1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአል ሲሲ ማንነት፤የግብፅ የሕዝባዊ አብዮትዋ ክሽፈት

ሰኞ፣ መጋቢት 22 2006

ያኔ-ከ21ዱ የወታደራዊ ሁንታዉ አባላት ሁሉ ወጣት ነበሩ።ያን ሚስጥር-በመናገራቸዉ የካይሮ ሠልፈኞችን በቁጣ፤ የመብት በተለይም የሴቶች መብት ተሟጋቾችን በዉግዘት ከማንጫጫቱ ባለፍ፤ ድምፀ ለሥላሳዉ ወጣት ጄኔራል የሚፈልጉትን ለማደረግ-የፖለቲካዉን ትኩሳት የለኩበት መግለጫ መሆኑን ያሰበ-ያስተዋል አልነበረም።

https://p.dw.com/p/1BZIA
ምስል picture alliance/AP Photo

የሚፈልጉትን ትልቅ ማዕረግ እራሳቸዉ ለራሳቸዉ ወስነዉ በሾሟቸዉ ፕዝዳንት እጅ ከትከሻቸዉ ላይ አስለጠፉ። ፊልድ ማርሻል ሆኑ።ጥር። የሚበልጥ ጉጉት፤ፍላጎትሲያድርባቸዉ ደግሞ እንዲያ የጓጉ፤የፈለጉትን የአፍሪቃም፤የአረብም ታላቅ ጦር ታላቅ ማዕረግንባለፈዉ ሳምን እራሳቸዉ፤በራሳቸዉ አዉልቀዉ ጣሉ።ፊልድ ማርሻሉ፤«አቶ»ነኝ አሉ።ሚስተር ወይም አል ሰይድ አብዱል ፈታሕ ሰኢድ ሁሴይን ቻሊል አስ ሲሲ።በመጪዉ ሰኔፕዝዳንት ይሆናሉ፤አል ረኢስ።የግብፅ ሕዝብም የማርሻል ማዕረጋቸዉን በሱፍ ከራባት ቀይረዉ ሰላሳ ሁለት ዘመን በብረት ጡንቻ ረግጠዉ የገዙትን ሆስኒ ሙባረክን ባደባባይ ሰልፍ-አመፅባስወገደበሰወስተኛ አመቱ የማርሻል ማዕረጋቸዉን ላወለቁት አዲስ ገዢዉ በይፋ ይገብራል።የአል ሲሲ ማንነት፤የግብፅ እዉነት፤የሕዝባዊ አብዮትዋ ክሽፈት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።ከ1970 (ዘመኑ በሙሉ እንድ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ወታደር ናቸዉ።የጦር መኮንን።ኋላየጦር አዛዥ-ጄኔራል።ከጥር ወዲሕ ፊልድ ማርሻል።በሕዝብ የተመረጡትን ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲን ባለፈዉ ሐምሌ በሐይል ከስልጣን ካስወገዱ ወዲሕ ደግሞ እንደ ጄኔራል፤ እንደ ፊልድ ማርሻልምየጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ፤ እንደ ሁሉን ሹዋሚ፤ ሻሪ፤ሸላሚ-አስገዳይ፤ ፈቺ-አሳሪ ሁሉን አድራጊ ፖለቲከኛ ናቸዉ።

የድምፅ-ቅላፄቸዉ፤ የቃላት ምርጫ -አሰዳደራቸዉ፤ ንግግራቸዉ ባጠቃላይ ግንከጦር ጄኔራል፤ማርሻልነታቸዉ ጋር አይዋደድም።ከሚንስትር ዋና ፖለቲከኝነታቸዉ ጋርም አይጣጥም። ለስላሳ ነዉ።ተራ ወይም የዘወትር።ቀጥታእና ደረቅ።

«ታላቁ የግብፅ ሕዝብ።የመከላከያ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ለመልቀቅ በመወሰኔ በወታደራዊ ዩኒፎርም (መለዮ)ከፊት ለፊትሕ ሥቆም ይሕ ለመጨረሻ ጊዜ ነዉ።የዚሕች ሐገሬን ተስፋ እና ምኞት ለማሳካት መላ ሕይወቴን በወታደርነት ሳገለግል ኖሬያለሁ።አገልግሎቴን ወደፊትም እቀጥላለሁ።»

Schwache Konkurrenz in den Präsidentenwahlen in Ägypten
ምስል DW/A. Hamdy

አሉ ባለፈዉ ሳምንትሮብ።

ለስላሳ ድምፅ፤ ተራ ቃላት፤ ደረቅእና የአካላት እንቅስቃሴ አልባ ንግግር።መፈንቅለ መንግሥትለማድረግለደፈረ የጦር አዛዥ፤ ሐገር ለመምራት ላቀደ ፖለቲከኛ ቀርቶ ለሐይማኖት ሰባኪም አይሆንም።ዲፕሎማት ባይሆኑ እንኳን በሳዑዲ አረቢያ የግብፅ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ሆነዉ የዲፕሎማሲዉን ዓለም በቅርብ አዉቀዉታል።ድምፅ አነጋገራቸዉ ግን ለዲፕሎማትነት አልተገራም። ላስተማሪ፤ ለጋዜጠኛነትም፤ አይጥምም።ምናልባት ለሰላይ ይሆን ይሆናል።

እሳቸዉ ግን ወታደርነታቸዉን ነዉ የሚወዱት።መለዮያቸዉን ነዉ የሚያፈቅሩት።«ይሕ ለኔ በጣም ወሳኝ ጊዜ ነዉ።ወታደራዊ መለዮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጠለቅሁት የአስራ-አምስት አመት ወጣት እያለሁ በ1970 አይር-ኋይል ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ሥገባ ነበር።ከአርባ አምስት ዓመት ግድም በፊት።ሐገሬን ከጥቃት የሚከላከለዉን ጦር መለዮ በመልበሴ ሁልጊዜ እኮራለሁ።»

የጦር አዋቂዎች እንደሚሉት ከአፍሪቃም፤ ከአረቡ ዓለምም በብዛትም በጥራት-ጥንካሬም አቻ የማይገኝለት-የግብፅ ጦር ባልደረባ መሆናቸዉን ቢኮሩበት አያስደንቅም።ደግሞስ ለዚሕ ያደረሳቸዉ ምን፤ማን ሆነና።ግን፤ ከ1948 ጀምሮ፤ የአረብና የእስራኤል ጦርነት፤ የግብፅ እና የብሪታንያ፤ የፈረንሳይ የእስራኤል ወይም (የስዊዝ ቦይ) ጦርነት፤የየመኖች ጦርነት፤ የስድስቱ ቀን ጦርነት፤የዮም ኩፑር ጦርነት፤ እየተባለ ከጦርነት-ግጭት ተለይቶ የማያዉቀዉ የግብፅ ጦር ባልደረባ በመሆናቸዉ የመኩራት ፤ የመፈራት-መከበራቸዉን ያሕል ባንድም ጦርነት ተዋግተዉ፤ አዋግተዉ አያዉቁም።

ሠላይ-አስላይ ግን ነበሩ።እንዲያዉም በ2011ከቀድሞዉ የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ሥልጣን የተረከበዉ የግብፅ ጦር ሐይሎች ላዕላይ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ የወታደራዊ ሥለላ (መረጃ ወይም ደሕንነት ይሉታል ስያሜዉን ሲያበጃጁት) የበላይ ሐላፊ ነበሩ።

Gericht in Alexandria verurteilt zwei Mursi-Anhänger zu Tod
ምስል picture-alliance/dpa

ወታደራዊዉ ሑንታዉ፤ አል-ሲሲ በቀደም «ታላቁ» እያሉ ያንቆለጳጰሱትን የግብፅ ሕዝብ አብዮት ድልን ነጥቆ የያዘዉን ሥልጣን እንደያዘ ለመቀጠል ማቀዱን በመቃወም ዳግም ተሕሪር አደባባይን ያጥለቀለቁ ወጣቶችን የሚከታተል፤ የሚሰልል፤የሚያስር ምናልባትም የሚገድለዉን ሰላይ ጦር የሚያሰማሩት እሳቸዉ ነበሩ።

ጦሩ በገፍ የሚያሥራቸዉን በተለይም ወጣት ልጃገረዶችን አስገድዶ የመድፈሩ ዜና እንደ ተቃዉሞ ሰልፉ ሁሉ ካይሮን ሲያጥለቀልቅ-እስከዚያ ጊዜ ድረስ ብዙም የማይታወቁት ሜጄር ጄኔራል ወደ መገናኛ ዘዴዎች ብቅ አሉ።«ሐሜት ወቀሳዉን፦ ለማጣራት፤ የእስረኞቹን ደሕንነት ለመጠበቅ፤ ጦሩን ከሐሜት ለማዳን እስረኞቹ ልጃገረድ መሆን አለመሆናቸዉን የሚያረጋግጥ ምርመራ ተደርጓል።» አሉ

ያኔ-ከ21ዱ የወታደራዊ ሁንታዉ አባላት ሁሉ ወጣት ነበሩ።ያን ሚስጥር-በመናገራቸዉ የካይሮ ሠልፈኞችን በቁጣ፤ የመብት በተለይም የሴቶች መብት ተሟጋቾችን በዉግዘት ከማንጫጫቱ ባለፍ፤ ድምፀ ለሥላሳዉ ወጣት ጄኔራል የሚፈልጉትን ለማደረግ-የፖለቲካዉን ትኩሳት የለኩበት መግለጫ መሆኑን ያሰበ-ያስተዋል አልነበረም።

Ägypten Muslimbrüder Demonstration Gewalt 27.03.2014
ምስል Reuters

ሰዉዬዉ በርግጥ እንዲያ ነበሩ።ናቸዉም።የሚፈልጉ፤ የሚመኙትን ብዙ አይናገሩም። ሕልም ፍላጎታቸዉ ግን፤ በቅርቡ የቀጠሩ ቴሌቪዥን ጣቢያ አል-ጀዚራ ባጋለጠዉ በሚስጥር የተቀዳ ንግራቸዉ «ሕልም» ያሉት ነዉ።

«አንድ ጊዜ በሕልሜ እንዲሕ የሚል ድምፅ ሠማሁ።ለማንም ያልሰጠነዉን ላንተ እንሠጥሐለን።ሌላ ሌሊት፤ በሌላዉ ሕልሜ ደግሞ ከፕሬዝዳንት ሳዳት ጋር ሆኜ አየሁ።እንዲሕ አሉኝ፤-የግብፅ ፕሬዛዳንት እንደምሆን እርግጠኛ ነበርኩ።እኔም መለሥኩላቸዉ፤-እንዲሕ ብዬ፤ የሪፕብሊኳ ፕሬዝዳንት እንደምሆን ሁል ጊዜም ርግጠኛ ነኝ።»

ለቅጂዉ ትትክክለኛነት ዶቸ ቬለ ሐላፊነቱን አይወስድም።ሰዉዬዉ ግን የሚፈልጉትን ለማደረግ፤ከሚመኙት ለመድረስ ያላደረጉና የማያደርጉት የለም።የጦር ትምርቱን ከካይሮ-እስከ ዋችፊልድ-ታላቅዋ ብሪታንያ፤ እስከ ፔንስሎቬንያ-ዩናይትድ ስቴትስ ተመላልሰዉ ተምረዉታል።

ጦርንት ግጭት በማይለዉ ጦር መሐል ሆነዉ ከዉጪ ጠላት ጋር ተዋግተዉ አዋግተዉ ግን አያዉቁም።ሳይዋጉ ሳያዋጉ ከብዙ የአገልግሎት፤ የእድሜ አቻዎቻቸዉ ቀድመዉ፤ ከተዋጉ-ካዋጉት የጦር ባለሟሎች እኩል፤ የሜጄር ጄራልነት ማዕረግ ለመለጠፍ ግን ለሆስኒ ሙባረክ ታማኝ ታዛዥነቱን ቻሉበት።ተሳካላቸዉም።

ፆም፤ ሶላት፤ ዱዓ-ሰደቃቸዉ« ጠብ» የማይል ሐይማኖተኛ ናቸዉ።ሐይማኖተኝነታቸዉን ከሙስሊም ወድማማቾች ማሕበር የወጡትን የፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲንና ያማካሪዎቻቸዉን ቀልብ በቀላሉ ለመሳብ ተጠቀሙበት።ወይም ጠቀማቸዉ።ሙርሲ የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን በያዙ በወሩ የሰባ ሁለት ዓመቱን መከላከያ ሚንስትርና የወታደራዊ ሁንታዉን መሪ ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን አል-ተንታዊን ሻሩ።

ከአንጋፋዎቹ ጄንራሎች ሁሉ አል-ሲሲን መርጠዉ የመከላካያ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ከሙሉ ጄንራልነት ማዕረግ ጋር አስረከቧቸዉ።ነሐሴ አስራ-ሁለት 2012።አል-ሲሲ እንደተሾሙ የሙስሊም ወንድማማቾችን ማሕበርን የሚጠሉ፤የሚፈሩ፤ ማሕበሩን የማያዉቁ፤ ሥልጣን ለመቀማት የሚሹ የዉጪም የዉስጥም ፖለቲከኛና የፖለቲካ ተንታኝ የሚባሉ ሁሉ ጄኔራሉ የሙስሊም ወንድማማቾች ታማኝ መሆናቸዉን ለማሳመን ያለሰጡት ምክንያት እና ትንታኔ-አልነበረም።

መሐንዲሱ፤ ሐይማኖተኛዉ፤መምሕሩ ፕሬዝዳንትም የሳቸዉንም፤ የማሕበራቸዉንም ፖለቲካዊ-ማሐበራዊ፤ ሕይወት ነፃነትም የሚያነድ-የደጋፊ፤ተከታይ አባሎቻቸዉን ሕይወት የሚያጠፋ እሳት ከጉያቸዉ መታቀፋቸዉን ለማወቅ ፤ብልጠቱ፤ መረጃዉ ፋታዉም አልነበራቸዉም።

Proteste Massenprozess gegen Muslimbrüder in Ägypten
ምስል picture-alliance/dpa

ጄኔራሉ-ሿሚ፤ሸላሚያቸዉ እንዳይነቁ ከዉጪም አመቺ ጊዜ-እስኪያገኙ ድምፃቸዉን አጥፈተዉ ያደቡ ያዙ።

ከሕዝባዊ አብዮት በሕዋላ በተደረገ ምርጫ ሥልጣን የያዙት ዶክተር መሐመድ ሙርሲ ከዉስጥ፤- የሕዝባዊ አብዮቱን ድል ቀምተዉ ለራሳቸዉ ለማድረግ፤ በሕይልም፤ በምርጫም ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ያክል ሞክረዉ ያልተሳካላቸዉ የሙባራክ ታማኝ ጄንራሎች ጠላት ናቸዉ።በሕዝባዊ አብዮቱ ሥልጣን ለማግኘት ሞክረዉ ያልተሳካላቸዉ ሊብራል ወይም ለሐይማኖት ያልወገኑ የሚባሉ ሐይላት ጠላት ናቸዉ።

ከዉጪ ሙስሊም ወንድማማች ማሕበርን በሚፈሩት በእስራኤልና በምዕራባዉን መንግሥታት ዘንድ በጥርጣሬ የሚታዩ ናቸዉ።ሙባረክ ከሥልጣን ሲወገዱ« ነግ በኔ» ብለዉ ይርበተበቱ የነበሩት የአረብ ገዢዎች ቀንደኛ ጠላት ናቸዉ።የዉስጥ ጠላት፤ ተቃዋሚዎቻቸዉ ያልተኙላቸዉ፤ ምዕራባዉያን አማራጭ የሚፈልጉላቸዉ፤ ከራባት-እስከ ሪያድ የሚገኙ የአረብ ነገስታት በክፉ አይን የሚዩቸዉ ሙርሲ እሾሕ-አሜኬላ የተገጠገጠበትን የፖለቲካ መንገድ ለመጓዝ ግራ-ቀኝ ሲላጉ የሾሙ-የሸለሟቸዉ ጄኔራል ማንቁርታቸዉ ላይ ቆሙ።ሐምሌ 3 2013።መፈንቅለ-መንግሥት።

ከዉጪ ጠላት ጋር ተዋግተዉ አዋግተዉ አያዉቁም ብለናል-አይደል።ሙርሲ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በሙስሊም ወንድማማች ማሕበር፤ በአባላት ደጋፊዎቹ ፤ ለዲሞክራሲ፤ለሕዝብ፤መብት በቆሙ ግብፃዉያን ሁሉ ላይ አፋፋሙት። መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ በታንክ፤በሄሊኮፕተር፤ባነጣጥሮ ተካሽ ጦር ያሳጭዱት ገቡ።

ሺዎችን አስገደሉ።በግብፅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡትን ፕሬዝዳን ጨምሮ ብዙ ሺዎችን በየወሕኒ ቤቱ አጎሩ።የርዳታ ድርጅት፤ ተቋማትን፤ ነፃ መገናኛ ዘዴዎችን፤ አገዱ።ሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበርን በአሸባሪ ድርጅትነት ፈረጁ።ወነጀሉ።በቀደም ታላቁ እያሉ ያወደሱት ሕዝብ የወገኖቹ ሕይወት፤ ደም፤ አካል ገብሮ ለድል ያበቃዉን ሕዝባዊ አብዮት ገደሉት።

529 Todesurteile bei Massenprozess gegen Islamisten in Ägypten
ምስል AFP/Getty Images

ያን በአደባባይ ሰልፍ፤ አመፅ በወገኖቹ ሞት-እስራት የተሰቃየዉን፤ሥራ፤ገቢዉ የታጎለበትን ሕዝብ-አሸባሪ መጣብሕ አሉት።ካሸባሪ ጥቃት-አደጋ ብቸኛዉ አዳኝ እሳቸዉና እሳቸዉ ብቻ እንደሆኑ በሚቆጣጠሯቸዉ መገናኛ ዘዴዎች ያስፈራሩ፤ያሸማቅቁት ያዙ።ለድጋፍ አሰለፉ፤ አሳደሙትም።

የፕሬዳንት ሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ጥር 2011 ሲገረሰስ ያቺ ታሪካዊት ሐገር በደደረ ታሪኳ ላይ አዲስ ታሪክ አከለች።እስካለፈዉ ሳምንትም በጎ ይሁን መጥፎ አዳዳሲ ታሪክ አልተለያትም።ባለፈዉ ሳምንት ፊልድ ማርሻል አል ሲሲ ሌላ ታሪክ ከማከከላቸዉ በፊት ግብፅ በሁለት ቀን ችሎት ባንድ ቀን ፍርድ አምስት መቶ ሃያ-ዘጠኝ ሰዎችን በሞት በመቅጣት በአዲሱ-ዘመን የዓለም ታሪክ አዲስ ታሪክ አከለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሩፐርት ኮልቪሌ እንዳሉት በሁለት ቀን ችሎት የአምስት መቶ ዘጠና አይደለም ያንድ ሰዉን ጥፋት መመርመር እንኳን አይቻልም።

«ግብፅ ዉስጥ በሁለት ቀን ችሎት 529 ሰዎች በጅምላ በሞት የተቀጡበት ልዩ ፍርድ ሲበዛ አሳስቦናል።ብይኑ የተገቢ የፍርድ ሒደትን በርካታ መመዘኛዎች የጣሰ ነዉ።የዓለም አቀፍ ሕግንም በግልፅ የጣሰ ነዉ።ስዎችን እንዲሕ በጅምላ መቅጣት በርግጥ አስደንጋጭ ነዉ።በሁለት ቀን ሂደት የ529 ሰዎች አይደሉም የአንድ ሰዉም ተገቢዉን ፍርድ አያገኝም።»

ብቻ አል-ሲሲ ባለፈዉ ሐምሌ የገደሉትን የዴሞክራሲ ብልጭታ በመጪዉ ግንቦት-ወይም ሰኔ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ-ይቀብሩታል።ለሳቸዉና ለደጋፊዎቻቸዉ ግን-የሕልማቸዉ እዉንነት ይረጋገጣል።«ያሰብኩት ተሳካ፤ ያለምኩት ደረሰ» ነዉ ያለዉ ጥላሁን።እኔ ነጋሽ መሀመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ