1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተጠፋፉ ስደተኞችን የሚያገናኘዉ ዓለም አቀፉ መረብ

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2009

በጦርነትና ድህነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሻለ ኑሮን ለማግኘት የትዉልድ ሃገራቸዉን ጥለዉ ይሰደዳሉ። በስደት ምክንያትም አብዛኞቹ ሰዎች ከሚወድዋቸዉ ቤተሰቦቻቸዉ ይለያያሉ።«REFUNITE» የተሰኘዉ ድርጅት በዘረጋዉ መረብ  የተጠፋፉ ሰዎችን በማገኛኘት ርዳታ ይሰጣል። 

https://p.dw.com/p/2YmO7

Die Organisation 'REFUNITE', die Flüchtlingen hilft, ihre Familien wiederzufinde - MP3-Stereo

 

የሶማልያን ጦርነት ሽሽት በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ዓ,ም  የተሰደደዉ የ 47 ዓመቱ ጎልማሳ አብዲ በወቅቱ  በሶማልያ የሚንቀሳቀሰዉ ሚሊሽያ ቡድን አፍኖ ይወስደኛል የሚል ፍርሃት  ነበረበት። ዋና መስርያ ቤቱ ኬንያ በሚገኘዉ የንግድ ድርጅት ዉስጥ ይሰራ የነበረዉ አብዲ በዓለም እጅግ ግዙፍ ወደሚባለዉና ዳዳብ ኬንያ ወደሚገኘዉ የስደተኞች ጣብያ ተሰደደ።

አብዲ ከአባቱ ከወንድሞቹ፤ ከወንድሞቹ ልጆች በአጠቃላይ ከ24 የቤተሰቡ አባላት ጋር በመሆን  የሶማልያን ጦርነት ሸሽተዉ ሲሰደዱ በመንገድ ላይ ተጠፋፍተዋል። አብዲ ቤተሰቦቹን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ቢጥርም አልተሳካለትም። «REFUNITE» በተሰኘዉ ድርጅት በሚሰጠዉ የሰዎች ማገናኛ የኢንተርኔት መረብ አገልግሎት በኩል ቤተሰቦችህን ማግኘት ትችላለህ ተብሎ ቢነገረዉም ፤ መረቡን በመጠቀም አገኛቸዋለሁ የሚል እምነት አላደረበትም።   

« በአንድ ሌላ የማገኛኛ ድርጅት በኩል ቤተሰቦቼን ለማግኘት ሞክሪያለሁ። አሁን ደግሞ አንዱ ሌላ የተጠፋፉን የሚያገናኝ ድርጅት አለ ሲል ነገረኝ። ቤተሰቦቼን ልታገናኘን አትችልም ስል ነዉ የመለስኩለት። ነገሩ እንዴት እንደሚሰራ በደንብ አስረድቶኛል ። እኔ ግን ብዙም ስላላመንኩበት፤ ጉዳዬ ብዬ በደንብ አላዳመጥኩትም።  ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ ስልኬ ላይ ከ«REFUNITE» አንድ መልክት አገኘሁ።»

በዓለማችን ወደ 65,3 ሚሊዮን ሰዎች ሳይወዱ ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት «UNHCR» ያወጣዉ መረጃ ያሳያል። ከነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ ከ 50 % በላይ የተሰደዱት ከተለያዩ የአፍሪቃ እና ከመካከለኛዉ ምስራቅ ሃገራት ነዉ።ብዙዎቹ በስደት ወቅት የቤተሰብ አባሎቻቸዉ ጋር ተለያይተዋል። 

 «REFUNITE» ሰዎችን የሚያገናኘዉ የአጭር መልክቶችን በመላክያዉ SMS አልያም «USSD» በተሰኘዉ የመገናኛ መረብ መሆኑን የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢዳ ጄንግ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ይህ የተጠፋፉ ሰዎችን የሚያገኛነዉ የኢንተርኔት መረብ የተመሰረተዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ዓ,ም ዴቪድ እና ክሪስቶፈር በተባሉ ሁለት ወንድማማች የዴንማርክ ዜጎች ሲሆን  እነዚህ ወንድማማቾች ከቤተሰቡ ያገኛኙት የአፍጋኒስታን ዜጋ አሁን «ኤሪክሰን» ከተሰኘ የስልክ ኩባንያ ድጋፍ በማግኘት በዓለም ዙርያ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመርዳት የመገናኛ መረብ በመገንባት ላይ ይገኛል።

Menschen nutzen die REFUNITE-App
ምስል REFUNITE app

በስማርት ስልኮች አገልግሎትን የሚሰጠዉ «REFUNITE» የተሰኘዉ የመገናኛ መረብ አጭር የጽሑፍ መልክቶችን እና በሃገር ዉስጥ የቀጥታ የስልክ ግንኙነት አገልግሎቶችን ይሰጣል። «REFUNITE» የመገናኛ መረብ ድርጅት ዉስጥ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ያለ ምንም የኢንተርኔት አገልግሎት መመዝገባቸዉን የድርጅቱ ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ኢዳ ጄንግ ገልፀዋል። ለምሳሌ በኬንያ ዳዳብ በሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ዉስጥ ስደተኞች በማንኛዉም አይነት የተንቀሳቃሽ ስልክ «USSD» በተሰኘዉ  የመልክት ማስተላለፍያ መረብ አግልግሎት ማግኘት ይችላሉ። በምስራቅ አፍሪቃ «SMS» እና «USSD» የተሰኘዉን የግልጋሎት መረብ በመጠቀም በተለይ በስልክ ክፍያ አገልግሎት የሰፋ ሆኖ ይታያል።        

በዓለም ዙርያ ከሚገኙ የስልክ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ጋር የሚሰራዉ «REFUNITE» የተሰኘዉ የመገናኛ መረብ የተጠፋፉ ቤተሰቦች የሚገኛኑበት የነጻ መስመር ለመዘርጋት እየሰራም መሆኑ ተጠቅሶአል ። እንደ ኢራቅ፤ ሶማልያ፤ ኬንያ እና ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ባሉ ሃገራት ዉስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች የጠፉ የቤተሰብ አባላትን የአጭር የጽሑፍ አገልግሎት ማለት «SMS»  እንዲሁም «USSD» የተሰኘዉን ፕላትፎርም ማለትም የመረጃ መድረክን በመጠቀም የስልክ አገልግሎትን መጠቀም ይችላሉ።  «REFUNITE» መረብ የኢንተርኔት መረብ ማለት «web» ን በመጠቀም በመላዉ ዓለም ግልጋሎት ማግኘት ይቻላል። ነጻ አገልግሎትን ለማግኘት «REFUNITE» በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ፊስቡክ ጋር እየሰራ መሆኑን የድርጅቱ ኮሚኒኬሽን ዋና ተጠሪ ኢዳ ጄንግ ተናግረዋል።

በሶማልያ በኮንጎ እንዲሁም በፓኪስታን የሚገኙ ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ሰዎች  «REFUNITE» አጠቃቀም ላይ ችግር ደቅኖባቸዋል። በሌላ አካባቢዎች መረቡን ለመጠቀም ክፍያ በማስጠየቁ ፤ ለምግብ እና ለመኖርያ ገንዘባቸዉን መቆጠብ ያለባቸዉ ስደተኞች ነገሩ አጠያያቂ ሆኖባቸዋል።

«REFUNITE» የተሰኘዉ የመገናኛ መረብ ማንበብ እና መፃፍ የማይችሉ ሰዎች መጠቀም እንዲችሉ ድምፅን በመጠቀም ብቻ በመረቡ ግልጋሎት ማግኘት እንዲችሉ ድርጅቱ እየሰራ መሆኑም ተመልክቶአል።

 

አዜብ ታደሰ / ማናሲ ጎፓላክሪሽናን

ነጋሽ መሃመድ