1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ ዘመቻ

ሰኞ፣ ሐምሌ 18 2008

ከመርሕ ይልቅ ሌሎችን በመዉቀስ መተቸት፤ ከጨዋ ፖለቲካዊ ስብዕና ይበልጥ በተራ-ዘለፋና ስድብ የተካኑት፤ከተጨባጭ እዉነታ ይልቅ ስሜትን በመጓጎጥ፤ የተዛባ እዉነታን በመጥቀስ፤ ከሁሉም በላይ በጥላጫ የታጨቀዉን የዶናልድ ትራምፕን አስተሳሰብ ብዙ ሚሊዮን አሜሪካዉን እንደሚደግፉት፤ እንደሚጋሩት፤ ለገቢራዊነቱ እንደሚጥሩ መዘንጋት የለበት

https://p.dw.com/p/1JVhI
USA Republican National Convention in Cleveland
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Rourke

[No title]

እንደስደተኛ የልጅ-ልጅ፤ ልጅም፤ እንደስደተኛ አግቢ፤ ጠንካራ ሠራተኛ፤ ስደተኛ አፍቃሪ ባልም ናቸዉ።ግን የስደተኛ ጠር።እንደ ነጋዴ አዱኛ የሰገደችላቸዉ ቢሊየነር ናቸዉ።ግን ሐይለኛ አሳካሪ ።እንደ ቴሌቪዥን ሰዉ አስቂኝ ብጤ ናቸዉ።ግን አዋራጅም።ዶናልድ ጆን ትራምፕ።አሁን ደግሞ የቱጃር ልዕለ ሐያሊቱ ሐገር ዕዉቅ ፖለቲከኛ፤ ምርጥ ተናጋሪ፤ የለየለት ፅንፈኛ ሆኑ። የወግ አጥባቂዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አጩ ፕሬዝደንት።ዳራ፤ ዓላማ ዕቅዳቸዉ ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ።

ባልሜዲ-አቤርዲንሺር-ስኮትላንድ ለገነቡት የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ በ2006 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮያኑ አቆጣጠር ነዉ) መሬት ከሸጡላቸዉ አንዱ «ሰዉዬዉ ዋጋ ለማስቀነስ ሲከራከር የሚተዉን ነበር-የሚመስለዉ።» አሏቸዉ።መሬቱን ሲገዙ ኩባንያቸዉ 6ሺሕ የአካባቢዉን ሰዎች እንደሚቀጥር ቃል ገብተዉ ነበር።በ10 ዓመት ዘንድሮ የራሳቸዉ ድርጅት ባወጣዉ ዘገባ እንዳማነዉ የተቀጠሩት ሰራተኞች ሁለት መቶ ብቻ ናቸዉ።

«ብልጥ ይሏል ይኼ ነዉ።» አሉ እኒያ መሬት ሻያጭ በቀደም። ለየዋሆች ከሩቅ ገነት እያሳዩ የጨበጡትን መንጠቅ።ሐብታሙ ነጋዴ ባፍታ ፖለቲከኛ ሆነዉ ከሆኑ በኋላ ባለፈዉ ወር ግዙፍ የጎልፍ መጫወጫ ሜዳቸዉን ጎብኝተዉ ነበር።ስኮት ላንድ የገቡት የብሪታንያ ሕዝብ ሐገሩ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት እንድትወጣ በወሰነ ማግሥት ነበር።ዉሳኔዉን «ድንቅ» አሉት።የሕዝቡን ስሜት ደግሞ «ሐገሩ እንዲመለሥለት ይፈልጋል።»

«ሰዎች ሐገራቸዉ እንዲመለስላቸዉ ይፍልጋሉ። ነፃነታቸዉን ይፈልጋሉ።የመላዉ አዉሮጳ ሕዝብ ትናንት ማታ ከሆነዉ በላይ ይፈልጋል።ድንበራቸዉ፤ ገንዘባቸዉ፤ ብዙ ነገር እንዲመለስላቸዉ ይፈልጋሉ። ሐገራቸዉ እንዲመለስላቸዉ ይፈልጋሉ።»

USA Republican National Convention in Cleveland Donald Trump Rede
ምስል Reuters/C. Allegri

ሰዉዬዉ መሬት የሸጡላቸዉ የዋሕ እንዳሉት ቲያትር እየሰሩ ይሆን? ስኮትላንዶችስ? ትራምፕ የወሰዱባቸዉ መሬት፤ የገቡላቸዉ ቃል እንዲመለስላቸዉ አይፈልጉ ይሆን? ማይክል ፎርቢስ መጀመሪያኑ ሰዶ-ማሳደዱን አልፈልጉትም። ዋዛ ገበሬ አይደሉም።በ2006 የእርሻ መሬታቸዉን እንዲሸጡላቸዉ ትራምፕ አባበሏቸዉ እንቢኝ አሉ።ዋጋ ጨመሩላቸዉ አልሸጥም አሉ።እንደገና ጨመሩላቸዉ-450 ሺሕ ፓዉንድ ለመሬቱ እና በዓመት 50 ሺሕ ፓዉንድ ደሞዝ ልቁረጥልሕ አሏቸዉ።ገበሬዉ እንቢኝ ብለዉ ድርቅ።

የትራምፕ ኩባንያ የፎርቢስን ትንሽ የእርሻ መሬት ከሰፊዉ የጎልፍ ሜዳ ጋር ቀይጦ አጠረባቸዉ።ገበሬዉ በፍርድ ቤት ተሟግተዉ አሸነፉ።ያኔ የአሜሪካና የብሪታንያ ጋዜጠኞች፤ የፊልምና የድራማ ደራሲዎች የገበሬዉን ታሪክ የዜናቸዉ ማድመቂያ፤ የፊልም ድርስታቸዉ ጭብጥ፤ የገቢያቸዉ ምንጭ አድርገዉ ጀግንነቱን ያራግቡት ገቡ።

የማይክል ፎርቢስን ፅናት፤ ትዕግሥት፤ እድል፤ ብልሐት ያላገኙ ስንት ገበሬዎች፤ ስንት ወዛደሮች፤ ስንት ደከሞች በስንት ቱጃሮች ለስንት ጊዜ ተገፍተዉ-ይገፉስ ይሆን-ነዉ መልስ የለሹ ጥያቄ? ብቻ ስኮትላንድ የዶናልድ ትራምፕ እናት የወይዘሮ ሜሪ አን ማክሎይድ ሐገር ነዉ።በናታቸዉ ስደተኛ ናቸዉ ማለት ነዉ።አባታቸዉ ፍሪድ ትራምፕ ካልሽታት ከተባለችዉ የጀርመን ትንሽ ከተማ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተሰደዱ ባልና-ሚስት ልጅ ናቸዉ።በአያቶቻቸዉም ስደተኛ ናቸዉ።

በቀደም በደቡብ ጀርመናዊቱ ትልቅ ከተማ ሙኒክ አንድ የአዕምሮ ሕመምተኛ ወጣት አስር እራሱን መግደሉ እንደተሰማ ገዳዩ አሸባሪ-መሆን አለመሆኑ በሚያከራክርበት መሐል ሰዉዬዉ ከቴሌቪዥን ካሜሪ ፊት ብቅ አሉ-እና « የራሳቸዉ ጥፋት» ነዉ አሉ።«የዉጪ ሰዉ «እያጋበሱ»«ሰዎች ወደ ግዛታቸዉ እንዲገቡ ፈቅደዋል።Brexit የደረሰዉ ለዚሕ ነዉ። ግልፅ ነዉ።ምክንያቱም ብሪታንያዎች የነሱ ጣጣ በጣም ሰለቸን አሉ።ምንድነዉ የሚደረገዉ ሰለቸን አሉ።»

USA Republican National Convention in Cleveland Donald Trump Ivanka Trump
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Scott Applewhite

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀዉ ከዓለም ሕዝብ 65 ሚሊዮኑ ስደተኛ ነዉ።አብዛኛዉ ስደተኛ የሠፈረዉ ደሐ ሐገራት ዉስጥ ነዉ።የብሪታንያዉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም ባለፈዉ ሳምንት ይፋ ባደረገዉ ጥናቱ እንዳስታወቀዉ ከግማሽ የሚበልጠዉን ስደተኛ የሚያስተናግዱት አምስት ደሐ ሐገራት ናቸዉ።ዮርዳኖስ፤ ቱርክ፤ በሐይል የተያዘዉ የፍልስጤም ግዛት፤ፓኪስታንና ሊባኖስ።

እነዚሕ ሐገራት ከዓለም አጠቃላይ ምጣኔ ሐብት ሁለት በመቶዉን ብቻ ያገኛሉ።ዩናይትድ ስቴትስ፤ ቻይና፤ ጃፓን፤ ጀርመን፤ ብሪታንያና ፈረንሳይ ከዓለም ምጣኔ ሐብት አብዛኛዉን ያጋብሳሉ።እነዚሕ ስድስት ሐብታም ሐገራት የሚያስተናግዱት ስደተኛ ከ65 ሚሊዮኑ ዘጠኝ በመቶዉን ብቻ ነዉ።ለዶናልድ ትራምፕ ይሕም በዝቶ ስደተኛ ጨርሶ አንቀበልም አሉ።«ስደተኞችን የምንቆጣጠርበት ስልት ትክክለኛነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ፤ አሸባሪዎች ይኖሩባቸዉን ከሚባሉ ሐገራት ስደተኛ እንዳይመጣ ማገድ አለብን።ሐገራችን እንዲገቡ አንፈልግም።»

አያቶቻቸዉ ስደተኛ ወይም የዉጪ ሰዉ ናቸዉ።እናታቸዉ ስደተኛ ናቸዉ።ባለቤታቸዉ ስደተኛ ናቸዉ።እሳቸዉ ግን ፀረ-ስደተኛ።ብቻቸዉን ግን አይደሉም።በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታይ፤ ደጋፊ፤ አድናቂ አጨብጫቢም አላቸዉ።

18 ዓመቱን ወጣት ፎቶ ግራፍ ያየ ቆፍጣና ወታደርነቱን አይጠራጠርም።ወታደራዊ ዩኒፎርሙ በሽልማት ሪባን፤ በኒሻንና ጌጥ ተንቆጥቁጧል።ከፎቶ ግራፉ ግርጌ ያለዉ ፅሁፍ፤ የኒዮርክ የጦር አካዳሚ ይላል።ይሁንና ከትንሺቱ ገጠራማ ከተማ ኮርንዎል ኦን ሐድሰን አጠገብ የሚገኘዉ ትምሕርት ቤት የግል እንጂ የአሜሪካ ወታደሮች የሚሠለጥኑበት አይደለም።

የቬትናም ጦርነት ባየለበት በዚያ ዘመን ወታደራዊ እዉቀት ያለዉ ቀርቶ ማንኛዉም አሜሪካዊ ወጣት ቬትናም የመዝመት ብሔራዊ ግዴታ ነበረበት።ፎትግራፉ ላይ ቆፍጣና ወታደር የመሠለዉ ወጣት ግን ሐብቱንም፤ዘመዱንም፤ ብልጣብልጥነቱም ጋሻ-መካታ አድርጎ የጤና እክል የሚል ሰበብ ፈጠረ።ከዘመቻ ቀረ።

በቅርቡ ግን ኦርላንዶ ላይ አንድ ታጣቂ ሐምሳ ሰዎችን ሲገድል በወጣትነታቸዉ እንዳደረጉት ወይም እንደተወኑት ሳይሆን በፎቶ-ግራፍ እንዳስመሉት የሚያደርግ ጀግና ቢኖር ኖሮ አሉ።ከባርኔጣ እስከ ቲ-ሸርት፤ ከቴሌቪዥን ማስታወቂያ እስከ መሰብሰቢያ አዳራሽ ቅስት የሚፃፍ፤የሚነገር፤ የሚለጠፍ መፈክራቸዉ አሜሪካንን ዳግም ታላቅ ማድረግ የሚል ነዉ።«አሜሪካ ከምንግዜዉም በላይ ታላቅ፤የተሻለችና ጠንካራ ሆና መምጣትዋን ለዓለም የምናሳይበት ወቅት ነዉ።»

USA Republican National Convention in Cleveland Ivanka Trump
ምስል picture-alliance/AP Photo/P. Sancya

ታላቅዋ አሜሪካ ዶናልድ ጆን ትራምፕን ፕሬዝደንቷ ታደርጋለች።የትራምፕዋ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በግንብ ታሳጥራለች።ስደተኞች ና ሙስሊሞች ግዛትዋ ከገቡ ታባርራለች።ለመግባት ከሞከሩ ታግዳለች።ምናልባትም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የሕልዉናዋ መሠረት የሆነዉን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስታፈርስ፤ ወይም ከአባልነት ስትወጣ ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር ያላትን ወዳጅነት ትቀንሳለች።

የትራምፕዋ አሜሪካ ከዓለም ሁለተኛ ሐብታም ሐገር ቻይና ጋር ያላትን የንግድ ልዉዉጥ ትገድባለች።ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የቀረጥ ጭማሪ ታደርጋለች። በነገራችን ላይ የትራምፕ ደጋፊ፤አድናቂ፤ አወዳሾች በየሥፍራዉ ለምርጫ ዘመቻ የሚጠቀሙበት አብዛኛ ቁሳቁስ በተለይም በሸክላ ላይ የተቀረፀ የትራምፕ ምስል የሚገዛዉ ከቻይ ነዉ።

የትራምፕ የወጪ መርሕ አዉሮጳን ከቻይና ሜክሲኮን ከኔቶ ሳይለይ ለአሜሪካ መንበርከካቸዉን ለማረጋገጥ ያለመ ነዉ።በ1947 በዩናይትድ ስቴትስ ግፊትና ጫና በብሪታንያ ትብብር እስራኤል ከተመሠረተች ወዲሕ መካከለኛዉ ምሥራቅ ሰላም ሰፍኖ አያዉቅም።

ከሐሪ ኤስ ትሩማን እስከ ባራክ ኦባማ የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች በዚያ ምድር ሠላም ለማስፈን እየፎከሩ ጦርነት እያቀጣጠሉ ወደ ሥልጣን እየመጡ መሔዳቸዉ ሐቅ ነዉ።ለዶናልድ ትራምፕ ግን የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት የተጀመረዉ የዛሬ አስራአምስት ዓመት ነዉ።የጦርነቱ ጥፋት ዉድመት ደግሞ የዋና ተቀናቃኛቸዉ የወይዘሮ ሒላፊ ክሊንተን ዉርስ ነዉ።

«በመካከለኛዉ ምሥራቅ የተቀጣጠለዉ ጦርነት አስራ-አምስት አመት ካስቆጠረ በኋላ፤ በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከወጣና በሺ የሚቆጠር ሕይወት ከጠፋ በኋላ አሁንም ሁኔታዉ ከምን ጊዜዉም በላይም አስከፊ ነዉ።ይሕ የሒላሪ ክሊንተን ዉርስ ቅርስ ነዉ። ሞት፤ጥፋት፤ሽብር እና ደካማነት።»

እርግጥ ነዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ ለ15 ሳይሆን ለስልሳ ስምንት ዓመት ሰላም ሰፍኖ አያዉቅም።ጦርነቱ በ1948 ሲጀመር ሒላሪ ክሊንተን የአንድ ዓመት ጨቅላ ነበሩ። የዛሬ አስራ-አምስት ዓመት ማለት በ2001 እንዳዲስ የተጀመረ ጦርነት የለም።ቢኖር እንኳ ክሊንተን በ2001 ቀዳማዊ እመቤትም፤ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርም አልነበሩም።

ዩናይትድ ስቴትስ በቀጥታ የተካፈለችና የምትካፈልበትን ጦርነት የጫረችዉ በ2003 ኢራቅን ስትወር ነዉ።የዚያ ወረራ መሪ፤አቀናባሪና አዛዥ ደግሞ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ሐብታም፤ ወግ አጥባቂ፤ አክራሪ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸዉ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ተጋሪም ናቸዉ። ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ።ያም ሆኖ ትራምፕ ብዙ ሕይወት፤ ትሪሊዮን ዶላር አስቆጠረ ያሉትን ጦርነት የሚያስቁመበትን መርሕ አልተናገሩም።ጦርነቱን ለማጋጋም ግን ዛቱ።

USA Nominierung von Donald Trump bei der Republikanischen Konvention in Cleveland
ምስል picture-alliance/newscom/P. Marovich

«የአይሲስን አረመናዊነት አናሸንፈዋለን።ባጭር ጊዜ እናሸንፋቸዋለን።»የሒላሪ ክሊንተን አፀፋ በያዝነዉ ሳምንት ማብቂያ በግልፅ ይታወቃል።የአሜሪካ ሕዝብን አጠቃላይ ዉሳኔ ለማወቅ እስከ ሕዳር መጠበቅ ግድ ነዉ።እስከዚያዉ ከመርሕ ይልቅ ሌሎችን በመዉቀስ መተቸት፤ ከጨዋ ፖለቲካዊ ስብዕና ይበልጥ በተራ-ዘለፋና ስድብ የተካኑት፤ከተጨባጭ እዉነታ ይልቅ ስሜትን በመጓጎጥ፤ የተዛባ እዉነታን በመጥቀስ፤ ከሁሉም በላይ በጥላጫ የታጨቀዉን የዶናልድ ትራምፕን አስተሳሰብ ብዙ ሚሊዮን አሜሪካዉን እንደሚደግፉት፤ እንደሚጋሩት፤ ለገቢራዊነቱ እንደሚጥሩ መዘንጋት የለበት።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ