1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታሳሪዎች ሰብዓዊ መብትና የቤተሰቦቻቸዉ ጭንቀት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 20 2009

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተፈፃሚነት የሚመረምረዉ አጣሪ ቦርድ ካለፈዉ ሰምንት ጀምሮ የታሳሪዎችን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ለመመርመር በኦሮሚያና በአማራ ክልል ያሉ እስርቤቶችንና ወታደራዊ ካምፖችን እየጎበኘ መሆኑ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/2TSZp
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

Prisoners HR and Family Concern - MP3-Stereo

የመንግሥት መገናኛ ብዙሀን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ቦርድ በአማራ ክልል አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በእንጅባራ ማረሚያ ቤት የእስረኞች የምግብ አቅርቦት እና  የጤና ሁኔታ ጥሩ መሆኑንና «ማረሚያ ቤት ከገቡ በኋላም ምንም አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተፈጸመባቸው» ታራሚዎቹቹ ተናግረዋል ሲሉ ዘግበዋል።

ስለ ቦርዱ መግለጫ አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው መካከል አንድ የአዳማ ነዋሪ ይገኙበታል። «ከቦርዱ የምንሰማቸዉ ነገሮችና በመሬት ያለዉ የሚሆነው በጣም ለየቅል ነዉ» «ኮማንድ ፖስቱ ሳይቋቋም በፊትም ሆነ ከተቋቋመ በዋላ ወከባዉ፣ ድብደባዉና የጅምላ እስር ቀጥለዋል» ይላሉ የአዳማው ነዋሪ ። እንደርሳቸው የእስረኞች መብት አልተጣሰም የሚባለዉ «ቀልድ» ነዉ።

አሁን ባለው ሁኔታ «የታሰረን ሰዉ ሄዶ መጠየቅ ወንጀለኛ ያደርጋል ይላሉ የአዳማው ነዋሪ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ አስተያየት ሰጭ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ የሚኖሩት ሁለት ወንድሞቻቸዉ በጦላይ ወታደረዊ ማሰልጠኛ ካምፕ በእስር ላይ እንደምገኙ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። እርሳቸዉ እንደሸሹ የሚናገሩት እኝሁ አስተያየት ወንድሞቻቸዉ እንዴት እነደታሰሩና በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል፣ «መጀመርያ ሲይዟቸዉ ከከተማ ዉስጥ ነበር። ከዛ በኋላ ወደ ጦላይ እንዳሳለፋቸዉ ተናግረዉ ነብር። አንተ ማወቅ ያለብህ የጦላይን ተዉና እዚህ በወረዳችን የታስሩትን ለመጠየቅ ከባድ ሆኖዋል። በዙ ሰዎች ሄደው ለመጠየቅ ፍላጎት ቢኖራቸዉም እኔም እታሰራለዉ በሚል ለደህንነታቸዉ ፈርተዉ ቁጭ ብለዋል። ሄዶ መጠየቅም ይከብዳል። መሄድም አይቻልም።»

ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት ታናሽ ወንድማቸዉ ከቢሮቸዉ ተወስደው መታሰራቸውን ይናገራሉ ። የታሰሩበትን ምክንያት ማወቅ ግን አልተቻለም ይላሉ።

የአጣሪ ቦርዱ አባላትና ሌሎች የሚመለከታቸዉን የመንግስት አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራርያ እንዲሰጡን ለመጠየቅ ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካም። 

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ