1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና የኦሊምፒክ መሰናዶና በዓለም ዙሪያ የቲቤት ጉዳይ ያስከተለው ንትርክ፧

ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2000

የምዕራብ አውሮፓን ያህል ስፋት ያላት ቲቤት፧ በቻይና ቁጥጥር ሥር ከዋለች አያሌ ዐሠርተ-ዓመታት አሥቆጥሯል። ሆኖም፧ ህንድ ውስጥ፧ በስደት የሚገኘው የቲቤት መንግሥትም ሆነ የኖቤል ሰላም ተሸላሚው ዳላይ ላማ ለህዝባቸው መብት፧ ባህልና ሃይማኖት መጠበቅ፧ በሚያደርጉት እንቅሥቃሴ ሳቢያ፧ የቲቤት ጉዳይ የተዳፈነ አልመሰለም። ጉዳዩ

https://p.dw.com/p/E86y
ቲቤታውያን በሎዛን፧ እስዊትስዘርላንድ የቻይናን መንግሥት የኃይል እርምጃ በመቃወም ያሳዩት ትርዒት፧
ቲቤታውያን በሎዛን፧ እስዊትስዘርላንድ የቻይናን መንግሥት የኃይል እርምጃ በመቃወም ያሳዩት ትርዒት፧ምስል AP
የፖለቲካውንና የእስፖርቱን ዘርፍም ማነጋገሩ አልቀረም።
በቅርቡ የቲቤት የቡድሃ ሃይማኖት ተከታይ መነኮሳት ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ፧ ለመበታተን፧ ቻይና የኃይል እርምጃ በመውሰዷ ዓለም አቀፍ ቅሬታን ከመፍጠር ባሻገር፧ በራሷ ላይ ብርቱ ነቀፌታና ውግዘት ጭምር እንዲፈራረቅባት ነው ያደረገው። ወደ ቤይጂንግ ኦሊምፒክ የመጓዝ እቅድን መሠረዝ ይገባል የሚሉም አልታጡም። ዓለም-አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፧ ቻይናን በምታዘጋጀው የኦሊምፒክ እስፖርት ውድድር አለመሳተፍ ነው የሚሉትን ወገኖች ሐሳብ ይቃወማል። ይሁንና፧ የዓለም እስፖርተኞች፧ የሰብአዊ መብት ይዞታ በተሻሻለበት እንጂ በሚያስፈራባት ሀገር መገኘቱ አያዝናናቸውምና ቻይና ይህን ጭምር ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርባት መምከሩ አልቀረም። የኦሊምፒክ ገጽና መንፈስ እንዳይበላሽ መጠንቀቅም ይገባል ነው ያለው።
ትናንት በኦሊምፒያ፧ ግሪክ የተቀጣጠለውና ነሐሴ ሁለት ቀን ቤይጂንግ ላይ የኦሊምፒክ እስፖርት መጀመሩን የሚያበሥረው ችቦ፧ በተለኮሰበት ሥነ-ሥርዓት፧ ቻይና ተቃውሞ የታየበትን ሁኔታ ያወገዘችበትን ድርጊት፧ እንዲሁም በቲቤት የወሰደችውን እርምጃ መንስዔ በማድረግ፧ የሉክሰምቡርግ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር፧ Jean Asselborn ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዲህ ብለዋል።
«ቤይጂንግ፧ ባለፈው ምዕተ-ዓመት በተሠራበት መንገድ መጓዟን ማቆም ይጠበቅባታል። ሳንሱር ማድረግ፧ ማጣጣል ማጥፋትም ሆነ መደብደብ፧ ዳላይ ላማንም ሰይጣን አስመስሎ ማቅረብ፧ መቆም ያለበት፧ ጊዜ ያለፈበት ዋጋ-ቢስ የአሠራር ዘዴ ነው። የአውሮፓው ኅብረት፧ ቻይና ትክክለኛውን ለዓለም እንድታስረዳ በግልጽ ማሳወቅ አለበት። የተባባሩት መንግሥታት ምርመራ መካሄድ ይኖርበታል። በቲቤት፧ ሰዎች ባህላቸውን የመጠበቅ መብታቸው ሊከበር ይጋባል። ላሠምርበት የምፈልገው፧...በህግ በምትተዳደረው ቻይና ይህ መቻል እንዳለበት ነው።«
ቲቤት እ ጎ አ በ 1950 ዓ ም በቻይና ህዝባዊ ጦር ከተወረረች በኋላ የቲቤት ውዝግብ መፍትኄ እንዲገኝለት ዳላይ ላማ፧ ከያኔው የቻይና ኮሙዩኒስት መሪ ማዖ ዜዶንግ ጋር በተደጋጋሚ በመነጋገር ጥረት አድርገው ነበር። ይሁንና ድርድሩ መፍትኄ ሳያስገኝ ቀርቶ በዘጠንኛው ዓመት፧ በመዲናይቱ በላሳ፧ ህዝቡ ከቻይና የጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ ተቃውሞውን አደባባይ ውጥቶ ሲያሳይ፧ በጦር ሠራዊቱ ደም-አፋሳሽ እርምጃ ተገታ። ዳላይ ላማ፧ በኀዘን ወደ ህንድ ተሰደዱ። ይሁንና ህዝባቸው በነጻነት መብቱ ተከብሮለት እንዲኖር ያላሰለሰ ጥረት ከማድረግ የቦዘኑበት ጊዜ የለም።
«በውጭ የሚኖሩ ቲቤቶች ብቻ ሳይሆኑ፧ በሀገር ውስጥ የሚገኙትም ሆኑ ጠቅላላው ህዝብ፧ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ፧ ለመሠረታዊ መብቱ ሽንጡን ገትሮ መታገል ይኖርበታል። በመሠረቱ፧ እኛ የምንፈልገው መገንጠል ወይም ነጻነት ማወጅ ሳይሆን፧ ሰፋ ያለ የውስጥ አስተዳደር መብት ማግኘትን ነው።«
እኒህ የቲቤታውያን መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማ፧ በቻይና መንግሥት ገንጣይ እየተባሉ ነው የሚወገዙት። በሌላው የዓለም ክፍል ግን የተወደዱና የተከበሩ ሰው ናቸው። የሰላም መልእክተኛ መሆናቸውም ነው የሚነገርላቸው። እ ጎ አ በ 1989 ዓ ም፧ የኖቤል ሰላም ሽልማት ያገኙት ዳላይ ላማ፧ የአገራቸው የቲቤት ችግር፧ በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ መፍትኄ እንዲያገኝ ነው የሚታገሉት።