1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዚያ ፖለቲካዊ ትኩሳት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 9 2005

የቱኒዚያዉ ገዢ ፓርቲ ሊቀመንበር ፖርቲ የሌለዉ መንግስት እንዲመሰረት ከተቃዋሚዎች የሚቀርበዉን ጥሪ እንደማይቀበሉ አስታወቁ። የአናህዳ ፓርቲ ሊቀመንበር ራሺድ ጋኑቺ ግብጽ ዉስጥ የሚታየዉ ሁኔታ ለቱኒዚያ ማስፈራሪያ ሳይሆን የሀገሪቱን ቀዉስ ለመፍታት ፓርቲዎች ወደዉይይት እንዲገቡ የሚጋብዝ መሆኑን ዛሬ አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/19Qdt
ምስል Reuters

ምክትላቸዉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጥያቄ መደገፋቸዉን ይፋ ባደረጉ ማግስት ነዉ የቱኒዚያዉ ገዢ ፓርቲ አናህዳ ሊቀመንበር ራሺድ ጋኑቺ ያለፓርቲ መንግስት የሚለዉን ሃሳቡን ዉድቅ ማድረጋቸዉን የገለጹት። በአንጻሩ ጋኑቺ ሁሉም ፓርቲዎች የሚወከሉበት ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ይቋቋም ቢባሉ እንደሚቀበሉ ነዉ ያመለከቱት። ያ ካልሆነ ግን አሉ፤ ካልሆነ ግን ምክር ቤት ዉስጥ የሚሰባሰቡ ባለሙያዎች ሀገሪቱ ያለችበትን አስጊ ሁኔታ ማስተካከል አይችሉም። መንግስት የቱኒዚያን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ቀዉሶች ለማስተካከል ጊዜ እንደሚያስፈልገዉ በማመልከትም ግብጽ አሁን የገባችበት ሁኔታ እነሱንም ሊስብ እንደማይገባ አሳስበዋል። ቱኒዚያ ዉስጥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የሚናፍቁ ላሏቸዉ ወገኖችም ዳግማዊ አል ሲሲን ቱኒዝ ላይ እናያለን ከሚለዉ ቅዠት እንዲወጡ ጠይቀዋል። እንደዉም ግብጽ የምትገኝበት ዉጥንቅጥ ቱኒዚያዉያን ለዉይይት እንዲቀመጡ የሚገፋፋ ነዉ ብለዉ እንደሚያምኑም ነዉ የተናገሩት።

Rached Ghannouchi Ennahda Partei Tunesien
ራሺድ ጋኑቺምስል REUTERS

የጋኑቺ የዛሬዉ ዉሳኔና ንግግር ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ከተቃዋሚዎችን የሚደግፈዉን በምህጻሩ UGTT ማለትም የቱኒዚያ የሠራተኞች ኅብረት ፌዴሬሽንንም ሳያስቆጣ እንደማይቀር ይገመታል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢዉ አናህዳ ፓርቲ ጋ የሚደራደሩት እስላማዊ መንግስቱን ካፈረሰ በኋላ እንደሚሆን ግልጽ አድርገዋል። በአካባቢዉ ዉጥረት ከተባባሰ በኋላ ቱኒዚያን ለመጎብኘት ከአዉሮጳ የመጀመሪያዉ የሆኑት ባለስልጣን የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ በለዉጥ ጎዳና ላይ ናት ያሏት ቱኒዚያ የግብጽን ፈለግ መከተል እንደማይኖርባት አሳስበዋል።
«ቱኒዚያ ግብጽ አይደለችም። ግብጽ ዉስጥ የተከሰተዉም ቱኒዚያ ዉስጥ መታየት አይኖርበትም። ለዚህም ነዉ እዚህ ያለነዉ እና ሁሉን የሚያካትት አዲስ ነገር እንዲጀመር ለማመቻቸት ነዉ። እኛ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለንም ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ስብስብንም አንፈልግም፤ እኛ ከዴሞክራሲ ወገን ነዉ የምንቆመዉ። ከምንም በላይ ለቱኒዚያ ሕዝብ የወደፊት መልካም የማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ እጣ ፈንታ ነዉ የቆምነዉ።»
አያይዘዉም ቬስተርቬለ ለቱኒዚያ ወቅታዊና ፖለቲካዊ ቀዉስ መፍትሄዉ ዉይይት ብቻ እንደሆነም አሳስበዋል። ራሺድ ጋኑቺ ኢናህዳ ፓርቲ የሚመራዉ መንግስት ለአረቡ ዓለም ሕዝባዊ አብዮት መገኛ መሆኑን ቢጠቅሱም በሀገሪቱ ያለዉን የኤኮኖሚ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ማሻሻል እንዳልተሳካለት ያምናሉ። ሮይተርስ እንደጠቀሰዉም «ስህተቶች ሰርተናል ግን መፈንቅለ መንግስት ሊደረግብን አይገባም» ነዉ ያሉት።

Tunesien / Tunis / Großdemonstration / Protest gegen Regierung
ምስል Reuters

መንግስትን በመቃወም ቱኒዝ ጎዳና ላይ ከወጡት ወጣቶች መካከል የ24ዓመቷ ሳራ አሁን ምርጫ ቢካሄድ ኤናህዳ በዜሮ ይሸኝ ነበር ትላለች፤
«አናህዳ አንድ ሶስተኛዉን ድምጽ ነበር ያገኘዉ፤ ያ ማለት ግን ቱኒዚያዉያን እነሱን ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። ከአንድ ዓመት በኋላ ህዝቡ ስልጣን እንዲለቁ ይፈልጋል። አሁን የመምረጥ እድል ቢሰጠን አናህዳ ሊሳካለት አይችልም።»
ሳራ ለሰልፍ የወጣችዉ መፈክር ካነገቡ መሰል ሴት ጓዶቿ ጎን ነዉ። አናህዳ ፓርቲ መሪነት ቱኒዚያ ለሴቶች ያሻሻለዉ የመብት ይዞታ ሁኔታ የለም። ይህና ሌላዉ ችግርና ቀዉስ ተዳምሮም አናህዳ ፓርቲ ስልጣን እንዲለቅ ግፊት እየተደረገበት ነዉ።
ከግብጽ ጋ ሲነጻጸር የቱኒዚያ ጦር ኃይል በኤኮኖሚዉ ያን ያህል ድርሻ የሌለዉና በልማዱም ፖለቲካ ዉስጥ ጣልቃ የማይገባ አይነት ነዉ። ጥቂት ታዛቢዎች ግን አሁንም ጦር ኃይሉ ቀዉሱን ለመፍታት እጁን ፖለቲካዉ ዉስጥ ይከታል ባዮች ናቸዉ። ከሃይማኖት ባለመወገን የምታወቀዉ ሀገር ቱኒዚያ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች።

ሸዋዬ ለገሰ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ