1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን ተምች በአፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2009

በእንግሊዝኛዉ ስያሜዉ አርሚዎርም የሚል መጠሪያ ያለዉ የተምች ዘር ስያሜዉን ያገኘዉ በተናጠል ሳይሆን በኅብረት ሆኖ ሲንቀሳቀስ በመንገዱ ያገኘዉን ማንኛዉንም የተክል ዘር እያወደመ ስለሚጓዝ መሆኑን አንዳንድ የትርጉም ማብራሪያዎች ይጠቁማሉ።

https://p.dw.com/p/2cFQg
Simbabwe Landwirtschaft Tatenda Mapfumo
ምስል DW/C. S. Mavhunga

የአሜሪካን ተምች በአፍሪቃ

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሠረት ይህ ተክል አዉዳሚ በተለያዩ የደቡብ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ የአፍሪቃ ሃገራት እየተዛመተ እንደሚገኝ ማሳሰቡን ቀጥሏል። በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የእጸዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶ፤ ከሀገር ሀገር እየተዛመተ ስለሚገኘዉ ፀረ ሰብል ትል ምንነት ይናገራሉ።

ለጊዜዉ ሀገራዊ መጠሪያ ያልተሰጠበትም ምክንያት አላቸዉ፤ ቀደም ሲል የሚታወቅ መደበኛ ተምች በመኖሩ ከዚህ ከአዲስ መጤዉ ጋር ልዩነትም ሆነ አንድነት ስላላቸዉ አርሶ አደሩም ሆነ ሌሎች አካላት ግር እንዳይሰኙ፤ ተገቢዉ መረጃ እና ስልጠና እስኪሰጥ በሚል መቆየቱን አብራርተዋል። ሁለቱም ሰብል አዉዳሚ የተምች ዘሮች በበልግ ዝናብ ወቅት እንደሚከሰቱ ነዉ ባለሙያዉ ያብራሩልን። ይህ አዲስ መጤዉ የአሜሪካን ተምች በእድገት ሂደቱ ወደ በራሪ የእሳት እራትነት ይሻገራል።

BG Heerwurm - Larva
ምስል Phil Sloderbeck/Kansas State University/Bugwood.org

 የአንጎላ መንግሥት በሀገሪቱ ከፍተኛ በቆሎ አምራች በሆኑ አራት አካባቢዎች ይህ ፀረ ሰብል የሆነዉ ትል መዛመቱን፤ በአምስተኛዉ ግዛቱ ደግሞ የበቆሎ ግንድ በመቦርቦር የሚታወቅ ሌላ ፀረ ሰብል ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝም አስታዉቋል። አንጎላ ዉስጥ ብቻም ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ የበቆሎ፣ የአጃ እና የማሽላ ሰብል የወደመ ሲሆን፤ የደረሰዉ ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ወደ 1,8 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተገምቷል። በዚህ ፀረ ሰብል የትል መንጋ ምክንያትም በአብዛኛዉ በአነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ገበሬዎች መጎዳታቸዉ ነዉ የተነገረዉ። አቶ ዘብዴዎስ ፤ ጉዳት እንዳይደርስ እየተደረገ ነዉ ያሉትን እንዲህ ገልጸዋል።

መነሻዉ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ዉስጥ እንደሆነዉ የሚነገረዉ ይህ የትል መንጋ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 ነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የታየዉ። ቀስ በቀስ ከሰሃራ በስተደቡብ ወደሚገኙ ሃገራት በቆሎ እና ሌሎች የሰብል ምርቶችን እያወደመ መስፋፋቱ ተመልክቷል። በተለይ ደግሞ በኤሊንኞ ክስተት ምክንያት በድርቅ የተጠቃዉ ደቡባዊ አፍሪቃ ሚሊዮኖች የምግብ ርዳታ ፈላጊዎች ሆነዉ ሳለ፤ የዚህ ሰብል አዉዳሚ ትል መዛመት ችግሩን በማባባስ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል አስግቷል። ምንም እንኳን በዚህ ዓመት የዝናቡ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ጥሩ ምርት እንደሚታፈስ ተስፋ ቢደረግም ሰብልን በቁሙ የሚያወድመዉ ትል መስፋፋት እንዳሰጋት እና ወረርሽኙም እንደተከሰተባት አንጎላ አሳዉቃለች። የዚህ የመጤ ተምች ወረርሽኝ እንደተከሰተባቸዉ የገለጹ ሃገራት የእርሻ ምርታቸዉን ለዉጭ ንግድ ማቅረብ እንዳልቻሉም ተነግሯል።

BG Heerwurm - Adult
ምስል Lyle J. Buss/University of Florida/Bugwood.org

አሁን ባለዉ የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህ አዲስ መጤ የተምች ዘር የተከሰተበት አካባቢ በቆሎ ከተዘራዉ ወደ 1 መቶ ሰባሺ ህ ሄክታር መሩት 10 በመቶዉን እንኳ እንዳላዳረሰ ነዉ አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶ የገለጹልን። በዚህም ምክንያት እንደነአንጎላ የተምች ወረርሽኝ ተከስቷል ማለት እንደማይቻልም አመልክተዋል። ተምቹ በሌሎች ሃገራት ላይ ያደረሰዉ ችግርም ለኢትዮጵያ መነሻ በመሆኑ ፈጣን ጥንቃቄ ለመዉሰድ ረድቶናልም ባይናቸዉ። ይህ የተምች ዘር ርጥበትና ሞቃታማነት ባላቸዉ አካባቢዎች እንደሚራባ እና ያንን የአየር ጠባይ እንደሚፈልግም አመልክተዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ