲካሄድ የእርሱን እንቅስቃሴ በመደገፏ ባለዉለታዉ ናት። ምርጫዉ ደግሞ እጩዉ በላዕላይ እና ታህታይ ምክር ቤት ለሚገኙ ለሕዝብ ተወካዮች በሚያቀርበዉ የገንዘብ መጠን የሚወሰን ነዉ። እናም ቀጠር ባትደግፋቸዉ ኖሮ ሊመረጡ እና ፕሬዝደንት ሊሆኑ አይችሉም ነበር ተብሎ ይታመናል።  እናም ቀጠር ባለዉለታቸዉ ናት።»

ጋዜጠኛዉ እንደሚለዉ በምርጫዉ ወቅት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ፤ እጅግም ድጋፍ ያልነበራቸዉና የመጨረሻዉ ሰዉ ነበሩ። ከቀጠር ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ ግን በምርጫዉ አሸንፈዋል። ከዚህም ሌላ ፕሬዝደንቱ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በሶማሊያ ዉስጣዊ ጉዳይ አላግባብ እጇን ከትታለች የሚል አቋምም አላቸዉ። ኤሜሬቶች ማዕከላዊዉን የሶማሊያ መንግሥት ያላካተተ ዉል ከየፌደራል  መንግሥታት ጋር እንደሚፈራረሙም ጠቅሷል። በምሳሌነትም ከፑንትላንድ እና ሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ያነሳል። በዚህም ምክንያት የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሳዉዲ መራሹ  ትብብር ቀጠርን ለማግለል የወሰደዉን ርምጃ የሚያዳክም ትብብር ማድረጋቸዉ ታይቷል። የሶማሊያ ርምጃ በአካባቢዉ ባለዉ የኃይል ሚዛን ላይ የሚኖረዉን ተፅዕኖ በተመለከተ ሲናገርም፤

Karte Mitgledsstaaten Gulf Cooperation Council ENG

«የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢን በተመለከተ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ሳዉዲ አረቢያ በግንባር ቀደምትነት ከዚያም ደግሞ ቀጠር ትልቅ ተፅዕኖ አላቸዉ ተብሎ ይታመናል። ይህ ግን እየተቀየረ ነዉ፤ ቀጠር በአካባቢዉ ሰፋ ያለ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የላትም፤ ከሶማሊያ ጋር ብቻ ነዉ ጥሩ ግንኙነት ያላት። ኤርትራ እና ጅቡቲን ብንመለከት ግን ድጋፋቸዉን ለሳዉዲ እና ኤሜሬቶች ነዉ ያደረጉት። ሆኖም እስካሁን ሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸዉ ገለልተኛ በመሆን ችግሩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ የሚጠይቁት።»

ጅቡቲና ኤርትራ ድጋፋቸዉን ለሳዑዲ አረቢያ ባሳዩ ወቅት ቀጠር ሁለቱ ሐገራት አወዛጋቢ ድንበር አስፍራዉ የነበረ ማዉጣቷን የጠቀሰዉ ሙሃይዲን አህመድ ሮቤ፤ የቀጠር ጦር እንደወጣ አስመራ ያንን ቦታ መያዟን አስታዉሷል። ይህ ደግሞ የአስመራን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ለሚከታተለዉ የአዲስ አበባዉ መንግሥት የሆነ መልዕክት እንዳስተላለፈም ያምናል።

Qatar Airways
ምስል picture alliance/dpa/epa/Stringer

«ኤሜሬት ኤርትራ ዉስጥ ወታደራዊ የጦር ሰፈር አላት፤ ሳዑዲ ደግሞ ምናልባት ከኤርትራ መንግሥት ጋር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እየተደራደረች ይሆናል ፤ ይህ ደግሞ ከሚያወዛግባት ግዛት የኤርትራን ኃይሎች ማስወጣት እንድትችል ለጅቡቲ የገንዘብም ሆነ የጦር ድጋፍ የምታደርገዉ ኢትዮጵያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ይከታታል።»

ፕሬዝደንት አብዱላሂ ፎርማጆ የወሰዱት አቋም ከዚህም በላይ አሁን የተረጋጋች በምትመስለዉ ሶማሊያ ዉስጥም ሌላ መዘዝ ሊኖረዉ እንደሚችል ነዉ የሚገምተዉ፤

«የፖለቲካ አለመረጋጋት ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ሶማሊያ ዉስጥ የሚደረጉት  ፖለቲካዊም ሆነ ብሔራዊ ዉሳኔዎች መቅዲሹ በሚገኘዉ ማዕከላዊ መንግሥት ብቻ አይደለም። የየግዛቱ መንግሥታትም ትልቅ ሚና አላቸዉ። የሶማሊያ ፌደራል ፈፅሟል ብዬ የምገምተዉ ስህተት ይህን ዉሳኔ ከማሳለፉ በፊት ሌሎቹን አላማከረም። ምክንያቱም እነዚህ ግዛቶች ከቀጠር ይልቅ ሳዑዲ እና ኤሜሬቶች ላይ ጠንካራ የኤኮኖሚ እና ፖለቲካ ፍላጎት አላቸዉ። የቀጠር ግንኙነት መቃዲሾ ላይ የተወሰነ ነዉ። መላ ሀገሪቱን ያዳረሰ የልማት ፕሮጀክት የላትም። በዚህም ምክንያት የየክልሉ መንግሥታት እና ፖለቲከኞች ቀጠርን የመደገፍ ፍላጎታቸዉ ትንሽ ነዉ። ከቀጠር ይልቅም ሳዉዲ አረቢያ እና ኤሜሬቶችን እንደዋና የገንዘብ ለጋሾች ነዉ የሚያዩዋቸዉ። በዚህ ምክንያትም ከእነዚህ ሃገራት ጎን መቆም ነዉ የሚፈልጉት። በአረብ ሃገራቱ መካከል ዉዝግቡ በቀጠለ መጠንም በሶማሊያ መንግሥት ዉስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ያባብሳል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ