1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ምርጫና አንደምታው

ማክሰኞ፣ ግንቦት 7 2004

ከ 16 ቱ የጀርመን ፈደራል ክፍለ ግዛቶች አንዱ በሆነው በምዕራባዊው ኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚካሄድ ምርጫ ሁሌም ትኩረት እንደሳበ ነው ፤ የዚህም አንዱና ዋነኛው ምክንያት የምርጫው ውጤት በበርሊን መንግሥት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ነው ።

https://p.dw.com/p/14w6d
ምስል Reuters

ከ 16 ቱ የጀርመን ፈደራል ክፍለ ግዛቶች አንዱ በሆነው በምዕራባዊው ኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚካሄድ ምርጫ ሁሌም ትኩረት እንደሳበ ነው ፤ የዚህም አንዱና ዋነኛው ምክንያት የምርጫው ውጤት በበርሊን መንግሥት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ነው ። ከዚህ በመነሳትም መገናኛ ብዙሃን የእሁዱን ምርጫ ትንሹ ብሔራዊ ምርጫ እያሉ ነበር የሚጠሩት ። የብሔራዊውንና የፌደራል ክፍለ ሃገሩን ምርጫ ትስስር ለመግለፅም ኖርድ ራያን ቬስትፋለን ሳል ከጀመረው በርሊን ጉንፋን መያዟ አይቀርም የሚል አባባልም አለ ። ክፍለ ግዛቱ ከሌሎቹ የጀርመን ክፍለ ግዛቶች በህዝብ ብዛት የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል ። ከጀርመን ህዝብ የ1/5 ተኛው መኖሪያ በሆነው በዚህ ግዛት ፓርቲዎች የሚያገኙት ድምፅ በህዝብ እንደራሴዎችና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች በሚይዙት መቀመጫ ቁጥር ላይም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ። በነዚህ አብይ ምክንያቶችም ግንቦት 5 ፣ 2004 ዓ.ም የተካሄደው ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ውጤት በጉጉት ሲጠበቅ ነበር የቆየው ። በፌደራል ክፍለ ግዛቱ ከ 2 ዓመት በፊት በተካሄደ ምርጫ በግዛቱ ከዓመታት በኋላ አብላጫ ድምፅ ያገኘው የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ

NRW Wahl Röttgen
ምስል dapd

ከአረንጓዴዎቹ ጋር ተጣምሮ የመሰረተው ጥምር መንግሥት ለ 22 ወራት ካስተዳደረ በኋላ ነበር መንግሥት ፈርሶ ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ የተጠራው ። ይህን ያስከተለውም በፌደራዊ ክፍለ ሃገሩ ምክር ቤት SPD ና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ በጋራ  90 መቀመጫ ተቃዋሚዎቹ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ CDU ና የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ FDP እንዲሁም ግራዎቹ በአጠቃላይ 91 መቀመጫ ይዘው በነበሩበት የፌደራል ክፍለ ሃገሩ ምክር ቤት የግዛቱን በጀት ለማፅደቅ የሚያስችል በቂ ድምፅ ባለመገኘቱ ነው ። በዚህና በሌሎችም ሁኔታዎች የተቀዋሚዎችን ድምፅ ማግኘት ግድ ይሆንበት የነበረው የአናሳው መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የ SPD ዋ ሀነሎረ ክራፍት በጀት ማፀደቅ ባለመቻላቸው ፓርላማውን በትነው ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ለመጥራት ተገደዱ ። በዚሁ ባለፈው እሁድ በተካሄደው ምርጫም SPD የዛሪ 2 ዓመት ካገኘው ድል የላቀ አስተማማኝ ውጤት የላቀ ድል በማስመዝገብ በፌደራል ክፍለ ሃገሩ ተመራጭነቱን ዳግም አረጋግጧል ።በእሁድ ምርጫ SPD 39.1 በመቶ ድምፅ ነው ያገኘው ይህም ከ 2 ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ካገኘው 34.5 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ድል ሆኖ ተመዝግቧል ። በዚሁ መሠረት ፓርቲው በምክር ቤቱ የሚይዘው መቀመጫ ከ 80 ወደ 92 ከፍ  ብሏል ። በአሁኑ ምርጫ 11.8 በመቶ ድምፅ ያሸነፉት አርንጓዴዎቹም ከምክር ቤቱ 221 መቀመጫ

Landtagswahlen in Nordrhein-Westfalen Hannelore Kraft jubelt in Duesseldorf auf der Wahlparty der SPD
ምስል Reuters

28ቱን በማግኘታቸው ሁለቱ ፓርቲዎች እንደ ቀድሞው አናሳ ሳይሆን በምክርቤት አብላጫ ድምፅ ያለው መንግሥት ነው የሚመሰርቱት ። የ SPD ሊቀ መንበር ዚግማር ጋብርየል ፓርቲያቸውን ለድል የበቃው ለህዝብ ፋላጎት ትኩረት በመስጠቱ ነው ብለዋል

« SPD ና አረንጓዴዎች ትናንት እንዳሳዩት ምርጫዎችን በህብረት ማሸነፍ እንችላለን ። መራጩ ህዝብ በሚፈለገው ጉዳይ ላይ በርግጥ ካተኮረ ይህ የሚቻል መሆኑን የትናንት ማታው የፖለቲካ መልዕክት አስመስክሯል ። አንጌላ ሜርክልና CDU ና FDP  አብልጫ ድምፅ ክእንግዲህ የሚያገኙበት ተስፋ የላቸውም ። »

የጥምሩ መንግሥት አካል የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ CDU ደግሞ በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ምርጫ አይሸነፉ ሽንፈት ነው የደረሰበት ።  ከ SPD በተቃራኒው ቁልቁል ነው የወረደው ። ከ 2 ዓመት በፊት ካገኘው 34.6 በመቶ በ አንድ ሶስተኛ ያህል ቀንሶ 26,3  በመቶ ድምፅ ብቻ ነው ያገኘው ።  CDU በአሁኑ ምርጫ ያጋጠመው ሽንፈት እስከዛሬ በግዛቱ ደረሶበት የማያውቅ ነው ። ፔተር አልትማየር በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ ሊቀ መንበር ውጤቱ ከባድና መራር መሆኑን አልሸሸጉም ።

Deutschland Landtagswahlen NRW Reaktionen CDU Angela Merkel und Norbert Röttgen in Berlin
ምስል Reuters

« በምርጫው የተገኘው ውጤት ለኛ ብርቱ ምት ነው ። በተለይም ለደጋፊዎቻችንና መራጮቻችን መራር ተመክሮ ነው ። »

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ሽንፈቱ ተመሳሳይ ስሜት እንዳሳደረባቸው ገልፀው በርሳቸው ግንባር ቀደም መሪነት በሚያራምዱት የቁጠባ መርህ ላይ ከተቀናቃኛቸው SPD ጋር እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል ።

«መራርእናየሚያምከባድየሽንፈትእለትነዉ።  የፋይናንስቁጠባእቅድናሰነድንበተመለከተተባብሮለመስራትናለመወሰንከሶሻልዴሞክራቶችናከተቃዋሚፓርቲዎችጋእነጋገርበታለሁ።

ለሽንፈቱ ተጠያቂ የተባሉት ከ SPDዋ ሀነሎረ ክራፍት ጋር ፓርቲያቸውን ወክለው ለውድድር የቀረቡት በግዛቱ የCDU መሪ  Norbert Rottgen ናቸው ። የፌደራል መንግሥቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሮትገን መራጩን ህዝብ መድረስ አለመቻላቸው አንዱ ድክመታቸው ተደርጎ ተወስዷል ። ሮትገን በምርጫ ዘመቻው መነሻ ላይ በምርጫው ቢሸነፉ ከበርሊን ፓርቲያቸውን ወደሚመሩበት ግዛት ወደ ኖርድራይን ቬስት ፋለን ለመዛወር አለመፈለጋቸውን አስቀድመው መናገራቸው  የመራጭ ቁጥር ለማነሱ ምክንያት ሆኖ ተወሰዷል ። ሮትገን ከአሰደንጋጩ ፣ ርሳቸው መራር ካሉት ሽንፈት በኋላ ወዲያውኑ ከፓርቲያቸው ሃላፊነት እንደሚነሱ ነበር ያሳወቁት ። 

« ሽንፈቱ መራር ነው ። በጣም የሚያሳምም ሽንፈት መሆኑ ግልፅ ነው ። ይሄ ውጤት   የፌደራል ክፍለ ሃገሩን የክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ መሪነት እንድለቅ የሚያስገድድ ነው ። »

Hannelore Kraft NRW Wahlkampf Wahlen
ምስል Reuters

CDU ያገኘው ድምፅ በቀደመው ምርጫ ከተሰጠው እጅግ ማነሱ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት ፓርቲው እጎአ በ2013 ቱ ብሔራዊ  ምርጫ ተሰፋ የሚያደርገውን ድል ከወዲሁ ያደበዘዘ መስሎ ታይቷል ። በተለይም ደግሞ አንጌላ ሜርክል ለ 3 ተኛ ጊዜ ለመራሂተ መንግሥትነት ተወዳድረው ማሸነፋቸውንም እንዲሁ አጠያያቂ ያደርጋል የሚሉም አሉ ። የአሁኑን ሽንፈትም ከሜርክል መርህ ተቀባይነት ማጣት ጋር የሚያያዙም አልጠፉም ሆኖም የሜርክል ፓርቲ አባላት በዚህ አይስማሙም ከነዚህም አንዱ ሊበር ክኔሽት የቱሪንገን ፈደራል ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ።

« አንጌላ ሜርክል የኛ መራሂተ መንግሥት ናቸው በፌደራል ደረጃ የኛ ሊቀመንበር ናቸው በኔ አመለካከት ምንም በዚህ ጉዳይ ላይ ያሳረፉት የተዛባ ነገር የለም ። »

የአጠቃላዩ ምርጫ መፈተኛ ተደርጎ የሚወሰደው የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ምርጫ ውጤት የ SPD ፓለቲከኞች የተቀናቃኛቸውን የCDU ን የፖለቲካ መርህ ለማብጠልጠል ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸው ነበር ። የ SPD ሊቀመንበር ዚግማር ገብርየለ ውጤቱ የሚያሳየው የ CDU የፖለቲካ መርህ ከህዝብ ፍላጎት ጋር ያለመጣጣሙን ነው ይላሉ ።

« CDU  በተከታታይ ለ11 ኛ ጊዜ ከ FDP ጋር ጥምረት ለመፍጠር አብላጫ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሁሉ አልተሳካለትም ። ይሄም በፖለቲከኞቹ ስብእንና ምክንያት ብቻ ሳይሆን የሚያራምዱት የፖለቲካ መርህ ከህዝቡ ፍላጎት ፍፁም የራቀ መሆኑ ነው ። »

NRW Wahl Lindner
ምስል dapd

በአንዳንዶች አስተያየት ደገሞ የኖርድራይን ቬስትፋለኑ ድል በግልፅ የ SPD ዋ ፖለቲከኛ የሃነሎረ ክራፍት ብቻ ነው ይላሉ ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት የርሳቸውን ስብዕናና በህዝብ ዘንድ ማሳደር የቻሉትን አመኔታ ነው ። በዚህ ምርጫ ሌላው ግልፅ ሆኖ የወጣው የሜርክል ፓርቲ ሊሸነፍ የሚችል መሆኑ ነው ። ይህም ከ 2 ዓመት በፊት ይካሄዱ በነበሩ ምርጫዎች ተከታታይ ሽንፈቶች ለደረሱበት SPD በራስ የመተማመን መንፈሱ እንዲጠናከር ረድቷል ። በአሁኑ ምርጫ እንደ SPD ም ባይሆን የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ FDP በክፍለ ሃገሩ መጠነኛ ድል ማስመዝገቡ ከዚህ ቀደም ተዳፍኗል የተባለውን እድሉን አለምልሟል ። ከ 2 ወር በፊት ምርጫ ሲጠራ በቂ ድምፅ አግኝቶ ምክር ቤት መግባቱ እንኳን አጠራጣሪ የነበረው የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ በዚህ ምርጫ ያስመዘገበው ውጤት አባላቱን አነቃቅቷል በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፓርቲው ተፎካካሪ አድርጎ ያቀረባቸው ወጣቱ ክርስቲያን ሊንድለር ከዚህ ቀደም እንዳሉት የተሻለ ውጤት ማግኘት ችለዋል ። FDP በአሁኑ ምርጫ 8,6 በመቶ ድምፅ አሸንፏል ይህም ፓርቲው ከሁለት ዓመት በፊት ካገኘው ድምፅ ከፍ ያለ ነው ። ሊንድለር ውጤቱን አጥጋቢ ለደጋፊዎችችን ደግሞ አስደሳች ነው ያሉት 

NRW Wahl Kraft
ምስል dapd

« ይሄ ውጤት በኖርድ ቭስት ፋለን ለሚገኘው FDP የምርጫው ውጤት አጥጋቢ ነው በዚህም ከኛ ጋር የታገሉትን እኛንም የደገፉት ሁሉ በርግጥ ሊደሰቱ ይችላሉ »

የFDP ሊቀ መንበር ፊሊፕ ሮሰለርም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት ። 

«ለኛ በኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ለምንገኝ ነፃ ዲሞክራቶች  ብቻ ሳይሆን በመላው ጀርመን ለሚገኙ አባላቱ ዛሬ ዛሬ ለኛ እፁብ ድንቅ ምሽት ነው »

ራይነር ብሩደርለ በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት የ FDP ሊቀ መንበር በኖርድ ራይን ቬስትፋለኑ ምርጫ ከተገኘው ውጤት በመነሳት FDP  ም ሆነ CDU ለመጪው ምርጫ በህብረት ጠንክረው እንደሚሰሩ ነው ያሳወቁት

« በምዕራቡ ዓለም እንደ ጀርመን በተሻለ ደረጃ የሚገኝ የለም ። ይሄ የሚያሳየው የተሳካ እድል ያጋጠመን መሆናችንን ነው ። እህትማማቾች ፓርቲዎችና እና ነፃ ዲሞክራቶች አንድ ላይ ጠንክረን ለችግሮች መፍትሄ ለመሻት እንንቀሳቀሳለን ፓርቲዎቹ ከኛ ጋር ጠንክረው ለችግሮች መፍትሄ ለመሻት ይንቀሳቀሳሉ ። የአብዛኛው የጀርመን ህዝብ ድምፅ ለማግኘት ይህን ነው ማሳካት ያለብን እነዚህ ናቸው ለ 2013 ቅድመ ግዴታዎቹ »

የ CDU ው  ፔተር አልትማየርም ከአሁን ወዲያ የምንከተለው መርህ የሚበጅ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።

« በአጠቃላይ በፌደራል ደረጃ ስህተት መፈፀም አይኖርብንም በቅድሚያ ማራመድ ያለብን የፖለቲካ ምርህ ለአንድ ፌደራል ክፍለ ሃገር የሚበጀውን ነው መሆን ያለበት »

ብዙዎች የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ምርጫ ውጤት በመጪው አጠቃላይ ሃገር ዓቀፍ ምርጫ ላይ ተፅኖ በማሳደሩ ቢስማሙም ለመራሂተ ወይም መራሄ መንግስትነት የሚያበቃው የተወዳዳሪው ስብዕና በመሆኑም ያምናሉ ። ሃነሎረ ክርፍትን ለድል ያበቃቸው ስብዕናቸው እንደሆነ የሚናገሩት አስተያያት ሰጪዎች ሜርክልን ሊወዳደሩ የሚችሉ እጩ ሊሆኑ ይችላሉ እያሉ ነው ። ክራፍት ግን ቦታዮ እዚያ ሳይሆን በተመረጥኩበት በኖርድራይን ቬስትፋለነ ነው ብለዋል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ