1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወታደሮች ሚና በሊባኖስ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 11 1998

የእስራኤል ወታደሮች ደቡባዊ ሊባኖስን ለቀው ሲወጡ

https://p.dw.com/p/E0iH
ምስል AP

የእስራኤልና የሂዝቦላን ጦርነት ለማስቆም በተላለፈው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት ውሳኔ መሰረት የሊባኖስ ወታደሮች ዛሬ ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ መንቀሳቀስ ጀምረዋል ። ወታደሮቹም ከሊታኒ ውንዝ በስተሰሜንና እና በስተደቡብ በሚገኙ አካባቢዎች ነው የሚሰፍሩት ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በእስራኤልና በሂዝቦላ መካከል ወደፊት ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን ለመከላከል አስራ አምስት ሺህ የሊባኖስ ወታደሮችን እንዲሁም አስራ አምስት ሺህ የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎችን ነው ደቡብ ሊባኖስ ለመላክ ያቀደው ። በዕቅዱ መሰረት በአካባቢው ይሰፍራል የተባለው ዓለም ዓቀፍ ሀይል ተግባር ምን እንደሆነ ብዙም ግልጽ እንዳይደለ የዶቼቬለው Jörg Kaminski ከአማን ዮርዳኖስ ዘግቧል ። የዛሬ ሳምንት አርብ የፀጥታው ምክርቤት የእስራኤል ሂዝቦላህ ጦርነትን እንዲያበቃ ያሳለፈው ውሳኔ ለብዙዎች ራስ ምታት መሆኑ እየተነገረ ነው ። ምክንያቱም ውሳኔው የበርካታ ዋና ዋና ጉዳዮችን ዝርዝር አፈፃፀም አላካተተምና ። ለምሳሌ በደቡብ ሊባኖስ የሚዘምተው ዓለም ዓቀፍ ሀይል በዚያ ምን እንደሚያደርግ ውሳኔው ላይ በግልጽ አልሰፈረም ። የወታደሮቹም መብትና ግዴታ ምን እንደሆነም አይታወቅም ። በተጨማሪም ለእነዚህንና ለመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማን መልስ እንደሚሰጥም እንዲሁ ግልፅ አይደለም ። ውሳኔው ከተላለፈ ነገ ሳምንት ይሞላዋል ። በዚህ የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም አገሮች ለዓለም ዓቀፉ ሀይል ወታደሮችን ለማዋጣት ፈቃደኝነታቸውን እያሳወቁ ነው ። ሊባኖስ ለሚዘምተው የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሀይል ወታደር ለማዋጣት ከተስማሙት ውስጥ ፈረንሳይ ፣ ቱርክ ፣ ማሌዥያ እና ፓኪስታን ይገኙበታል ። የእነዚህ ሀገራት ዲፕሎማቶችም በጉዳዩ ላይ ቤይሩት ውስጥ እየመከሩ ነው ። እነዚህ መንግስታት ግን ከሊባኖስ የሚጠብቁት ዐብይ ጉዳይ አለ ። ከሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ነፃ መሆን ካለበት የደቡብ ሊባኖስ ቀጣና ሂዝቦላህ ለመልቀቁ ከሊባኖስ መንግስት ዋስትና ይሻሉ ። ማናቸውም ቢሆኑ ወታደሮቻቸው ከሸማቂው ሂዝቦላህ ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ አይፈልጉም ። ምንም እንክዋን ሂዝቦላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔን ቢቀበልም ከደቡባዊ ሊባኖስ መወጣቱና ሸማቂዎቹንም ትጥቅ ማስፈታቱ አሁንም አጠራጣሪ ነው ። ከነዚህ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳትም እንደ ቱርክና ሞሮኮ ያሉት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት በሊባኖስ የሚሰማራው ዓለም ዓቀፍ ሀይል ሀላፊነት መብትና ግዴታዎችን የሚዘረዝር ሌላ ሁለተኛ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል ። እስከዚያው ድረስም ሁለቱ አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ሊባኖስ መላካቸውን እንደሚያዘገዩ ነው ያሳወቁት ። ወታደሮች እናዋጣለን ያሉት አገራት ይህን ሲሉ ሊባኖስ ደግሞ ውሳኔውን በቀና መንፈስ እንደምታየው ነው የምትገልፀው የገንዘብ ሚኒስትርዋ ዳሺሀድ አሱር ደቡብ ሊባኖስ የሚሰፍረው ጦራቸው ሀገሪቱን ያረጋጋል እያሉ ነው ።
ድምፅ...........
“የሊባኖስ ጦር በደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል መስፈሩ ለህዝባችን የተጠናከረ ፀጥታና መረጋጋትን እንደሚያመጣ እናረጋግጣለን ። በዕርግጥ የእስራኤልና የሂዝቦላህ ግጭት ወደ ውስጣዊ ግጭት እንዲቀየር ዕቅዳችን አይደለም ። “
የእስራኤል ጦር ዛሬ እንዳስታወቀው በደቡብ ሊባኖስ ከያዛቸው አካባቢዎች ግማሹን እዚያ ለሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ሀይል አስረክቧል ። ። በሊባኖስ የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሃይል ደግሞ እነዚህኑ አካባቢዎች ለሊላኖስ ጦር ያስረክባል ። በዕቅዱ መሰረት በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አስራ አምስት ሺህ የሊባኖስ ወታደሮች እንዲሁም ሊባኖስ የሚገኙት ሁለት ሺህ የተባበሩት መንግስታት ሀይሎች እስራኤል ድንበር ላይ ከሰፈሩ በኃላ በአጠያያቂው አካባቢ ሂዝቦላህ የሚወስደው ዕርምጃ ለሊባኖስ መንግስት የትብብር ዕንቅስቃሴ ወሳኝ ነው የሚሆነው ። ሂዝቦላህ ትጥቁን ካልፈታ የቤይሩት ማዕከላዊ መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ ማክሸፉ ተሳካለት ማለት ነው ። ይህ ከሆነ ደግሞ የሊባኖስ መንግስት ከዚህ በፊት የእስራኤልን ጥቃት ዝም ብሎ እንደተመለከተው ሁሉ ወደፊትም ሌሎች የተደራጁ ቡድኖች ሂዝቦላን ተቃውመው ቢነሱ መንግስት ተመልካች መሆኑ ነው ። ሂዝቦላም በሺዓዎች መተቸቱ አልቀረም ። የሂዝቦላ አመራር አገሪቱን ከሞላ ጎደል የታገተች አድርጎዋታል የሚሉ ነቀፌታዎች እየጨመሩ መጥተዋል ። አክራሪዎቹ የሊባኖስ የማሮናይት ክርስቲያኖች ቡድኖች ደግሞ የሺአዎቹን ድርጅት ሂዝቦላን የሚበቀሉበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ናቸው ።