1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዚያ የሀገር ጉብኚዎች ቁጥር መቀነስ

ረቡዕ፣ የካቲት 26 2006

በአለማችን የሚገኙ የተለያዩ ሀገራትን ማየት፣ አዲስ ባህልን የማወቅ ፍላጎት፤ ምኞት ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች እውን እየሆነ መጥቷል።

https://p.dw.com/p/1BK32
Festival Dunes Electroniques in Tunesien
ምስል DW/S. Mersch

የቻይና የህንድ እና የሩሲያ ሀገር ጎብኚዎች መበራከት ባለፈው ዓመት ብቻ የሀገር ጎብኚዎቹን ቁጥር ወደ 1,1 ቢሊዮን ከፍ እንዳደረገው ይነገራል። የዓለም የቱሪዝም ድርጅት እንደውም በጥቂት አመታት ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 1,4 እና 1,5 ቢሊዮን ከፍ ሊል እንደሚችል ይገልፃል። ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ጀርመኖች ለዚህ ቁጥር መጨመር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ባለፈው የጎርጎሮሲያኑ 2013 ዓ ም ብቻ ጀርመኖች ከ65 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ለሀገር ጉብኝት እንዳወጡ መዘርዝሮች ያመላክታሉ። እንደ ግብፅ እና ቱኒዚያ ያሉ ሀገራት ጀርመኖች ከአፍሪቃ የሚያዘወትሯቸው የዕረፍት ማሳለፊያ ቦታዎች ናቸው። ይሁንና በነዚህ ሁለት ሀገራት አብዮት ከተካሄደ በኃላ በአጠቃላይ ወደነዚህ ሀገራት የሚጓዙት የሀገር ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ።

Tunesische Tourismusministerin Amel Karboul
ሚኒስትር አሜል ካርቡልምስል DW/S. Mersch

በቱኒዚያ ትንሽ ከተማ ኔፍታ እና አልጄሪያ ድንበር አጠገብ «ኦንግ ጄማል» ወይም የግመል ጀርባ በሚል መጠሪያው የሚታወቅ አንድ የአሸዋ ክምር ይገኛል። በተለይ ለ«ስታር ዋርስ» ፊልም አፍቃሪዎች ይህ ስፍራ እንግዳ አይደለም። እዚሁ ስፍራ የተቀረፁ የፊልሙ ክፍሎች አሉ። በዚሁ የካቲት ወር የአንዱ የሳምንት መጨረሻም በስፍራው በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተሰብስበው ከቀን እስከ እኩለ ሌሊት በተለያዩ የዓለም አቀፍ የቴክኖ ሙዚቃዎች ይጨፍራሉ። « እናንተ ቱኒዚያን እስካልቀየራችኃት ድረስ ምንም የሚቀየር ነገር የለም» በማለት አሜል ካርቡል ለታዳሚዎቹ ይገልጿሉ። ታዳሚዎቹም ደስታቸውን የሚመልሱት በጩኸት ነው። በአረብኛ ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ እያፈራረቁ የሚናገሩት ካርቡል አስተዋዋቂ ወይም ቀልደኛ አይደሉም፤ ይልቁንስ በአካባቢው ያለውን የሀገር ጎብኚዎች ቁጥር መልሶ እንዲያንሰራራ ለመተባበር ወደ ደቡብ ቱኒዚያ የተጓዙ ሚኒስትር ናቸው። የ40 ዓመቷ ኢንጂነር ከአንድ ወር በፊት ሚኒስትር ሆነው ስልጣን ከመጨበጣቸው በፊት በስራ አመራር አሰልጣኝነት ያገለግሉ ነበር። ህዝቡ ሚኒስትሯን ጥሩ ተቀብሏቸዋል። ይሁንና ከቱኒዚያ ሁለት ሴት ሚኒስትሮች አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ብዙ ይጠበቅባቸዋል። ካርቡል ጀርመን ሀገር ነው የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት፣ በዚሁ ጀርመን ሀገር ትዳር መስርተው ልጆች አፍርተዋል። አሁን ግን ወይዘርዋ ወደ ቀድሞው የትውልድ ሀገራቸው ቱኒዚያ ተመልሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሜህዲ ጆማ ናቸው ባለፈው ጥር ወር በጊዜያዊው መንግሥት አንድ የሚኒስትርነት ቦታ ይይዙ እንደው ወይዘሮዋን የጠየቋቸው።

« አንድም ሆነ ሁለት ወይም ሶስት ሳምንት ብሰራ እቅዴ የረዥም ጊዜ ነው» ወይዘርዋ ቱኒዚያን ከሀገር ጎብኚዎች ቀውስ ለማውጣት እቅድ ይዘው ተነስተዋል።ይሁንና ችሎታቸውን ለማሳመን ካርቡል ብዙ ጊዜ የላቸውም። የያዝነው የጎርጎሬሲያኑ 2014 ዓም ሳያልቅ በሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ይካሄዳል።

የሕዝባዊ አብዮት በጀመረባት ቱኒዚያ፤ የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ቤን አሊ ከስልጣን ከተወገዱ እጎአ ከ2011 አንስቶ የሀገሪቱ ጎብኚዎች ቁጥር በጣም ቀንሷል። ከአቢዮቱ በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ60 በመቶ የቀነሰበት ወቅትም አለ። ለምን የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ሚኒስትሯ የሀገር ጎብኚዎቹን ውሳኔ ብዙም አይረዱትም። ከአብዮቱ በኋላ ትልቁ ርዕስ የደህንነት ጉዳይ ነበር። እስካሁን ማንም የውጭ ሀገር ዜጋ ላይ ጥቃት አልደረሰም። ነገር ግን ሊቢያ እና ግብፅ ብዙ ጥቃት ስለደረሰ ሰዎቹ በሙሉ አካባቢውን ጨርሶ ለመጎብኘት አያስቡትም። ይህ ለኔ ሰሜን አየርላንድ አንድ ቦንብ ስለፈነዳ ኢጣሊያን ለመጎብኘት አልሄድም እንደማለት ነው።»

ሌላም መሰረታዊ ችግር አለ። በ60ዎቹ እና 70ቹ በውሃው ዳርቻ የተገነቡት የማደሪያ ቤቶች ብዙም የሀገሪቷን ባህል እና አኗኗር የሚያንፀባርቁ አይደሉም። ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሆቴሎች እድሳት ይሻሉ። አንድ ሰው እንዴት በርካሽ ዋጋ አፍሪቃ ውስጥ ውሃ ዳር እረፍት ለማድረግ መሄድ ያዋጣኛል ብሎ ቢያስብ በቀዳሚነት የሚያገኘው ቱኒዚያን ነው። አሜል ካርቡል ይህንን ገፅታ ቀይረው አዲስ ደንበኞችን የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ነው ፍላጎታቸው።

historische Altstadt der tunesischen Stadt Tozeur
ታሪካዊ ከተማምስል DW/S. Mersch

« በመጀመሪያ የቱኒዚያ ገፅታ ነው። ምክንያቱም የአሁኑ ዘመን ቱሪስት የሚያዘወትረው ቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ የሚሀኙ ሆቴሎችን ነው። እኛ ግን ብዙ ባህላዊ እና ታሪካዊ ህንፃዎችም አሉን። ይህ ብቻ አይደለም ቁሳቁስ ያልሆነ እንደ ሙዚቃ እና ስነ ፁሁፍ አሉን። ነገር ግን ስለነዚህ ነገሮች በበቂ ሁኔታ አናወራም።» ቤርትራንድ ለሙዚቃው ምሽት ሲል ነው ከካሜሮን ወደ አሸዋማው የሳህራ በርሃ የተጓዘው። ቱኒዙያዊ ጓደኞች አሉት።

« በጣም ነው የተገረምኩት። ካለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ በየአመቱ ወደ ቱኒዚያ እመጣለሁ። እንደዚህ አይነት ግን አይቼ አላውቅም። » ሽቴፈን ደግሞ ፈረንሳያዊ ነው። ሙዚቃው በደስታ ውጦታል።

« እጅግ አስደናቂ ነው። አዎ እንደዛ ነው ማለት የሚቻለው። ብዙ ጠብቀን ነበር። የጠበቅነውም ሁሉ አግኝተናል። ወደዚህ ስለመጣን በጣም ደስተኞች ነን። የስታር ዋርስ ድንኳን በጣም ያምራል። ሙዚቃው አሪፍ ነው። ሆቴላችንም እንደዚሁ።»

እንደዚህ አይነት የሙዚቃ ድግሶች ብዙ የሀገር ጎንኚዎች የነበሯትን ቱኒዚያን ስም መልሰው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለማስጠራት ይረዳሉ። አልጄሪያ ድንበር አጠገብ በምትገኘው የሀገሪቷ የደቡብ ከተማ በተካሄደው የሙዚቃ ድግስ ላይ 10ሺ ታዳሚዎች እንደነበሩ ነው የተገለፀው።የሀገሬውም ህዝብ ቢሆን ከተማው መልሶ ነፍስ ስለዘራ ደስተኛ ነው። ከቴምር ምርት ቀጥሎ በዚህ አካባቢ ያለው ገበያ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ ናቸው። ከአቢዮቱ በኋላ በሀገር ጎብኚዎች መመንመን ምክንያት በቶዜሬ እና ኔፍታ ብቻ 13 ሆቴሎች ተዘግተዋል። ሴልሚ ቾክሪ በሀገሪቷ በኪሳራ ተውጠው ካልተዘጉ ጥቂት ሆቴሎች የአንዱ ሆቴል ኃላፊ ናቸው።በተለይ በዚህ ሳምንት መጨረሻ እጅግ ደስ ብሏቸዋል። ሆቴላቸው ያሉት 300 ማደሪያ ክፍሎች ሙሉ ናቸው። የዛሬ ዓመቱን ቁጥር መለስ ብለው ሲያስቡ በሆቴላቸው የተስተናገደው ቁጥር 30 ቢሆን ነው። « የሙዚቃ ድግሱ እና አዲሷ ሚኒስትር የሚመሰገኑ ናቸው። እንዲሁም ያለው የፖለቲካ ለውጥ ማለትም የአነሕዳ ፓርቲ ለአዲሱ መንግሥት ስልጣኑን ካስረከበ በኋላ የቱኒዚያ የሀገር ጎብኚ ቤተሰቦች ባለ ሙሉ ተስፋ ናቸው»

Tourismus Tunesien Protest
ስራ ያጡት የቱኒዚያ የሆቴል ሰራተኞችምስል DW/S. Mersch

ቾክሪ ብዙም ሳይቆዩ ግን ስለችግራቸው መናገር ቀጠሉ። «የፋይናንስ ችግር አለብን። ለሰራተኞቹ ዋስትና መክፈል አለብን። የመብራት ክፍያ አለ። ወጪያችን ከፍተኛ ነው። ከአቅማችን በላይ ነው። ቀውሱ ያስከተለው እስካሁን ጎድቶናል።»

በትንሻ ከተማ አንድ የተዘጋ ሆቴል ፊት ለፊት ወንዶች ተቀምጠዋል። 57 የሆቴሉ ሰራተኞች ያለ ስራ ከተቀመጡ ሁለት ወር አለፋቸው። የሆቴሉ ባለቤት የት እንደደረሰ አይታወቅም። ውጪ ተሰብስበው እየተቀመጡ ያለውን ሁኔታ ለሌሎች ማሳወቅ ይፈልጋሉ። ከነዚሁ ከስራ ከተፈናቀሉት አንዱ የሆኑት አብደልባኪ ምንም ስራ የማግኘት ተስፋ እንደማይታያቸው በጀርመንኛ ይገልጿሉ። « 47 ዓመቴ ነው። በሀገር ጉብኝት መስክ ስሰራ 25 ዓመት ሆነኝ። ምንም ስራ ላገኝ አልቻልኩም። ምን ላድርግ? አራት ልጆች አሉኝ። አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው።»

5000 ነዋሪ ባላት ትንሽ ከተማ የሆቴሉ ሰራተኛ ብዙም ተስፋ አይታያቸውም። ይልቁንስ በአሁን ሰዓት እንደ አማራጭ የሚያዩት ወደ አልጄሪያ መሰደድን ነው። አብደልባኪ እንደሚሉት እሳቸውና ባልደረቦቻቸው በግማሽ ክፍያ ሁሉ ለመስራት ስራ ጠይቀው ነበር። ነገር ግን የሆቴሉ ባለቤት ያንን እንኳን መክፈል እንደማይችል ነው የነገራቸው። አብደልባኪ እና ሌሎች በዚህ የስራ መስክ የተሰማሩ ሰራተኞች ያላቸው አማራጭ ጥሩ ቀን እስኪወጣላቸው መታገስ ብቻ ነው።

ሳራ ሜርሽ

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ