1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታሪክ አሻራ ለወደፊት ትዉስታ

ሐሙስ፣ መስከረም 8 2007

በዓለማችን «ግሎባላይዜሽን» ወይም አፅናፋዊዉን ትስስርን ተከትሎ በተለይ በአፍሪቃ ሀገራት ከተሞች የሚደረገዉ ፈጣን የግንባታ ሥራ ታሪካዊ ቅርሶችን እያወደመ መሆኑ አሳሰቢነቱን እያጎላ መጥቶአል።

https://p.dw.com/p/1DF6r
Internationale Konferenz Future Memories in Addis Abeba
የሜክሲኮ አደባባይ ፍራሽን ፎቶ የያዘዉ የጉባዉ መጥርያ ካርድ

ጉባኤዉ በከተማ ግንባታ ሰበብ እየጠፉ እና እየተረሱ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችና ባህላዊ አካብያዊ ማኅበረሰቡ የገነባቸዉ ኃሳባዊ ቦታዎችን እንዴት መጠበቅ ይቻላል፤ በሚለዉ ርዕስ ላይ ተወያይቶአል። „ፊቸር ሜሞሪስ“ «የወደፊት ትዉስታዎች» በተሰኘ መጠርያ የተሰጠዉ አዲስ አበባ ላይ የተዘጋጀዉ ስብሰባ በጀርመኑ የዉጭ ግንኙነት ተቋም እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፤ አለ የሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት የተዘጋጀና የታሪክ ምሁራን፤ የምህንድስና ሰራተኞች፤ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች እንዲሁም በተለያየ የሞያ ዘርፍ የሚሰሩ ዓለማቀፍ እንግዶችን ያሳተፈ ነበር። በጉባኤዉ የጀርመን የዉጭ ግንኙነት ተቋም የሥነ-ጥበብ ክፍል ኃላፊ ኤልካ አዉስ ዴሞር ተገኝተዋል። የለቱ ዝግጅታችን «የወደፊት ትዉስታዎች» በሚል በከተማ ግንባታ ሰበብ በመጥፋት ላይ ያለዉን ታሪካዊ ቅርስ ለመጠበቅ በተደረገዉ ጉባኤ ላይ ያተኮረ ነው። ለሶስት ቀናት የዘለቀዉ ጉባኤ በጀርመኑ የዉጭ ግንኙነት ተቋም እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ «አለ የሥነ - ጥበባትና ዲዛይን ት/ቤት» ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ በተለይ በከተማ መገንባት ሰበብ እየጠፋ ያለዉን የሥነ-ጥበብ ታሪካዊ ዉጤት እና ትዝታዉን እንዴት ማቆየት ይችላል የሚል መልክትን ያዘለ እንደነበር በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አለ የሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አሻግሪ ገልፀዉልናል።
በሶስቱ ቀን ጉባኤ አዲስ አበባ ላይ የተገኙት በጀርመን የዉጭ ግንኙነት ተቋም የሥነ-ጥበብ ክፍል ኃላፊ፤ ኤልከ አዉስ ዴሞር እንደገለፁት ድርጅታቸዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥነ-ጥበብ ጥበቃ ረገድ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አራት ዓመት ሆኖታል፤
« በዓለም ዙርያ በሚገኙ ከተሞች በሚታየዉ የግንባታ ሥራ ትልቅ ለዉጥ መታየቱን እናዉቃለን፤ በዚህም „ፊቸር ሜሞሪስ“ «የወደፊት ትዉስታ» በሚል ባዘጋጀነዉ ስብሰባ ላይ በከተማ አደባባዮች እና አካባቢዎች ላይ ባህላዊ ሥነ-ጥበባዊ ሥራዎች ምን ያህል ተጠብቀዉ ይታያሉ የሚለዉን ጥቃቄን ለማየት ሞክረናል።»
ገጣሚና በሥነ-ጥበብ ሥራዎችዋ ታዋቂ የሆነችዉ «ጦብያ የፖየቲክ ጃዝ ቡድን» መሥራች ወጣት ምህረት ከበደ፤ የፈረሱም ሆነ ሊፈርሱ ያሉ ታሪካዊና ሥነ-ጥበባዊ የማኅበረሰቡ መገለጫዎችና ኃብቶችን ባለሞያ በማማከር መጠበቅ አለብን ስትል ተናግራለች።
ከተማ ሲገነባ የዚህ ዘመን ትዉልድ አሻራዉን መተዉ ነዉና ፤ ይህንን አሻራ ለወደፊት ለማቆየት ያለፈዉን አሻራ ሳናጠፋ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ አበባ የአፍሪቃ ሕብረት ዋና መቀመጫ እንደመሆንዋ መጠን ለኛም ይህን ዓለማቀፍ ጉባኤ እዚህ ማዘጋጀታችን እጅግ ወሳኝነት አለዉ ሲሉ የገለፁልን፤ የጀርመን የዉጭ ግንኙነት ተቋም የሥነ-ጥበብ ክፍል ኃላፊ ኤልከ አዉስ ዴሞር በበኩላቸዉ፤
« አዲስ አበባ የአፍሪቃዉ ሕብረት ህንፃ ባለበት ይህን ስብሰባ በማካሄዳችን የአፍሪቃዉያንም የተለያየ ሃሳብ አንድ ላይ አናሰባስባለን። ይህ አይነቱ ሁኔታን በጀርመንም ያየነዉ ነዉና፤ የከተማ ልማትና መስፋት እንዴት ነዉ፤ በከተማ ልማት የሥነ-ጥበባት አስተዋፅኦ ምን ይመስላል የሚለዉን ነጥቦች ሁላችንም ከልምድ ተሞክሮአችን እንማማራለን ኃሳብን እንቀያየራለን»
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ « አለ የሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት» ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አሻግሪ እንደገለፁት፤ በተለይ በአዲስ አበባ ባለፉት አስር ዓመታት እጅግ ስር ነቀል በሆነ ፈጣን የግንባታ ሥራ ታይቶአል፤ በዚህም ምክንያት ፤ ታሪክን ባህልን ከማቆየትና ከመጠበቅ አንፃር የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች አስተዋፆ ምን መሆን አለበት ብለን መጠየቅ አለብን ሲሉ ገልፀዋል። አቶ ብርሃኑ፤ የሚያስተዳድሩት ትምህርት ቤት ባለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት ከጀርመን ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ገጣሚ እና ሰዓሊ ምህረት ከበደ በአዲስ አበባ ጎተ-ተቋም በሥነ-ጥበብ እና ባህል ኪነ-ጥበብ ላይ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ለሚያደርገዉ ድጋፍ ምስጋናን አቅርባለች።
የጉባኤዉ አባላት በሶስት ቀኑ ስብሰባቸዉ አዲስ አበባ ዉስጥ፤ ለኢትዮጵያ ከታሪክ ከባህል አንፃር አስፈላጊ ዋንኞቹ ናቸዉ ተብለዉ የተመረጡ አንዳንድ ቦታዎች ዓለም አቀፍ ልምድ ባላቸዉ ተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል፤ ስለ ታሪካዊ ቦታዎቹም ገለፃ ተደርጎላቸዋል። በዝግጅቱ ቃለ- ምልልስ ለሰጡን በጀርመኑ የዉጭ ግንኙነት ተቋም የሥነ-ጥበብ ክፍል ኃላፊ፤ ኤልከ አዉስ ዴሞር፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፤ «አለ የሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት» ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሻግሪን፤ እንዲሁም ገጣሚ ሰዓሊና ምህረት ከበደን በማመስገን፤ ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያዳምጡ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ

Äthiopien Kaiser Menelik II. Denkmal in Addis Abeba
ምስል DW
Internationale Konferenz Future Memories in Addis Abeba
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn
Internationale Konferenz Future Memories in Addis Abeba
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn