1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ስጋት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 6 2009

በሁለቱ እጩዎች የምርጫ ዘመቻ ወቅትም አብዛኛዎቹ የአውሮጳ ፖለቲከኞች ትራምፕን ሲያጣጥሉ የሚናገሩትንም ፋይዳ ቢስ ሲሉ ነበር የከረሙት ። አብዛኛው ዓለም ሲተቻቸው እና ሲያብጠለጥላቸው የቆየው ትራምፕ ማሸነፋቸው ፣አውሮጳን አስደንግጧል ። ለምን ?

https://p.dw.com/p/2SiNe
US-Präsidentschaftswahl 2016 - Sieg & Rede Donald Trump
ምስል Getty Images/S. Platt

Europa 151116 ( Europa nach dem Sieg von Trump) - MP3-Stereo

የዛሬ ሳምንት በዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የአወዛጋቢው የሪፐብሊካኖቹ እጩ የዶናልድ ትራምፕ ማሸነፍ እዚህ ጀርመን እንዲሁም በአጠቃላይ በአውሮጳ ማነጋገሩ ቀጥሏል ። የርሳቸው መመረጥ በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ሥልጣን ለመያዝ ለቋመጡት ቀኝ ጽንፈኞች የልብ ልብ የሚሰጥ  ውጤት መሆኑ  ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል ።  የዛሬው አውሮፓ እና ጀርመን ዝግጅታችን የትራምፕ ድል በጀርመን ብሎም በአውሮጳ ያሳደረው ስጋት እና ምክንያቱን ያስቃኘናል ። 
የዩናይትድ ስቴትስ ወግ አጥባቂ ፓርቲ የሪፐብሊካኖቹ እጩ ቱጃሩ ፖለቲከናኛ ዶናልድ ትራምፕ ድል ማድረጋቸው ለብዙ አውሮጳውያን ያልተጠበቀ ነበር ፤ ውጤቱ እስካሁንም ያልተዋጠላቸው ጥቁት አይደሉም ። ከተራው ዜጋ አንስቶ እስከ ፖለቲከኞች ፣በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ልምድ ያላቸው አንጋፋዋ ፖለቲከኛ ሴናተር እና የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዴሞክራቶቿ እጩ ሂለሪ ክሊንተን ምርጫውን እንደሚያሸንፉ በጣም እርግጠኛ ሆነው ነበር ውጤቱን የሚጠባበቁት ። በሁለቱ እጩዎች የምርጫ ዘመቻ ወቅትም አብዛኛዎቹ የአውሮጳ ፖለቲከኞች ትራምፕን ሲያጣጥሉ የሚናገሩትንም ፋይዳ ቢስ ሲሉ ነበር የከረሙት ። አብዛኛው ዓለም ሲተቻቸው እና ሲያብጠለጥላቸው የቆየው ትራምፕ ማሸነፋቸው ፣አውሮጳን አስደንግጧል ። ለምን ? የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው አውሮጳውያንን ድንጋጤ ላይ የጣለቸው እና ያሰጋቸው እነዚህ የትራምፕ ባህርያት ብቻ አይደሉም ። በምርጫ ዘመቻ ወቅት ያነሷቸው አወዛጋቢ ሃሳቦችም ጭምር እንጂ ። የ70 ዓመቱ ቢሊየነር ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ህገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ከአሜሪካን  ለማባረር ፣ ሙስሊሞች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ለማገድ ፣ እንዲሁም ነፃ የንግድ ውሎችን ለመሰረዝ ቃል ገብተዋል ። የንግድ ውሎቹ አውሮጳንም ይመለከታል ።እነዚህ ቃል ከገቡባቸው ብዙ አወዛጋቢ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው ። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ደግሞ ለብዙዎቹ አውሮጳውያን ድንጋጤው ፣ እኛም የአሜሪካን እጣ ይገጥመን ይሆን ? ከሚል ስጋት የመጣ ነው ይላል ። እንደ ገበያው የአውሮጳውያኑ  ስጋት ይህ ብቻ አይደለም ከዚህ በተቃራኒ የሚሰጡ አስተያየቶችም አሉ ። የትራምፕ መመረጥ አውሮጳን ከማናጋት ይልቅ  እዲጠናከር ያደርጋል የሚለው አስተሳሰብ አንዱ ነው ። አሜሪካ ከአውሮፓ ጋር በተለያዩ መስኮች የሚኖራት ትብብር እንዴት እንደሚቀጥል ለጊዜው ግልጽ አለመሆኑ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው ። የትራምፕ የውጭ መርህ በግልፅ ባይታወቅም በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ሀገራቸው ሩስያ እና ቻይናንን ከመሳሰሉ ሀገሮች ጋር እንዲኖራት ስለሚፈልጉት ግንኙነቶች ፍንጮች ሰጥተዋል  ። እነዚህ ግንኙነቶች፣ በአውሮጳ ላይ ሊያሳድሩ የሚችሏቸውን ተፅእኖዎች ለመቋቋም አውሮጳ ራስዋን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባት አመልካች ናቸው ይላል ይልማ።
ሩስያን በሚመለከት የትራምፕን አስተሳሰብ የሚጋሩ የአውሮጳ ሀገራትም አሉ ።በዚህ ረገድ ኢጣልያ ትጠቀሳለች ። በሌላ በኩል ትራምፕ ምናልባት በምርጫ ዘመቻ ወቅት እወስዳቸዋለሁ ያሏቸውን አወዛጋቢ እርምጃዎች በሙሉ ሥልጣን ሲረከቡ ሊተዉቸው ይችላሉ የሚሉ ግምቶች ይሰነዘራሉ ። ይህን በሂደት ለማየት የሚጠብቁ እንዳሉ ሁሉ መሆኑን የሚጠራጠሩም አልጠፉም ። የአውሮጳ ህብረት ግን ከትራምፕ ጋር በህብረቱ እና በአሜሪካን ግንኙነቶች ላይ ለመነጋገር ብራሰልስን እንዲጎበኙ ከወዲሁ ጋብዟቸዋል ። ትራምፕ አውሮጳ ሲመጡ የመሪዎች መስተንግዶ ብቻ ሳይሆን የህዝቡ ተቃውሞም ነው የሚጠብቃቸው ይላል ገበያው ።በመጪው ጥር 12 ፣2009 ዓም ሥልጣናቸውን ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚያስረክቡት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት የመጨረሻ በተባለ የግሪክ የጀርመን እና የፔሩ ጉብኝታቸው በዩናይትድ ስቴትሱ ምርጫ ውጤት የተደናገጡትን የዓለም መሪዎች ለማረጋግት ይሞክራሉ  ።ኦባማ ነገ ማታ በርሊን ሲመጡ  በአጋጣሚው ፣  ከውጭ መሪዎች የቅርብ አጋራቸው ሆነው የዘለቁትን የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ያመሰግናሉ ፤ ዋና ዋና ከሚባሉ የአውሮጳ መሪዎችም ጋር ይወያያሉ ተብሏል ። ኦባማ በጉብኝታቸው የእስከዛሬዎቹ ግንኙነቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ያሳስባሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው።የትራምፕ ድል የገባቸው የአውሮጳ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ብቻ ይመስላሉ ። እነርሱ በምርጫው ውጤት ፈንድቀዋል ። የአውሮጳ መሪዎች እና ፖለቲከኞች ግን ትራምፕ ምን ይዘው እንደሚመጡ ለማወቅ ተቸግረዋል ። ፈረንሳይ የውጭ መርሃቸውን ግልጽ እንዲያደርጉ ጠይቃለች ። ጀርመን ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ባሏቸው የጋራ እሴቶች መሠረት ከርሳቸው ጋር በቅርበት ለመሥራት እንደምትፈልግ አስታውቃለች ። ጥያቄዎቹ እና ግርታዎቹ ዶናልድ ትራምፕ ከዛሬ ሁለት ወር በኋላ 45 ተኛው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ሆነው ሥልጣን ሲይዙ መልስ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርግ  ። 

USA Washington Treffen Obama und Amtsnachfolger Trump
ምስል Getty Images/AFP/J. Watson
Deutschland Reaktion US-Wahl - Bundeskanzlerin Angela Merkel
ምስል Reuters/A. Schmidt

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ