1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት

ረቡዕ፣ መጋቢት 17 2006

የአሸባሪዎች ጥቃት፣ የሐይማኖት ግጭት እና ሙስና ባልተለያት ናይጄሪያ በኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሆነች ነው የሚነገረው። ይህ እዕን ከሆነ ደግሞ በነዳጅ ዘይት ሀብታም የሆነችው ናይጄሪያ በቅርቡ በኢኮኖሚ እድገቷ ከአፍሪቃ አንደኛ ከሆነችው ደቡብ አፍሪቃ መቅደሟ አይቀሬ ነው።

https://p.dw.com/p/1BVgw
Karte Nigeria

የምጣኔ ሀብት ምሁር ራዚያ ካን በቅርቡ ባወጡት ጥናት እንዳሉት ከሆነ በያዝነው በጎርጎሮሲያውያኑ 2014 ዓ ም በናይጄሪያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ይመዘገባል። « የናይጄሪያ ብሔራዊ ያልተጣራ ገቢ ( ጂዲፒ) በሚገመገምበት ጊዜ ናይጄሪያ ትልቅ እና ወሳኝ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ሆና ልትታይ ትችል ይሆናል። ግን የግምገማው ሂደት ምን ያህል እንደሚሆን በአሁኑ ሰዓት የኢኮኖሚ ምሁራንን እያከራከረ ነው። »

ራዚያ ካን የሚያደርጉት ቅድመ ትንበያ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። ታዋቂዋ የምጣኔ ሀብት ምሁር በብሪታንያ ስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ ናቸው። ወይዘርዋ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚፈልጉ ደንበኞችን ይመክራሉ። « አዎ! በእርግጠኝነት። ናይጄሪያ ውስጥ ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው ብለን ያነሳናቸው ነጥቦች ከናይጄሪያ ፈቅ የሚያስብሉ አይደሉም።»

ይሁንና ካን አያይዘው የሚያስጠነቅቁት ነገር አለ። የመረጃ መዘርዝሮች ወጥ አለመሆንን ያነሳሉ። የናይጄሪያ ብሔራዊ ያልተጣራ ገቢ በእንግሊዘኛ ምህጓሩ ( ጂዲፒ) ለመጨረሻ ጊዜ ከተሰላ 24 ዓመታት ተቆጥረዋል ባይ ናቸው። ሌሎች ሀገራት በየ5 ዓመቱ አጠቃላይ ምርታቸውን እንደ አዲስ ያሰላሉ። የናይጄሪያ የምጣኔ ሀብት መዋቅር ባለፉት አመታት መቀየሩ የማያጠራጥር ነው። የቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፉን እንኳን የተመለከትን እንደሆነ የዛሬ 24 ዓመት ከነበረው ጋር አይመሳሰልም። የናይጄሪያ ጂዲፒ እንደ አዲስ ቢሰላ ናይጄሪያ በኢኮኖሚ እስካሁን ከተገመተው በላይ እድገት እንዳስመዘገበች አያጠራጥርም። እንደ የዓለም ባንክ ከሆነ የናይጄሪያ ብሔራዊ ያልተጣራ ገቢ እጎአ በ2012 ዓም 262 ቢሊዮን ዩ ኤስ ዶላር የነበረ ሲሆን የኢኮኖሚ እድገቱ ደግሞ በ2013 ዓም 6,7 ከመቶ ነበር። ቀደም ሲል ባለው ስሌት መሰረት ደቡብ አፍሪቃ በኢኮሞኒ የአህጉሩ ጠንካራዋ እና የመጀመሪያዋ ሀገር ናት። አሁን ግን እንደ ባለሙያዎቹ ከደቡብ ወደ ምዕራፍ አፍሪቃዊቷ ሀገር መሻገር ሳይኖርብን አይቀርም።

Flüchtlingsfamilie aus Nigeria bei Diffa Niger
ምስል DW/Larwana Malam Hami

ለመሆኑ ከቁጥሮቹ በስተ ጀርባ ምንድን ነው ያለው? ሚሻኤል ሞነርያን «አፍሪቃ- የጀርመን ኢኮኖሚ በተሰኘ ማህበር ውስጥ የአፍሪቃን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሂደት ይመለከታሉ። « ቁጥሩን ብቻ የምንመለከት ከሆነ በቂ አይደለም። በተለይ እንደ ናይጄሪያ ያለች ሀገር፣ 90 ከመቶ የውጭ ገቢዋ በነዳጅ ዘይት ሽያጭ ላይ የተመረኮዘ ነው። በቀጥታ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ለማነፃፀር ያዳግታል። ያም ማለት ምንም እንኳን አጠቃላይ አመታዊ ምርቷ ቢቀራረብ እንኳን የኢኮኖሚያቸው መዋቅር ይለያያል። ናይጄሪያ የነዳጅ ምርት እና ሽያጭ ላይ ታተኩራለች። አዎ ! በግንባታ ላይም ናይጄሪያ ውስጥ ባለፉት ጊዜያት ትልቅ ለውጥ ታይቷል፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ገበያ እና ግብርናውም ተሻሽሏል። ቢሆንም ግን ደቡብ አፍሪቃ በነዚህ ረገድ ገፍታ የሄደች እና የበለፀገች ናት። የራሷ የሆነ የመኪና ፋብሪካ አላት። ማሽኖች ያመርታሉ። ኬሚካል ንጥረ ነገሮች ሳይቀሩ በደቡብ አፍሪቃ ይመረታሉ።»

ናይጄሪያ በአንፃሩ ነዳጅ ዘይት አላት። ሀገሪቷ ከዓለም የነዳጅ ዘይት ከሚሸጡ ሀገራት በ8ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይሁንና የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት በውጭ ሀገር ገበያ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ መሆኑ ሀገሪቷን በአንድ እግሯ ብቻ እንድትቆም አድርጓታል። የዓለም የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ ተለዋዋጭ ነው። ናይጄሪያ ደግሞ ድፍድፍ ዘይቱን ሙሉ በሙሉ አጣርታ ለውጭ ገበያ አታቀርብም። ይህም የሽያጩን ዋጋ ይቀንሰዋል። ምንም እንኳን በሀገሪቱ የተንቀሳቃሽ ስልክ ሽያጭና ግንባታው ቢጨምር እና የ« ኖሊውድ» የፊልም ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በርካታ ተመልካቾችን ቢያተርፍም ካን እንደሚሉት ለሀገሪቷ ወሳኝ የሆኑትን ምርት እና የነዋሪውን ግብይት በተመለከተ ጥያቄ የሚያስነሱ ነገሮች አሉ።« የናይጄሪያ ማህበረሰብ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ሲነፃፀር በ3 እጥፍ እንደሚበልጥ እናውቃለን። ታድያ እንዴት ነው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን ምርቶች ማመሳከር የሚቻለው? ምን ያህል የችርቻሮ ንግድ አለ? ይህ ከሌሎች የኢኮኖሚ እድገቶች ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል? እነዚህ የ ምጣኔ ሀብት ይዞታን የሚጠቁሙና የምናያቸው ምልክቶች ናቸው ። »

ናይጄሪያ ባለሀብቶችን የሚያሳምን አቅም አላት። በ168 ሚሊዮን ነዋሪቆቿ ናይጄሪያ ከአለም 7ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ድምሩ ቀላል ነው። ብዙ ሰው የሚኖርበት፣ ብዙ አማራጮች አሉ። ብዙ አማራጮች ደግሞ ካሉ ብዙ እድገት ይፈጥራሉ። ይሁንና ይህ ድምር እንዲስተካከል ደግሞ የሚያመርቱ እና የሚሸምቱ መኖራቸው ብቻ የተስተካከለ ኢኮኖሚ እንዲኖር በቂ አይደሉም ይላሉ ካን። ምንም እንኳን አሁን ናይጄሪያ ከአፍሪቃ በኢኮኖሚ የመጀመሪያዋ ሀገር ልትሆን ብትችልም ፤ 63 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧ በድህነት ስር ነው የሚኖረው።

Nigeria - Oloibiri Öl-Quelle
ምስል DW/ Haussa

« የናይጄሪያ ህዝብ ከአንድ ዶላር ባነሰ ገንዘብ በቀን እንደሚኖር እናውቃለን። እና በነሱ እና አማካይ ገቢ ባላቸው ናይጄሪያውያን መካከል ያለው የገቢ ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ ነው የሚሄደው።» ምንም እንኳን የናይጄሪያ ኢኮኖሚ ከፍ ቢልም እያንዳንዱ ሰው ኪስ የሚቀረው ገንዘብ ትንሽ ነው። መካከለኛ ገቢ ያላቸው ናይጄሪያውያን ቁጥር እያደገ አይደለም። በአሁኑ ሰዓት አትራፊ የሆኑት ጥቂት መካከለኛ ገቢ የነበራቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። ከአፍሪቃ ማህበር ሚሻኤል ሞነርያንም በዚህ ይስማማሉ።« በናይጄሪያ የምጣኔ ሀብት ላይ የሚሰነዘረው ትችት እድገቱ ለመላው ማህበረሰብ አለመድረሱ ላይ ነው።በተለይ ደግሞ በሰሜኑ ክፍል።»

እርግጥ ነው። የናይጄሪያ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኮ ሐራም ታጣቂዎች በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ በተደጋጋሚ በሰዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል፣ ንብረቶችን ወድመዋል። ሁኔታው ለናይጄሪያ ጦር እና ፖሊስ ፈታኝ ሆኗል። እስካሁን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።እጎ አ በግንቦት ወር 2013 የሀገሪቱ መንግሥት ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን ካስታወቀ በኃላ ወደ 300 000 የሚጠጉ ሰዎች ከቦርኖ፣ አዳማዋ እና ዮቤ ወደ ሌላ የሀገሪቱ ከተሞች ሸሽተዋል።

በተለይ በናይጄሪያ ትላልቅ ከተሞች የስደተኞች ፍልሰት መብዛት አስጊ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው ይላሉ፤ በናይጄሪያ -አቡጃ የሚገኘው የኮንራድ አደናወር የጀርመን ተቋም ኃላፊ ሂልደግራድ ኪጎዚ።«በነዚህ አካባቢዎች የሚታየውን አሉታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይበልጥ ያባብሰዋል። ስደተኞች ብዙ ሕዝብ ወደሚኖርባቸው እና ለራሱ እንኳን ስራ ወደአጣባቸው ከተሞች ሲመጡበት ፤ በበጎ አይቀበላቸውም። ይህም ውጥረቱን ያከረዋል። ስርቆት እና አነስተኛ ወንጀሎችም ይበራከታል። ዝርፊያ እና ግድያንም ያስከትላል።»

አሚና አልሀጂ አሊ ከተሰደደች ከሁለት ቀን በኋላ የወለደችው ልጇን ታቅፋለች። የ23 አመቷ ወጣት ህይወታቸው እንዴት እንደሚቀጥል ምንም የምታውቀው ነገር የለም።« የት እንደምንኖር ብዙም አያሳስበኝም። ዋናው ነገር ልጄ ብቻ በሰላም ይደግልኝ ። ትላለች ወጣቷ እናት። ስደተኞቹ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ያላቸውን ንብረት ጥለው ነው የተሰደዱት። ብዙዎች ግራ የተጋቡ እና ፍርሃት ያስጨነቃቸው ናቸው። ቲጃኒ ሁሴይን በሚኖሩበት መንደር አቅራቢያ ባለ መንደር ውስጥ ቦኮ ሀራም 43 ተማሪዎችን በተኙበት እንደገደለ ይናገራሉ።

« በተደጋጋሚ በሚደርሰው ጥቃት ሳቢያ ሰዎች በፍርሃት ነው የሚኖሩት። ምንም ሰላም የላቸውም። ሽብር መቼ በርህን እንደሚያንኳኳ አታውቅም።የናይጄሪያ ኢኮኖሚ እነዚህ አሳሳቢ ችግሮች ሁሉ እያሉበት እንዲህ ማደግ ከቻለ ያን ያህል የአሸባሪነት ችግር የሌላት ደቡብ አፍሪቃ ኢኮኖሚ ለምን እየቀነሰ እንደሆነ ይነገራል? ሞነርያን እንደሚሉት ግን የደቡብ አፍሪቃ ኢኮኖሚ ባለበት ነው የቆመው እንጂ አልቀነሰም። ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠሩት አንደኛው ምክንያት ገዢው የአፍሪቃ ብሔራዊ ሸንጎ በምህፃሩ ( ኤ ኤን ሲ) እንደሆነ እና ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በኃይል ምንጭ በኩል የሚደረገው ግንባታ ነው።

« የመብራት ኃይል ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በጣም ርካሽ ነበር። ለአስርተ ዓመታት በዚህ ዘርፍ ምንም ያህል ወጪ አልተደረገም ነበር። አሁን ግን ለግንባታው ብዙ ገንዘብ መውጣት አለበት። ይህ ከሆነ ደግሞ ኃላ ላይ የመብራት ዋጋ ይጨምራል። ስለዚህ ቦታው ውድ ቦታ ነው። አፍሪቃ ውስጥ እንደ አዲስ ለመጀመር የሚፈልግ በቀጥታ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትን መመልከት ይጀምራል።» እንደ ካን ሁሉ ሞነርያንም ባለሀብቶች ናይጄሪያን አልፈው የሚሄዱበት መንገድ የለም ይላሉ። ይሁንና ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ሲነፃፀር መዋለ ንዋይ አፍሳሾቹ ትልቅ ኪሳራ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ መዘንጋት የለባቸውም።

ሽተፈኒ ዱክሽታይን

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ