1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ የኒሱ አደጋና ዉግዘቱ

ዓርብ፣ ሐምሌ 8 2008

በፈረንሳይዋ የባህር ዳርቻ ግዛት ኒስ ትናንት በደረሰዉ አደጋ 84 ሰዎች መገደላቸዉ ቢገለጽም የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ተጎድተዉ ሀኪም ቤት ከገቡት 50ዎቹ በሕይወት እና ሞት መካከል እንደሚገኙ ዛሬ አስታወቁ። ከሟቾቹ መካከልም የዉጭ ዜጎችም እንደሚገኙበት ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/1JPgV
Frankreich Anschlag Lastwagen-Attacke in Nizza
ምስል Getty Images/AFP/V. Hache

[No title]

የሀገሪቱ ብሔራዊ በዓል በተከበረበት በትናንትዉ ዕለት ምሽት በኒስ ከተማ ባህር ዳርቻ የርችት ተኩስ ለመመልከት በተሰበሰበ ሕዝብ መካከል በፍጥነት የሚሄድ ከባድ የጭነት መኪና ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። አሽከርካሪዉ ወዲያዉ በፈረንሳይ የፀጥታ ኃይሎች ጥይት የተገደለ ሲሆን እስካሁን ለደረሰዉ አደጋ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ የደረሰዉ የሽብር አደጋ ነዉ ሲሉ፤ የአዉሮጳን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች ዘግናኝ ጥቃት መሆኑን በመጥቀስ በሽብርተኝነት ላይ የተከፈተዉን ዘመቻ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አስታዉቀዋል። የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዣን ክላዉድ ዩንከር እንዲህ ያለዉ አረመኔያዊ ጥቃት መቼ ነዉ የሚያበቃዉ ሲሉ ጠይቀዋል።

«በምሽት የኒስ ከተማ ዉስጥ የደረሰዉ አረመኔያዊ የሽብር ጥቃት ከመጠን በላይ አስደንግጦኛል፤ አሳዝኖኛል ነክቶኛልም። በድጋሚ ሕይወት ጠፍቷል፤ ሕልም ተሰናክሏል፤ የበርካቶች ታሪክ ወድሟል። እናም ይህ መቼ ያበቃ ስንል ልንጠይቅ እንገደዳለን፤ ከኒስ ዜጎች ጎን ነን በርካታ አዉሮጳዉያን ኑሯቸዉን ለመኖር ወደዚያ ይሄዳሉ። ከፈረንሳዉያን ጎን በትብብር መቆማችን ይቀጥላል። ፈረንሳይ እና ሪፐብሊኳ ለዘለዓለም ይኑሩ።»

Frankreich Trauer im Élysée-Palast nach dem Anschlag in Nizza
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Camus

የፈረንሳይ መንግሥት ከነገ ጀምሮ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አዉጇል። ፓሪስ ከተማ ላይ ባለፈዉ ከደረሰዉ የሽብር ጥቃት ወዲህ እስከመጪዉ ሐምሌ 19 ድረስ በሀገሪቱ ታዉጆ የነበረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም መራዘሙን ፕሬዝደንት ኦሎንድ ዛሬ አስታዉቀዋል።

«እስከመጪዉ ሐምሌ 19 የሚቆየዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ ሦስት ወራት እንዲራዘም ወስኛለሁ። ረቂቅ አዋጁ በመጪዉ ሳምንት ለምክር ቤት ይቀርባል። ሽብርን ለመዋጋት ካለን ፈቃድ ሊያግደን የሚችል ነገር አይኖርም። እንደዉም ሶርያ ላይም እንደኢራቅ ሁሉ የምንወስደዉን ርምጃ እናጠናክራለን። እናም በገዛ መሬታችን ላይ ጥቃት ያደረሱብንን የእነሱን አካባቢ ለይተን መደብደባችንን እንቀጥላለን።»

ትናንት ፈረንሳይ ዉስጥ ከደረሰዉ የጥቃት አደጋ በኋላ ጣሊያን እና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት የድንበር ላይ ጥበቃቸዉን አጠናከረዋል።

ደቡባዊ ፈረንሳይ ኒስ ውስጥ ለትናንቱ የፈረንሳይ ብሔራዊ በዓል የሚተኮስ ርችት ለማየት በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በተፈፀመው ግድያ ዓለም ኃዘኑን እየገለፀ ነው። የዓለም መሪዎች በአደጋው የተሰማቸውን ኃዘን እና ቁጭታቸውን ከመግለጽ በተጨማሪ ከፈረንሳይ ጎን መቆማቸውን እያሳወቁ ነው። በአደጋው የተለያዩ ሃገራት ዜጎች መገደላቸው ተዘግቧል። ትናንት ማታ ነበር አንድ ተጠርጣሪ ቱኒዝያዊ፤ በፍጥነት ያሽከረክር በነበረው ከባድ የጭነት መኪና ለበዓሉ የሚተኮሰውን ርችት ለማየት የተሰበሰበውን ሕዝብ በመግጨት ቢያንስ ከ84 ሰዎች በላይ የገደለው። በአደጋው በርካቶች ቆስለዋል። አሽከርካሪው በፖሊሶች በተደጋጋሚ ተተኩሶበት እስኪገደል ድረስ ሰዉ ሰዎችን እየገጨ ሁለት ኪሎሜትር ያህል መጓዙ ተዘግቧል። የፈረንሳዩ መንግሥት ከነገ ጀምሮ የሦስት ቀናት ሃዘን አውጇል። ስለ አደጋው እና ከአደጋው በኋላ በመወስድ ላይ ስላሉት እርምጃዎች የፓሪሷን ዘጋቢያችንን ሃይማኖት ጥሩነህን በስልክ አነጋግሬያታለሁ።

Ukraine Poroschenko legt Blumen vor der französischen Botschaft in Kiew nieder
ምስል Reuters/G. Garanich

ሃይማኖት ጥሩነህ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ