1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታዳጊው ዓለም መዋቅራዊ ልማትና የዕርዳታው ጥረት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 1998

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነዳጅ ዘይት አምራች መንግሥታት በዓለም ላይ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ የታዳጊ ሃገራትን መዋቅራዊ ልማት ለማራመድ ከንግዱ ከሚያገኙት ገቢ አንድ-አሥረኛዋን ድርሻ እንዲያበረክቱ ሰሞኑን ሃሣብ ሰንዝሯል።

https://p.dw.com/p/E0dZ
የአፍሪቃ የልማት እጦት ገጽታ
የአፍሪቃ የልማት እጦት ገጽታምስል AP

የድሃ ድሃ ተብለው ከሚመደቡት ሃምሣ አገሮች መካከል አብዛኞቹ፤ ማለትም 34ቱ የሚገኙት አፍሪቃ ውስጥ ነው። ሃሣቡ ገቢር ቢሆን ድህነትን ለመቀነስ ከተጸነሱት ሌሎች ውጥኖች ተጣምሮ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የብዙዎች ዕምነት ነው። ጥያቄው ጥሪው ሰሚ ጆሮ ያገኛል ወይ ነው። በተባበሩት መንግሥታት ተቋም በዝቅተኛ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራት ጉዳይ ምክትል ዋና ጸሐፊ አንዋሩል-ካሪም-ቾውዱሪይ ነዳጅ ዘይት አምራች መንግሥታት ከእያንዳንዷ ከሚሸጧት በርሚል ነዳጅ ዋጋ አሥሯን ሣንቲም በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ለድሆቹ አገሮች መዋቅራዊ ዕድገት እንዲለግሱ አሳስበዋል። ይህም ለድሆቹ አገሮች ልማት አዲስ የገንዘብ ምንጭ ለማግኘት የተያዘው ጥረት አንድ አካል መሆኑ ነው።

እርግጥ ሃሣቡ ገቢር እንዲሆን ከአምራቾቹ አገሮችና በምርቱ ተግባር በቀጥታ ከሚሳተፉት ኩባንያዎች አኳያ አስተማማኝ ፍላጎት ወይም ዝግጁነት መገለጽ ይኖርበታል። ለነገሩ የነዚህ ወገኖች ሃብት በነዳጅ ዋጋ መናር ሳቢያ በእጥፍ ድርብ እየጨመረ ነው የመጣው። በዓለም ላይ የድሃ ድሃ ተብለው ከሚመደቡት ሃምሣ ሃገራት 34ቱ፤ ቡሩንዲን፣ ማሊን፣ ላይቤሪያን፣ ሮዋንዳንና ሶማሊያን የመሳሰሉት የሚገኙት ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት ሳውዲት አረቢያን፣ ኩዌይትን፣ ካታርንና ኢራንን በመሳሰሉት አገሮች ነዳጅ ዘይት ሰፊ የገንዘብ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ በዚህ ዓመት ከውጭ ንግድ የሚገኘው ገቢ ከአራት መቶ ሚሊያርድ ዶላር እንደሚበልጥ ይጠበቃል። ቀደም ባለው 2005 ዓ.ም. 307 ሚሊያርድ ዶላር ነበር።

ይህ ግምት የተመሠረተው በበርሚል አማካይ የ 57 ዶላር ዋጋን መሠረት በማድረግ እንደሆነ ባለፈው ሚያዚያ ወር ወጥቶ የነበረ የድርጅቱ ጥናት ያመለከተው ጉዳይ ነው። ግን ከዚያን ወዲህ ዋጋው ከሰባ ዶላር በላይ ሲንር ከአምሥት ዓመታት በፊት ከነበረው በሶሥት ዕጅ ጨምሯል። አምራቾቹ ይበልጥ ካብተዋል ማለት ነው። አልጄሪያን፣ ካናዳን፣ ቬኔዙዌላን፣ ኖርዌይን፣ ሜክሢኮንና አሜሪካን ጨምሮ 17ቱ ቀደምት ነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች ከበርሚል ነዳጅ ዋጋ አሥር ሣንቲም የምትሆነውን ለድሆች አገሮች ልማት ቢመድቡ በየወሩ ከሚያገኙት 176.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ 17.6 ሚሊዮኑ ድርሻ የሚሆን ነው።

በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በሚገኙት አገሮች አዲስ የገንዘብ ምንጭ ቢገኝ ሊደጎሙ የሚችሉ፤ ለጊዜው ግን የሚገባው ፊናንስ የተጓደለባቸው ብዙ የሚንቀሳቀሱ መዋቅራዊ ፕሮዤዎች አሉ። ቾውዱሪይ በቅርቡ ጀኔቫ ላይ ተካሂዶ በነበረ የተባበሩት መንግሥታት የምጣኔ-ሐብትና ማሕበራዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የልማት አስተዋጽኦውን ጥሪ በመሰንዘር የነዳጅ ዘይት አምራቾችን አወንታዊ ምላሽ እንደሚያገኙ ተሥፋቸውን ገልጸው ነበር። ሆኖም እስካሁን የተገኘ ጭብጥ ነገር የለም። ከመካከለኛው ምሥራቅ ሃብታም አገሮች በነዳጅ ዘይትና በጋዝ የታደለችው ካታር ብቻ ናት በዚህ አቅጣጫ መንቀሳቀስ የያዘችው።

ካታር ባለፈው ዓመት የ 77 ታዳጊ መንግሥታት ቡድን በመባል ለሚታወቀው 132 ዓባል ሃገራት ላሉት ስብስብ ልዩ የገንዘብ ጥረት ማንቀሳቀሷ አይዘነጋም። ሃምሣዎቹ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ አገሮች ደግሞ በዚሁ ስብስብ ውስጥ የተጠቃለሉ ናቸው። በሌላ በኩል አብዛኞቹ የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ ዘይት አምራቾች ግን ያጋጣሚ ሆኖ በወቅቱ በጦርነት የወደመችውን የሊባኖስን መልሶ-ግንባታ በመደገፍ ተወጥረው ነው የሚገኙት። ተጨማሪ ወጪ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸው ታዲያ ጥቂትም ቢሆን ያጠያይቃል። ይህም ሆኖ ግን ከአምራቾቹ አገሮች በኩል ጥሪው ሰሚ ጆር ሊያጣ የማይገባው ጉዳይ ነው።

ለምን? በ 70ኛዎቹ ዓመታት የአረብ መንግሥታት ዓለምአቀፍ የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ ይሄው ጸጋ የሌላቸው የደቡቡ ዓለም አገሮች፤ ይህም ማዕቀቡን የደገፉትንም ጭምር ይጠቀልላል በጣሙን ተጎድተዋል። ጉዳቱ ደግሞ በሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ላይ የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ እንደነበረው ግልጽ ነው። ስለዚህም ዛሬ ነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች የተወሰነ ገቢያቸውን የደቡቡን ዓለም ልማት ለመደገፍ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸው ተገቢነት አለው። በተለይም በዚህ በኩል የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች ያለባቸው ግዴታ ደግሞ የበለጠ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም። እነዚሁ ባለፉት ዓመታት በቀጠለው የዋጋ መናር ያጋበሱት ትርፍ መጠን ሲታሰብ በአንጻሩ በዓለም ሕዝብና በኤነርጂ ነክ ጉዳዮች የሚያሣዩት ዝንባሌ ሞራላዊነት የጎደለው ነው።

ይሁን እንጂ ብዙዎች ፖለቲከኞችና ተቋማት በነዳጅ ዘይት አውጪዎቹ ኩባንያዎች ላይ የቃላት ትችት ከመሰንዘር አልፈው ካጋበሱት ትርፍ ጥቂቱን እንኳን ለማግኘት ተግባራዊ ዕርምጃዎች ሲወስዱ አይታዩም። ታዲያ በቂ ሃብት ባልጠፋባት ምድር ረሃብና ድህነት የአንዱ ዓለም ክፍል ገጽታ መሆኑ ማሳዘን ብቻ ሣይሆን ግራ የሚያጋባም ነው። ነዳጅ ዘይት አምራቾች የገቢያቸውን ኢምንት ድርሻ እንዲለግሱ በተባበሩት መንግሥታት የቀረበው የቅርብ ሃሣብ በተለይ በዓለም ላይ ያለውን የድሃ-ሃብታም ግንኙነት መስፋት ለማመልከትም የተወጠነ ነው። እርግጥ ያለፈው ጊዜ ዝንባሌም ሊዘነጋ አይገባውም። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ 22 የዓለም ቀደምት ሃብታም አገሮች ከአጠቃላይ ዓመታዊ ብሄራዊ ምርታቸው 0.7 ከመቶ የምትሆነዋን ድርሻ ለታዳጊ አገሮች የባሕር ማዶ የልማት ዕርዳታ እንዲያውሉ የጠየቀው ከ 35 ዓመታት በፊት ነበር።
ግን እስከዛሬ የተጣለውን መስፈርት አሟልተው የሚገኙት አገሮች አምሥት ብቻ ናቸው። ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድና ሉክሰምቡርግ! ዕርዳታዋ በዝቅተኛ 0.1 ከመቶ ደረጃ ተወስኖ የሚገኘው አሜሪካ ሌላው ቀርቶ ከሶሥት አሠርተ-ዓመታት በፊት ከተጣለው መስፈርት መቼ እንደምትደርስ እንኳ የጊዜ ገደብ አላስቀመጠችም። በመሆኑም በዓለም ላይ ዋነኛዋ ሃብታም አገር አሜሪካ ከ 22ቱ የበለጸጉ አገሮች የመጨረሻውን ቦታ ይዛ ነው የምትገኘው። ይህ ደግሞ በታዳጊዎቹ አገሮች ዘንድ ተሥፋን የሚያዳብር አይደለም።