1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን መንገድ 

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 28 2010

ሼክ መሐመድ አል-አሙዲን ጨምሮ የሳዑዲ አረቢያን ልዑላን፤ሚኒሥትሮች እና ባለወረቶች ዘብጥያ የወረወረው ውሳኔ ያስተላለፈውን የጸረ-ሙስና ኮሚሽን በበላይነት የሚመሩት ገና የ32 አመት ወጣት አልጋወራሽ ናቸው። የሥልጣን መሰላሉን በፍጥነት የተሸጋገሩት ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን የሚወስዷቸው እርምጃዎች ዓለም በቁራኛ እንዲያቸው አድርጓቸዋል።

https://p.dw.com/p/2nCcs
Saudi Arabien - Kronprinz Mohammed bin Salman
ምስል picture-alliance/abaca/Balkis Press

አልጋወራሹ

ገና የ12 አመት ልጅ ሳሉ አባታቸው የዛሬው የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱል አዚዝ አል-ሳዑድ እጃቸው ይዘው ለፍርድ ከሚሰየሙበት ሸንጎ የሚወስዷቸው ተወዳጅ ልጅ ነበሩ። የዛሬው የ32 አመት ጎረምሳ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ የአገራቸውን ኤኮኖሚ፤ ባሕል እና ሐይማኖት ሊያዘምኑ የቆረጡ የባለ ብዙ ውጥን ባለቤት ናቸው። አልጋወራሽነት ሲቀዳጁ ገና 31 አመታቸው ነበር። ከቀደመው አልጋወራሽ በ25 አመታት ያንሱ ነበር። 

ልዑሉ ከተማ ሊገነቡ፤ አገራቸውን ከነዳጅ ዘይት ጥገኝነት ሊያላቅቁ እና ሙስናን ሊያጠፉ ምለው ተገዝተዋል። 30 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ባሏት ሳዑዲ አረቢያ 70 በመቶው እድሚያቸው ከልዑል መሐመድ በታች ነው። የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኙ ሰባስቲያን ሰንስ እንደሚሉት በተለይ በወጣት ዜጎች ዘንድ ልዑሉ ድጋፍ አላቸው።

"በመጀመሪያ ደረጃ የወጣቱ ትውልድ ድጋፍ አላቸው። አብዛኛዎቹ ወጣቶች በልዑሉ ባለ ተስፋ ናቸው። እድሜያቸው በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። የእነርሱን ትውልድ ይወክላሉ። የሚናገሩት ነገር ግልፅ ከመሆኑም ባሻገር ራሳቸውን በግልፅ ይተቻሉ። አጓጊ እቅዶቻቸው የማኅበራዊ ለውጥ ተስፋ አሳድረዋል። ሰዎች ወደ ሥራ ገብተው አገራቸውን መለወጥ ይፈልጋሉ።"

Kronprinz Mohammed bin Salman
ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

ልዑሉ የመከላከያ ሚኒሥትር በነበሩበት ጊዜ ያስጀመሩትን የየመን ጦርነት በሁለት ወር ውስጥ አጠናቀው ድል ሊያውጁ ቃል ቢገቡም እንዳሰቡት አልቀናቸውም። ደሐዋ የመን ማባሪያ ወደታጣለት ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ስታሽቆለቁል የሚታደጋት ሳዑዲንም ተይ የሚላት አልተገኘም። በሳዑዲ አረቢያ ሁሉም ነገር እንደታቀደው እየሔደ አይደለም። የነዳጅ ዘይት ዋጋ በማሽቆልቆሉ ምክንያት የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት እየተንገዳደገደ ነው። ሰባስቲያን ሰንስ እንደሚሉት አልጋወራሹ ራሳቸውን የሳዑዲ አረቢያ መሲሕ ለማድረግ እየጣሩ ነው። 

"ሳዑዲ አረቢያ ማሻሻያ አድርጋ ልትዘምን ይገባል። ከነዳጅ ዘይት ጥገኝነት መላቀቅ ይኖርባታል። ለዚህም ጥሩ ምሥል ያሻታል። ከውጭ አገሮች ባለወረቶችን መሳብ አለባት። ለሥራ ምቹ መሆን ያሻታል። ይኸ ሥራ በመፍጠር ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል። በዓለም መድረክ ጥሩ ምሥል ለማግኘት በኤኮኖሚው፣ ባሕላዊው እና ሐይማኖታዊው መስክ እንደ የለውጥ መሪ አድርጎ ራስን ማቅረብ ያስፈልጋል። እንደምታስቡን ከዓለም አልተገለልንም፤ ወግ አጥባቂም አይደለንም ብሎ ለዓለም መንገር ያሻል።"

አገሪቱ በኳታር ላይ የሞከረችው ጫና ተፅዕኖው አናሳ ነው፤ አሊያም ፈፅሞ አልሰራም። ኢራን በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ አሁንም ስታሰፋ ይታያል።ተቺዎቻቸው ግብታዊ እርምጃዎቻቸው ቀጠናውን ሊያምስ በመግባባት የተገነባውን የሳዑዲ አረቢያ ንጉሳዊ ሥርዓት ሊያፈርስ ይችላል የሚል ሥጋት ተችኗቸዋል። ይኸ ወደ አልጋ ወራሽነታቸው ሲመጡ ቡራኬያቸውን የሰጧቸውን ምዕራባውያን ይጨምራል። 
የሳዑዲን አረቢያን ብሔራዊ ዘብ አዛዥ አስረው ሲሽሩ፤ ልዑላኑን ወደ ቅንጡም ቢሆን ማረፊያ ቤት ሲያጉዙ ዓለም ማጉረምረሙ አልቀረም። እስካሁን ያገራቸው ጋዜጦች እርምጃቸውን ሲያዳንቁ ተቺዎቻቸው መውቀሳቸው አልቀረም። ከፍ ያለ ተደማጭነት ካላቸው የአገራቸው የሀይማኖት ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ግን ጥንቃቄ ይሻል። 
"መሐመድ ቢን ሳልማን የሐይማኖት መምህራንን ላለማስቀየም ሚዛን መጠበቅ አለባቸው። ምክንያቱን አንዳንድ ውሳኔዎቻቸው አከራካሪ ናቸው። ቢሆንም እስካሁን ከሐይማኖት ልሒቃኑ ያን ያክል ጠንካራ ትችት አልገጠማቸውም። በዚሁ ለመቀጠል ሚዛኑን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።"

Russland - Kronprinz Mohammed bin Salman und Vladimir Putin
ምስል picture-alliance /ZUMAPRESS/P. Golovkin

በሙስና ላይ የከፈቱት ዘመቻ የምር የመሆኑ ጉዳይ ያጠራጠራቸው አልጠፉም። አባታቸው ሲሞቱ ንግሥናውን የመውረስ እድላቸው የሰፋ በመሆኑ አስቀድመው ተቀናቃኞቻቸውን ማስወገዳቸው እንዳይሆን የሚል መላምት አስከትሏል።አሜሪካዊው የጸጥታ ተንታኝ ብሩስ ሪድል የልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን አባት ቢሞቱ አሊያም በገዛ ፈቃዳቸው ዘውዳቸውን ቢያወርዱ የስልጣን ሽግግሩ ሰላማዊ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም።  ሪድል በአል ሞኒተር ጋዜጣ ላይ በፃፉት ሐተታ የሥልጣን ሽግግር ንትርኩ ንጉሱ እና ልጃቸው ካሰቡት በላይ ለመሆኑ የዘመቻ እስር ጠቋሚ ነው ሲሉ ፅፈዋል። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ