1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርካና ሃይቅ የዉሃ  መጠን ቀነሰ ተባለ።

ረቡዕ፣ የካቲት 8 2009

በኬንያ የሚገኘዉ የቱርካና ሃይቅ የዉሃ  መጠን  በ1ነጥብ5 ሜትር ቀነሰ ተባለ። የሀይቁ የዉሃ መጠን መቀነስ ለአካባቢዉ ህዝቦች ስጋት ደቅኗል ሲል ለሰዉ ልጆች መብት የሚሟገተዉ ሂዉማን ራይትስዎች የተባለዉ ድርጅት ገልጿል።    

https://p.dw.com/p/2Xd3J
Äthiopien Omo Fluss Tal Landschaft
ምስል JENNY VAUGHAN/AFP/GettyImages

Impacts of Omo River Dams on Indigenous Peoples - MP3-Stereo


   
ኢትዮጵያ በኦሞ ሸለቆ አካባቢ የምታካሂዳቸዉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀግቶች ለሃይቁ የዉኃ መጠን መቀነስ ምክንያቶች ናቸዉ ሲል ድርጅቱ  አመልክቷል።  
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የድርጅቱ ዘገባ የሃገሪቱን ልማት ካለመቀበል የመጣ ነዉ ሲል አጣጥሎታል። 
በኬንያ ሰሜናዊ ስምጥ ሸለቆ ክፍል የሚገኘዉ የቱርካና ሃይቅ የዉኃ መጠኑ እየቀነሰ ነዉ ተብሎአል። ለሰዉልጆች መብት የሚሟገተዉ ሂዉማን ራይትስ ዎች የተባለዉ ድርጅት ሰሞኑን  ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉ የቱርካና ሃይቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት 1ነጥብ 5 ሜትር የዉሃ መጠኑ ቀንሷል ብሏል። ሃይቁ 90 በመቶ  የሚሆነዉን የዉሃ መጠን የሚያኘዉ በኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚገኘዉ የኦሞ ወንዝ ሲሆን በዚህ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸዉ የሸንኮራ አገዳ፣ የጥጥ እርሻወችና  የግድብን የመሳሰሉ   የልማት ፕቶጀክቶች ለሃይቁ ዉሃ መጠን መቀነስ ምክንያቶች ናቸዉ ሲል ድርጅቱ ገልጿል። ከ2014 በፊት በዉኃ ይሸፈን የነበረዉ የሃይቁ የጠረፍ ዳርቻ በአሁኑ ወቅት  1 ነጥብ 7 ኪሎሚትር  የሚሆነዉ ክፍል ዉሃ አልባ መሆኑ ተገልጿል።  በተለይም በጎርጎረሳዊ የዘመን ቀመር በታህሳስ 2016 የተገነባዉ የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ ለሃይቁ ዉሃ መቀነስ በእጅጉ አስተዋጽኦ አድርጓል  ሲሉ በድርጅቱ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳዮች ዋና አጥኝ ፊሊክስ ሆርን ገልፀዋል። 
«ታዉቃላችሁ የግልገል ጊቤ 3 ግድብ ከፍተኛ የዉሃ መጠን የሚፈልግ የመጀመሪና አሳሳቢ የልማት ፕሮጀክት ነዉ።የሸንኮራ አገዳና የጥጥ እርሻወች እንዲሁም ልሎች ተጨማሪ ግድቦችም እንዲሁ፤በመሆኑም ህይወታቸዉ በቱርካና ሀይቅ ጋር የተቆራኘዉን የሀገሬዉን ህዝብ ስጋት ላይ ይጥላል።»
 ስለሆነም የዉሃና የግጦሽ መሬትን የመሳሰሉ የተፈጥቶ ሃብቶች መቀነስ ህይወታቸዉ ከሃይቁ ጋር በእጅጉ ለተቆራኙ ከኦሞ ወንዝ በታች ለሚኖሩ 500 ሺህ በላይ ሰዎች ስጋት ደቅኗል ሲል ድርጅቱ ገልፆአል። በሃይቁ ላይ የአሳ ማስገርና በደለል አካባቢ የእርሻ ስራ የሚከናዉኑ ገበሬዎችም ቤተሰቦቻቸዉን ለመመገብ ይቸገራሉ ሲሉ አጥኚዉ ተናግረዋል።
«በቱርካና ሀይቅ አካባቢ የሚገኙ የሀገሬዉ ሰወች ቤተሰቦቻቸዉን ለመመገብ የአሳ ማስገር ስራ ይሰራሉ።በሚካሄዱት ልማቶች ምክንያት ሀይቁ የሚጠበቀዉን ያህል ካልሆነና ከቀነሰ የአሳ ማስገር ስራ ያከትማል።እናም በቱርካና ሀይቅ አካባቢ የሚኖሩ የሀገሬዉ ሰወች ለቤተሰቦቻቸዉ  ምግብ ማቅረብ አይችሉም።»
ከኦሞ ወንዝ በታች ለሚኖሩ ህዝቦች ስጋት የቱርካና ሃይቅ የዉሃ መጠን መቀነስ ባሻገር  የአየር ንብረት ለዉጥም ሌላዉ ፈተና መሆኑን ድርጅቱ አመልክቶአል።
ዘገባዉን በተመለከተ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መሃመድ ሰኢድ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እንደሃገር የመልማት መብት እንዳላት ጠቁመዉ ፤ በኦሞ ወንዝ ላይ የሚካሄዱ የልማት ስራወች ጎረቤቶቻችንን የማይጎዳና የሌሎችንም ጥቅም በሚከብር መልኩ እየተካሄደ ነዉ ብለዋል። የድርጅቱ ዘገባ የሃገሪቱን ልማት ካለመቀበል የመጣ ነዉ ሲሉ አጣጥለዉታል። 
«አጠቃላይ የልማት ስራወቻችን ግድቦችን ጨምሮ የስኳርና የጥጥ ፕሮጀክቶቻችንን ሌሎችንም ልናነሳ እንችላለን በጥናት ላይ የተመሰረቱ ስራወች ናቸዉ። በዚህ ረገድ የጎረቤቶቻችንን  ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ይልቁንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ነዉ የmrንንቀሳቀሰዉ።ሂዉማን ራይትስ ወችና ሌሎችም ከዚህ ጋር በተገናኘ ለአመታት ሪፓርቶች ከአየር ንብረት ጋር በተገናኘሲያወጡ የነበረበት ሁኔታ አለ። አሁን ደግሞ የቱርካና ሀይቅ ቀነሰ በሚል የሚነሳበት ሁኔታ አለ። የድርጅቱ ሪፓርቱ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በመጠቀም የመልማት አቅማችንን ያለመቀበል ዝንባሌ የወለደዉ ነዉ።»
ፊሊክስ ሆርን በበኩላቸዉ ልማት ተገቢና አስፈላጊ ቢሆንም በአካባቢዉ ያሉ ህዝቦችን የምግብ ዋስትና ፍላጎት ማክበር ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
በመጭዉ ጊዜ 2200 ሜጋ ዋት የሚያመንጭ እና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የግልገል ጊቤ አራትና ሌላም ተጨማሪ 5ተኛ ግድብ በኦሞ ወንዝ ላይ ለመገንባት በኢትዮጵያ በኩል እቅድ ተይዟል። የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ግን ግድቦቹ ሙሉ በሙሌu ተግባራዊ ሲሆኑ የቱርካና ወንዝ 20 ሜትር ያህል ይቀንሳል መባሉ በእጅጉ አሳስቦኛል ብሎአል።  

Äthiopien Omo Fluss Tal Landschaft Staudamm Gibe III
ምስል JENNY VAUGHAN/AFP/GettyImages

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ