1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባባሰው የዩክሬን ቀውስ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2006

የዩክሬን ግጭት ከምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል ወደ ደቡብም ተስፋፍቷል።በተለያዩ ከተሞች በተከሰቱ ግጭቶች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ ነው ።

https://p.dw.com/p/1Buk5
Bildergalerie Ostukraine 06.05.2014 Slowjansk
ምስል Vasily Maximov/AFP/Getty Images

የዩክሬን ግጭት ከተገመተው በላይ እየተባባሰ እየተወሳሰበና እየከፋ ቀጥሏል ። ሃገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ርስ በርስ ጦርነቷ የማማራቷ ስጋት ጨምሯል ። የኬቭ መንግሥት ኃይሎች ምሥራቃዊውን የሃገሪቱን ክፍል መቆጣጠር የቻሉ አይመስልም ። ለሩስያ የሚወግኑ ኃይሎች ይዞታቸውን በማጠናከር በነርሱ ላይ ከዘመተው የመንግሥት ጦር ጋር መጋጨታቸው ተባብሷል ። ከሁለቱም ወገኖች በኩል በግጭቱ የሚሞተው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ። ትናንት በምሥራቃዊቷ ከተማ በስሎቭያንስክ በደረሰ ግጭት ቢያንስ 34 በላይ ከሩስያ ጋር መቀላቀል እንፈልጋለን የሚሉ ኃይሎች መገደላቸውን መንግስት አስታውቋል ። አማፅያኑም በስሎቭዪንስክ ተዋጊዎቻቸው መገደላቸውን እንዳመኑ የሚገልፅ መግለጫ ነው የሰጡት ።

«ወደ ውስጥ ከገቡት ከ25 ቱ 5 ቱ ብቻ ናቸው ተመልሰው የወጡት ። ተከበብን፤ ከበባውንም አጠናከሩት ። ከፊት ከግራም ከቀኝም ይመጡ ነበር ። ወደ ኋላ ስናፈገፍግ ከኋላችንም ከበበቡን »

መንግስት እንደሚለው ከሚወጉት ውስጥ ከሩስያ ከቼችንያና ከክሪሚያ የመጡ ተዋጊዎች ይገኙበታል።

በውጊያው አራት ወታደሮች መገደላቸውን 20 ደግሞ መቁሰላቸውን መንግሥት አስታውቋል ። ከዚህ ሌላ አማፅያኑ አንድ ተጨማሪ ሂሊኮፕተርም መጥተው ጥለዋል ። አማፅያኑ ከከ4 ቀናት በፊትም ሁለት ሄሊኮፕተሮችን መጣላቸው ይታወሳል ። የዩክሬን ጦር በስሎቭያንስክ ፀረ ሽብር ያለውን የመከላከል እርምጃ በጀመረበት ባለፈው አርብም ቢያንስ 9 ሰዎች ተገድለዋል ። ከመካከላቸው ሁለት የውጊያ ሄሊኮፕተሮች ከምድር ወደ ሰማይ በሚምዘገዘጉ ሚሳይሎች ተመተው ሲወድቁ የተገደሉት ሁለት ወታደሮች ይገኙበታል ። ከአማፅያኑ እርምጃ በስተጀርባ የሩስያ እጅ በሰፊው እንዳለበት ሲነገር የከረመና አሁን በተደጋጋሚ የሚነገር ጉዳይ ነው ። ሃይንሪሽ በል የተባለው ድርጅት የክየቭ ቢሮ ሃላፊ ኪሪል ሳቪን ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየትም አሁንም በዩክሬን የሚሆነውን ሁሉ የምትዘውረው ሩስያ ናት ።

Bildergalerie Ostukraine 06.05.2014 Kramatorsk
ምስል Genya Savilov/AFP/Getty Images

« እዚህ ዩክሬን እስከምናውቀው ድረስ ፑቲን ሁሉንም ነገር እየዘወሩ ነው ። ከነዚህ ኃይሎች መካከል የሩስያ የደህንነት ድርጅት ባልደረቦች መሣሪያ የታጠቁ ልዩ ስልጠና የወሰዱ እኩይ ተግባር የሚፈፅሙ ኃይሎች ይገኙበታል ። ግን ቁጥራቸው ብዙ የሚባል አይደለም ። ምናልባት በአጠቃላይ 200 ቢሆኑ ነው ። በክሬምሊን ቁጥጥር ስር ያሉና የተደረጁ ኃይሎች ናቸው ። ግን ብቻቸውን አይደሉም ለገንዘብም ይሁን ወይም አምነውበት አለያም በሁለቱም ምክንያት በዚህ ግጭት የሚካፈሉ በአካባቢው የሚኖሩ ወንጀለኞችም አሉ ። ከዚህ በተጨማሪም ከሩስያ ጋር መሆን የሚፈልጉም ይገኙበታል ። »

እነዚህን የመሳሰሉት ክሶችች ተጨባጭ ማረጋገጫ አልተገኘላቸውም ሲባሉ ቢቆይም ከሳምንታት አንስቶ የሩስያ ወታደሮች ዩክሬን ውስጥ እendalu የሚጠቁሙ መረጃዎች ተገኝተዋል እየተባለ ነው ።

ሳቪን በዶኔትስክ ተፈፀሟል ለሚሉት ለዚህ ድርጊት ማረጋገጫዎ ምንድነው ተብለውም ተጠይቀው ነበር ።

«አማፅያኑና የሩስያ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተለዋወጧቸው በርካታ በኢንተርኔት የተለቀቁ ንግግሮችን የመሳሰሉ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ ።ለምሳሌ የሩስያ የደህንነት ድርጅት ሰዎች በስሎቭያንስክና በሌሎችም ከተሞች ግልፅ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ተሰምቷል ። በደንብ የሚታወቁትና በጣም ግልፅ ሆነው የሚናገሩት ከሩስያ የሚመጡት ተንኳሾችን ንግግር የሚያሳይ የቪድዮ ማስረጃም አለ ። ለኔ አንድ ነገር ግልፅ ነው ። የሩስያ ኃይሎች በዶንቴስክ ባይኖሩ ኖሮ ትልቅ ረብሻ አይፈጠርም ነበር ። ሰዉ እንዲሁ በዝምታ ለኬቭ መንግሥት ያለውን ጥላቻ ይገልፅ ነበር ። ሰዎቹ በመንግሥትም ደስተኛ ስላይደሉ በሩስያም ፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ ተፅእኖ ስለተደረገባቸው ግጭትም ሆነ የሰዎች ግድያ አይደርስም ነበር »

Bildergalerie Ostukraine 06.05.2014 Simferopol
ምስል Vasily Maximov/AFP/Getty Images

እስከ አለፈው አርብ ድረስ ሰላማዊ በነበረችው በደቡባዊቷ የወደብ ከተማ ኦዴሳ በተከሰተ ግጭት ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል ። መንግሥት በከተማይቱ ይዞታውን ለማጠናከር ልዩ ኃይሎችን አዝምቷል ። የዩክሬን መንግሥት እንደሚለው በምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል የሚያካሂደው ዘመቻ ዓላማ ሰላማዊ ሰዎችን መግደል አይደለም ። ይሁንና በመንግስት አባባል አማፅያን ሰለማዊ ሰዎችን ከለላ አድርገው የመንግሥት ኃይሎችን እየወጉ ነው ።

«የዩክሬን ወታደሮች ሰለማዊ ሰዎች ላይ መተኮስ አይችሉም ። እኛ የማንወስደውን ይህን እርምጃ ጠላቶቻችን ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው ። ጠላታችን ከሰላማዊ ሰዎች በስተጀርባ ሆኖ እኛ ላይ እየተኮሰብን ነው »

ዩክሬንን ከባሰ ቀውስ ይታደጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ምርጫ እንደታቀደው መካሄዱን ምዕራቡ ዓለም ይፈልጋል ። ሆኖም በዚህ ግጭት መሃል ምርጫው መካሄድ መቻሉ አጠራጣሪ ይመስላል ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ምርጫ ካልተካሄደ ዩክሬን የባሰ ችግር ውስጥ ትወድቃለች ፤ የርስ በርስ ጦርነትም ያሰጋታል ሲሉ ገልፀዋል ። በርሳቸው አስተያየት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምርጫው እንዲካሄድ አይፈልጉም። የታቀደው ምርጫ ይካሄድ ዘንድም ኦሎንድ መላው አውሮፓና ዩናይትድ ስቴትስ ሩስያ ላይ ማዕቀብ በመጣል ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ። በሩስያ ላይ ተጨማሪ የማዕቀብ እርምጃ ይወሰድ የሚለው ጥያቄ ባልቆመበት በዛሬው እለት የሩስያና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ 30 የአውሮፓ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ቭየና ኦስትሪያ ውስጥ በሚያካሂዱት የአውሮፓ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የዩክሬን ቀውስ ይመከርበታል ። ስብሰባው አሁን እየተባባሰ ለቀጠለው ግጭት መፍትሄ ማምጣት አለማምጣቱ አልታወቀም ። አንድ የታወቀ ነገር ቢኖር ጀርመን ሩስያ አልቆለታል ካለችው የጄኔቫው ስምምነት የሚቀጥል ሁለተኛ የሰላም ጉባኤ ጄኔቫ ውስጥ እንዲጠራ ግፊት እያደረገች መሆኑ ነው ። ሩስያ ደግሞ የተባባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ሌላ ስብሰባ እንዲጠራ እየጠየቀች ነው ። ሩስያ ይካሄድ ያለችው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ ምን ሊፈይድ ይችላል ተብለው የተጠየቁት በኬቭ የሃይንሪሽ በል ድርጅት ሃላፊ ሳቪን ይህ ሩስያ ራሷን ከደሙ ንፁህ ሰድራጋ ለማቅረብ የምትጠቀምበት ስልት ነው ሲሉ ነው የመለሱት ።

«ሩስያ አደገኛ ጨዋታ እየተተጫወተች ነው ። በዩክሬን ሩስያ የሌለችበት የርስ በርስ ጦርነት ነው የሚካሄደውሲሉ ዳር ቆመው ጉዳዩን በጣም በጭንቀት እንደሚመለከቱ ለዓለም ለማሳየት እየሞከሩ ነው ። ለሩስያ ተናጋሪ ህዝብ እንደምትጨነቅ ፤ ለራሷ ድንበር እንደምታስብ ፣ ግጭቱ ወደ ተለያዩ ከተሞች እንዳይሰራጭ እንደምትጨነቅም እንዲሁ ። እንደምትለውም ለዚህ ነው የሩስያ ወታደሮች ዩክሬን ድንበር ላይ የሰፈሩት ። ሩስያ ግጭቱን በምሥራቅና በምዕራብ ዩክሬን መካከል የሚካሄድ ብቻ አድርጋ አሳንሳዋለች ። ፑቲን ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት እስካሁን የተረሳው የምሥራቅ ዩክሬን ህዝብ አሁን ለመብቱ ለመቆምና ለመታገል መወሰኑን ነው ።የፀጥታው ምክር ቤት በዩክሬን ጉዳይ ላይ ስብሰባ እንዲያካሂድ መጠየቅም የዚሁ ትርዒት አካል ነው ።»

Ukraine prorussische Aktivisten Zusammenstöße in Odessa 4.5.14
ምስል Reuters

በስቪን አስተያየት ሩስያ ከዚህ ስብበሳ ሌላም ማትረፍ የምትፈልገው ጥቅም አለ ።

« በኔ አስተያየት ሩስያ ወታደሮቿ በዩክሬን ዘመቻ እንዲያካሂዱ ይህንንም ህጋዊ ለማድረግ ምክንያት እየፈለገች ነው ።በመጨረሻም ግጭቱ እንዳይዛመት ለማስቆም በሰላም አስከባሪነት ከመግባት ውጭ ሌላ ማድረግ የምንችለው ነገር አይኖርም ልትል ትችላለች ። በአሁኑ ጊዜ የሩስያ ወታደሮች ክሪሚያ እንዳደረጉት ዩክሬን ገብተው መሬት መያዝ የሚችሉአይመስልም ። ሆኖም አሁንም ቢሆን ይህ አይደረገም ብሎ ለመደምደም አይቻልም ። »

በግጭቱ መባባስ ስጋት ጀርመንን የመሳሰሉ ሃገራት ዜጎቻቸው ግጭት ካየለባቸው የዩክሬን አካባቢዎች እንዲወጡ እያስጠነቀቁ ነው ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጀርመናውያን ደቡባዊና ምሥራቃዊ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ መክሯል ።የዩክሬን መንግስት የችግሩ መፍትሄ ከአቅሙ በላይ ቢመስልም በዩክሬን ሰላም መልሶ የመስፈኑ ተስፋ አልጨለመም ይላል ። የዩክሬን ጊዜያዊው ፕሬዝዳንት ኦሌክሳንድር ቱርቺኖቭ ህዝቡ ሰላሙን ለመጠበቅ ከመንግስት ጎን መቆሙን የኦዴሳን ህዝብ ምሳሌ አድርገው ተናግረዋል።

« በኦዴሳ የዩክሬን ባለሥልጣናት ተግባራቸውን እያከናወኑ ነው ። በኦዴሳ ከተማይቱን ለመጠበቅና ዩክሬንንም ከጥቃት ለመከላከል የተዘጋጁ በርካታ ሃቀኛ አርበኞች አሉ ። በዩክሬን ሰላም መልሶ እንደሚሰፍን እርግጠኛ ነኝ ። »

መንግሥት በዩክሪን ተስፋ የሚያደርገው ሰላም የሚወርድበት ጊዜ ቅርቡ ሊሆን እንደማይችል መገመት የሚያዳግት አይመስልም ፤ ለሰላም አስፈላጊ የሆኑት ቅድመ ሁኔታዎች ከወዲሁ አይታዩምና ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ