1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይናና የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ግንኙነት

ረቡዕ፣ ኅዳር 2 2002

የቻይናና የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ግንኙነት ዘርፈ-ብዙ እየሆነ መሄዱን እንደቀጠለ ነው። የሁለቱ ወገን የንግድ ልውውጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአሥር ዕጅ ጨምሯል።

https://p.dw.com/p/KU2c
ምስል AP

ባለፈው ሰንበት የቻይናና የአፍሪቃ መድረክ አራተኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ ግብጽ-ሻርም ኤል-ሼይክ ላይ ተካሂዶ ነበር። ቤይጂንግ በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት አሥር ሚሊያርድ ዶላር ብድር ለማቅረብ ቃል ስትገባ ከመዋቅራዊ ግንባታ ባሻገር በተፈጥሮ እንክብካቤና በሣይንስ ዘርፍም ግንኙነቱን ለማስፋፋት መነሳቷን ነው ያስታወቀችው። የቻይና ተጽዕኖ በአፍሪቃ እያደገ መሄድ ለምዕራቡ ዓለም በአንጻሩ ይበልጥ ፈታኝ እየሆነ መሄዱም አልቀረም።

የሣይኖ-አፍሪቃው መድረክ አራተኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ የተካሄደው በሁለቱ ወገን ግንኙነት የተደረገውን ዕርምጃ ለመገምገም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ቻይና የአፍሪቃ አገሮችን መዋቅራዊ ግንባታና ማሕበራዊ ዕቅዶች ለማራመድ በመጪዎቹ ሶሥት ዓመታት ውስጥ አሥር ሚሊያርድ ዶላር ብድር እንደሚታቀርብ ቃል-መግባታቸው አገሪቱ ለትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠል የምትሰጠውን ከፍተኛ ክብደት የሚያሳይ ነው። ቻይና በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት ከትምሕርት እስከ ጤና ጥበቃ ዘርፎች በአፍሪቃ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ተሳትፎዋን ለማሳደግ እንደተነሳች በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርጋለች። የንግድ ሚኒስትሩ ቼን ዴሚንግ እንዳሉት ቻይና ለአፍሪቃ ምርቶች ገበዮቿን ለመክፈትና በተጨማሪም በክፍለ-ዓለሚቱ ይበልጥ የሥራ መስኮችን ለመክፈት ዝግጁ ናት። የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቡል ጋይትም በበኩላቸው የ 49 የአፍሪቃ መንግሥታት ልዑካን የተሳተፉበትን የሁለት ቀናት ጉባዔ በማንኛውም መስፈርት ስኬታማ ነበር ብለውታል።

ጉባዔው ያጸደቀው የጋራ መግለጫ የመጪዎቹን ሶሥት ዓመታት ዕርምጃዎች የሚጠቀልል ነው። በዚሁ መሠረት ቻይና ከመዋቅራዊና ማሕበራዊ ዕቅዶች ባሻገር በክፍለ-ዓለሚቱ የተፈጥሮ እንክብካቤና የሣይንስ ፕሮዤዎችን ታራምዳለች። አንድ መቶ የሚሆኑ የጋራ የንጹህ ኤነርጂ ፕሮዤዎችን ለመክፈት፤ እንዲሁም የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሽርክናን ለማስፈን ነው የሚታቀደው። ቻይና ከዚሁ ሌላ በርካታ ትምሕርት ቤቶችን ለመክፈትና መምሕራንን ለማሰልጠንም ቃል ስትገባ በርሷው ድጋፍ ለተቋቋሙ 60 ሆስፒታሎችና የወባ መከላከያ ማዕከላት የሕክምና መሣሪያዎችን ታቀርባለች፤ ሶሥት ሺህ የአፍሪቃ ሃኪሞችና ነርሶችም ለማሰልጠን ታቅዳለች። በጥቅሉ ቻይና ከአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ጋር ባላት የኤኮኖሚ ግንኙነት እስካሁን የምዕራቡ ዓለም መስኮች ሆነው ይታዩ የነበሩትን ዘርፎች ሁሉ ይበልጥ በቁጥጥሯ ሥር እያዋለች ነው። የበለጸጉት መንግሥታት በበኩላቸው ሂደቱን በዓይነ-ቁራኛ ሲከታተሩት ቆይተዋል። ሆኖም ጨርሶ ሊገቱት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሰ ነው የሚመስለው።

ምዕራቡ ዓለም ቻይናን በፍጥነት እያደገ የሚሄደውን ኢንዱስትሪዋን የኤነርጂና የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ለማርካት አፍሪቃን ትበዘብዛለች ሲል በየጊዜው መተቸቱ ይታወቃል። ሆኖም ቻይና ግንኙነቱን ሃቀኛና ቅድመ-ግዴታ የሌለበት አድርጋ ነው የምትመለከተው። በክፍለ-ዓለሚቱ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ብቻ ያተኮረም እንዳልሆነ ማስረገጧን ቀጥላለች። ለነገሩ ቻይና በአፍሪቃ የምታደርገው የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በተለይ ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት አጋማሽ ወዲህ ያለማቋረጥ ከፍ ሲል ነው የመጣው። ተሳትፎዋም ዘርፈ-ብዙ እየሆነ ሄዷል። ቻይና ዛሬ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ያልገባችበት አንድም አገር አይገኝም። እርግጥ በያዘችው ዘመቻ የኤኮኖሚ ጥቅሟ ቀደምት አጀንዳዋ ነው። ይሁንና በሌላ በኩል በዚህ በጀርመን የላይፕትሲግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ጥናት ፕሮፌሰር ሄልሙት አሸ እንደሚሉት ትኩረቷ ከዚያም ሻገር ይላል።

“ቻይና በአፍሪቃ ያላት ፍላጎት አዘውትሮ እንደሚነገረው በነዳጅ ዘይት፣ በመዳብና መሰል ጥሬ ሃብት ላይ ብቻ ያተኮረ ሣይሆን ሌላም ሁለተኛ ገጽታ ይኖረዋል። እርግጥ ነው ቻይና ጥሬ ዕቃዎች ያስፈልጓታል። አገሪቱ በአንድ በኩል የዓለም ዋና አምራች እንደመሆኗ መጠን ያለ ጥሬ ዕቃ ልትራመድ አትችልም። የኛም ፍጆት በተዘዋዋሪ ለዚሁ አስተዋጽኦ አለው። ግን ከዚሁ ተያይዞ የቻይና ፍላጎት በአፍሪቃ ገበያ ላይም የሚያተኩር ነው። ማለት ምርት መሸጥ የሚቻልበት”

ለምሳሌ ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ ወይም አልባሣት! ቻይና በአፍሪቃ የምታራግፈው በተቀዳሚ እነዚህን መሰል ርካሽ የሆኑ ምርቶች ነው። በሌላ በኩል የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪቃ አገሮች ውስጥ መንገዶችንና የባቡር ሃዲዶችን ይዘረጋሉ። የአየር ጣቢያዎችም ይገነባሉ። በ 2004 እና በ 2008 ዓ.ም. መካከል የሁለቱ ወገን ንግድ መጠን በአሥር ዕጅ ነው የጨመረው። ባለፈው ዓመት 170 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ደርሶ ነበር። ቤይጂንግ እርግጥ በክፍለ-ዓለሚቱ ጭብጥ የፖለቲካ ፍላጎቷንም ታራምዳለች። በዓለም ላይ ሃያሏ መንግሥት ለመሆን ባላት ግብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመሳሰሉት ዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ አጋርና አበሮችን ማፍራት ፍላጎቷ ነው። ቻይና ከአፍሪቃ ጋር አንድነቷን ለማስረገጥ ሁለቱ ወገኖች በጋራ የ 19ኛው ምዕተ-ዓመት ቅኝ-አገዛዝ ሰለቦች መሆናቸውን በተደጋጋሚ ታነሣለች። ግን በሌላ በኩል የሚያሳዝነውና ምዕራቡም ዓለም በየጊዜው የሚተችው የበርሊን የሣይንስና የፖለቲካ ምርምር ተቋም ባለደረባ ዴኒስ ቱል እንደሚሉት በአፍሪቃ ምድር የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ከበሬታ ለቻይና ቦታ የሌላቸው ነገሮች መሆናቸው ነው።

“በእርግጥም ይህ በብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች፤ በተለይም አምባገነን በሆኑት መንግሥታት ዘንድ በደስታ ነው የሚታየው። የቻይና ዝንባሌ ምዕራባውያን መንግሥታትና ለጋሽ ወገኖች የሚያደርጉት ግፊት እንዲቀንስ መርዳቱም አልቀረም”

ቻይና ከአምባገነን የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር መተባበሯ ዋናው የምትተችበት ነጥብ ነው። ለምሳሌ የሱዳንንና የዚምባብዌን ገዢዎች የመሳሰሉት ከቻይና የአፍሪቃ ሸሪኮች መካከል ይገኙበታል። የቻይና መንግሥት በቅርቡ ባለፈው ጥቅምት ወር ከጊኒ ወታደራዊ ገዢዎች ጋር በሰባት ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት ማዕድን ለማውጣት አንድ ውል መፈራረሙ የሚታወስ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ውሉ ከመፈረሙ ጥቂት ሣምንታት ቀደም ሲል ወታደራዊው መንግሥት ኮናክሪ ውስጥ በርካታ ተቃዋሚዎችን መግደሉ ዓለምን ክፉኛ ባስቆጣበት ወቅት ነበር። ይህ ቻይናን ወደደችም ጠላች ሊያሰወቅሳት የሚገባ ጉዳይ ነው። እያደር በቀላሉ የምትመለከተው ነገር ሆኖ ሊቀጥል የሚችልም አይመስልም።

“የቻይና መንግሥት በዓለምአቀፍ ደረጃ በገጠመው የዝና ጉድፈት ስጋት ላይ ,መውደቁ ይበልጥ እየታየ ይመስለኛል። ከምዕራባውያኑ ወገን ብቻ ሣይሆን አንዳንዴ ከአፍሪቃ አኳያም ትችት ሲሰነዘር ቢቀር ምላሽ መስጠቱ አልቀረም”

በዘልማድ የአፍሪቃ መንግሥታት ባለፉት አሠርተ-ዓመታት ከምዕራቡ ዓለም ከመተባበር ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። ብዙዎቹም በኤኮኖሚና በፖለቲካ የምዕራቡ ወገን ጥገኛ ሆነው ኖረዋል። ይህም ሆኖ ግን አፍሪቃ ለበለጸጉት መንግሥታት የዓለም ጓሮን ያህል ነበረች። አፍሪቃ በተለይም በዘጠናኛዎቹ ዓመታት የተረሳችው ክፍለ-ዓለም ነበረች ለማለት ይቻላል። ከፖለቲካ አንጻር ለምሳሌ በሩዋንዳ የጎሣ ዕልቂት ሲደርስ የበለጸገው ዓለም ዓይኑን ገልጾ ሊመለከተው አልፈለገም። ለዚህም ነው ዛሬ ቻይናን የመሳሰሉት በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ አገሮች በአፍሪቃ አዳዲሶቹ ተዋንያን ሊሆኑ መብቃታቸው። ይህ በአፍሪቃ የወደፊት ዕርምጃ ላይ ጠቃሚ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። በክፍለ-ዓለሚቱ ከወዲሁ አዲስ የፉክክር ሁኔታ እየተከሰተ ነው። አፍሪቃ እንደገና በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ የዓይን ማረፊያ መሆን ይዛ ነው የምትገኘው። የአፍሪቃ ጥናት ተመራማሪው ሄልሙት አሸ እንደሚሉት ሂደቱ ለአፍሪቃውያን አገሮችም አዲስ ጥርጊያን የሚከፍት ነው። ቀስ በቀስ በኤኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ጉዳዮች ከማን ጋር መተባበር እንደሚፈልጉ ራሳቸው ለመምረጥ ይችላሉ። በአንጻሩ ምዕራቡ ዓለም በሂደቱ ተጽዕኖውን እያጣ መሄዱን ግን እዚህ ገና ብዙዎች የተገነዘቡት አይመስልም።

“ምዕራቡ ዓለም ቻይናን፣ ሕንድንና ብራዚልን የመሳሰሉት አዳዲስና ክብደት ያላቸው የአፍሪቃ ሸሪኮች መጠናከር ታላቅ ፈተና እንደደቀነበት ገና በሚገባ አልተገነዘበውም”

በሌላ በኩል አፍሪቃ ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት በረጅም ጊዜ ተጠቃሚ መሆን መቻሏ ገና ግልጽ አይደለም። የቻይና ወደ አፍሪቃ ገበዮች ዘልቆ መግባት ምናልባት ክፍለ-ዓለሚቱን የሽቀጥ ማራገፊያና ቢቀር በጨርቃ-ጨርቁ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አያሌ አፍሪቃውያንን ሥረ-አጥ ሊያደርግ የሚችል ነው።

መስፍን መኮንን/DW

አርያም ተክሌ