1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታሊባኑ መሪ ሞት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 23 2007

ሞታቸው ትናንት ይፋ የተደረገው ሙላህ ኦማር በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ለሚገኙ የታሊባን ተዋጊዎች እንደ አባት የሚታዩ መሪ ነበሩ ። ታሊባንን አንድ አድርገው ያቆዩ ግርማ ሞገስ ያላቸው መሪም ይባላሉ ።

https://p.dw.com/p/1G7g6
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Gul

[No title]

የአማፂው ቡድን የታሊባን መሪ ሙላህ ሞሐመድ ኦማር መሞታቸውን የአፍጋኒስታን ታሊባን ከፍተኛ የአመራር አባላት ዛሬ አረጋገጡ ። የአመራር አባላቱ የታሊባን ምክር ቤት ፣ ባለፉት 3 ዓመታት የኦማር ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትን አክታር ማንሱርን የሙላህ ተተኪ አድርጎ መምረጡንም አስታውቀዋል ። መሞታቸው ትናንት የተነገረው ኦማር ሙላህ የአፍጋኒስታን መንግሥት እንዳለው ካረፉ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል ።
«የታሊባኑ መሪ ሞላህ ኦማር ስለ ማረፉቸው ዘገባዎች መውጣታቸውን እናውቃለን ። እነዚህን ዘገባዎች በማሰባሰብ ላይ ነን ። ተጨማሪ ትክክለኛ መረጃዎችን ወይም ደግሞ ለዘገባዎቹ ማረጋገጫ እንዳገኘን መገናኛ ብዙሃንና የአፍጋኒስታን ህዝብ እንዲያውቀው እናደርጋለን ።»
በህይወት ዘመናቸው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከሶቭየት ህብረት ፣ በኋላም ከሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት NATO ጋር አፍጋኒስታን ውስጥ ማብቂያ ያጣ ውጊያ ሲያካሂዱ ስለቆዩት ስለ ሙላህ ኦማር ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም ።በጎርጎሮሳዊው 1996 ዓም የታሊባን ሚሊሽያዎች የአፍጋኒስታንን ዋና ከተማ ካቡልን ሲቆጣጠሩ የታሊባን መንግሥት መሪ የሆኑት ኦማር እስከለተ ሞታቸው ድረስ ምስጥራዊ ሰው ነበሩ ። ኦማር የትና መቼ እንደተወለዱ የሚጠቁሙ መረጃዎች እንኳን የተለያዩ ናቸው ። ቡድናቸው ታሊባን ባሳተመው የህይወት ታሪካቸው ላይ ኦማር በጎርጎሮሳዊው 1960 አፍጋኒስታን ደቡባዊ ካንደሃር ውስጥ በሚገኘው ካሃክሪዝ በተባለው ቀበሌ መወለዳቸው ሰፍሯል ። በ5 ዓመታቸው አባታቸው ሲሞቱ 2 አጎቶቻቸው ጋር ለማደግ ወደ ሌላዋ ደቡባዊ ክፍለ ሃገር ኡርዝጋን ሄዱ ።በዚህ ቦታም በአካባቢው በሚገኙ መድረሳዎች የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ይከታተሉ ነበር ። ሆኖም ትምህርቱን አቋርጠው በጎርጎሮሳውያኑ በ1979 ሃገራቸውን በወረረችው በሶቭየት ህብረት ላይ የተከፈተውን ውጊያ ተቀላቀሉ ።ሶቭየቶች 1989 ከአፍጋኒስታን ሲወጡ ኦማር በአሜሪካንና በፓኪስታን ሲደገፉ እንደነበሩት እንደሌሎቹ ሙስሊም ተዋጊዎች በሶቭየት ይደገፍ የነበረው የአፍጋኒስታኑን የሞሃመድ ናጂቡላህ መንግሥት እስከወደቀበት እስከ 1992 ተዋግተዋል ።በዚሁ ውጊያም ኦማር ከቀኝ አይናቸው አጡ ። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ አፍጋኒስታን የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ስትገባ ሙጃሂዲኖች ሥልጣን ለመያዝ መገዳደል ጀመሩ ። በዚህ ጊዜ ሙላህ ኦማር ራሳቸውን ከጦርነቱ አግለው በካንደሃር መንደሮች እስልምናን በመስበክ ነበር ያሳለፉት ። በኋላም በ1994 በሃገሪቱ ፖለቲካ መሳተፍ ጀመሩ ። በዚሁ ዓመት 50 በሚሆኑ የመድረሳ ተማሪዎች ታጅበው ከካንደሃር ወደ ሌሎች የአፍጋኒስታን ክፍለ ሃገራት በመሄድ የጦር አበጋዞች ያቋቋሟቸውን ህገ ወጥ ቀረጥ መሰብሰቢያ ኬላዎች በማንሳት የህዝቡን ድጋፍ አገኙ ። በኋላ በሃገሪቱ እየተስፋፋ የሄደው ይህ ታሊባን ንቅናቄ መነሻ እንደሆነ ይነገራል ።ኦማር በኋላም በፓኪስታን ድጋፍ የኦማር ኃይሎች በ1996 ዋና ከተማይቱን ካቡልን ተቆጣጥረው ፕሬዝዳንት ናጂቡላን ከገደሉ በኋላ ሙላህ ኦማር የመሪነቱን ሥልጣን ተረከቡ ።በ1998 ከሃገሪቱ 90 በመቶውን የተቆጣጠሩት የኦማር ኃይሎች በሃገሪቱ የሸሪአ ህግ ደነገጉ ።በዚህ ጊዜም የኦማር አገዛዝ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችንና ጭፍጨፋ በመፈፀም ተከሷል ።በታሊባን አመራር የሴቶች መብቶች የተገደበ ሲሆን አናሳ የህብረተሰብ ክፍሎች ይበደሉ ነበር ።በዚህ ወቅት ነበር አፍጋኒስታን የዓለም ዓቀፉ አሸባሪ ቡድን የአልቃይዳ መሪዎች መሸሸጊያ የሆነችው ።የአልቃይዳ መሪ ኦስማ ቢን ላደን ከኦማር ጋር ቅርብ ግንኙነት የመሰረተው ካንደሃር ውስጥ በኖረበት ወቅት ነው ። ታሊባን ለአልቃይዳ መሪዎች በሚሰጠው ከለላ ከአልቃይዳ የገንዘብ ድጋፍ ያገኝ ነበር ።ቢን ላደን በአሜሪካን መስከረም አንድ 1994 ለደረሱት የሽብር ጥቃቶች ሃላፊነቱን ሲወስድ አሜሪካን ቢን ላደንን አሳልፈው እንዲሰጧት ሙላህ ኦማር ብትጠይቅም ኦማር ጥያቄው ውድቅ አደረጉት ። ይህም አሜሪካን አፍጋኒስታንን እንድትወር ከማብቃቱም በተጨማሪ ከምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር ኦማር ሲያካሂዱ የቆዩት የቀጣዩ ረዥም ጦርነት መነሻም ሆነ ። በአሜሪካን የሚመራው ጦር በ2001 ካቡልን ሲይዝ ኦማር ወደ ፓኪስታን ሸሹ ። እንደሚባለው ኦማር ከፓኪስታን የደህንነት በመስሪያ ቤት ጋር ቅርብ ግንኑነት ነበራቸው ተብሎ ይታመናል ። ፓኪስታን ሆነው በNATO ና በአፍጋኒስታን ኃይሎች ላይ የሽምቅ ውጊያ ያካሂዱ የነበሩትን ኦማር በአፀፋው በአፍጋኒስታን ከኒውዮርኩ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ የህንድን ተፅእኖ ለማስቀረት ታሊባን ለፓኪስታን የውክልና ጦርነት ያካሂድ እንደነበር የስለላ ምንጮች ይናገራሉ ።በአፍጋኒስታን የበርካታ አፍጋናውያንና የአሜሪካን የፀጥታ ኃይሎችን የገደሉ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶችን ሲጥል የቆየው የታሊባን መሪ ሙላህ ኦማር በ2014 በተካሄደው ምርጫ እንዲካፈሉ ቢጋበዙም የውጭ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን እስኪወጡ ድረስ ውጊያ አላቆምም በማለት ጥሪውን አልተቀበሉም ።ታሊባን ካለፈው ዓመት አንስቶ ከአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር የሰላም ንግግር እያካሄደ ነው ።ሞታቸው ትናንት ይፋ የተደረገው ሙላህ ኦማር በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ለሚገኙ የታሊባን ተዋጊዎች እንደ አባት የሚታዩ መሪ ነበሩ ።ታሊባንን አንድ አድርገው ያቆዩ ግርማ ሞገስ ያላቸው መሪም ይባላሉ ።

Gesucht: Mullah Mohammed Omar
ምስል AP
Taliban Afghanistan Terrorismus Islamismus Flash-Galerie
ምስል picture alliance/dpa
Mullah Mohammed Omar 1996
ምስል Getty Images/AFP/BBC NEWS

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ