የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባኤ ዘገባ
ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2006በመላው አፍሪቃ ደግሞ የአራት በመቶ እድገት አስመዝግቧል ። በአንዳንድ አካባቢዎችና በአፍሪቃ ሃገራት የእድገቱ መጠን ከቦታ ቦታ ልዩነት ይታይበታል ።ፍሬድሪከ ሙለር ያነጋገረቻቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የግል ንግድ ድርጅት መሪ ወይዘሮ ሙሉ ሰሎሞን ወደ ሃገራቸው ኢትዮጵያ የሚገቡ ዓለም ዓቀፍ ባለወረቶች ስብጥር እየተለወጠ በመሄድ ላይ መሆኑን ታዝበዋል ። ይህም አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል።
« መጀመሪያ ላይ የሚመጡት ቻይናውያን ቱርኮችና ህንዶች ነበሩ ። አሁን ግን ያለውን ሰፊ የስራና የገበያ እድል በመረዳት የምዕራባውያን ሃገራት ባለሃብቶች እየገቡ ነው ። »
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወይዘሮ ሙሉ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ነበሩ ። በዚህ ሃላፊነታቸውም የውጭ ባለ ሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እና ሥራቸውን የሚገድቡ ቢሮክራሲያዊ ደንቦችም እንዲቃለልላቸው ይታገሉ ነበር ።በወይዘሮ ሙሉ አስተያየት የውጭ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መወረታቸው ሃገሪቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጠቃሚ እያደረገ ነው ።
« ከፍተኛ እድገት ካስመዘገቡ ሃገራት ጋር አብረን ስንሰራ ለኛ ብዙ ጥቅም አለው ። ከነርሱ ትምህርት እንቀስማለን ። የስራ እድል መፍጠራቸው አንዱ ጥቅም ነው ። ሌላው ጥቅም ደግሞ የምርት ጥራትም ከፍ ማለት ነው ። የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን ብንወስድ እንኳን አንድ ኩባንያ 10 ሺህ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሰራል ።ሌላው ደግሞ ወደ ስምንት ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል ።ይህ ለኛ ትልቅ የስራ ገበያ እድል ነው ።»
ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጋር ሲነፃጸር ፣ ከ2012 የበለጠ ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በብዛት የተካሄደባት ሃገር ናት ። የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባኤ በምህፃሩ UNCTAD እንደሚለው በ2013 በምሥራቅ አፍሪቃ የዓለም ዓቀፍ ባለ ሃብቶች ውረታ በ15 በመቶ ከፍ ብሏል ። ከነዚህ ውረታዎች አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያና በኬንያ ነው የተካሄዱት። በ2013 በአፍሪቃ ከፍተኛው የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት የተመዘገበው ግን ደቡባዊ አፍሪቃ ውስጥ ነው ። ከ2012 ጋር ሲነፃፀር በደቡባዊ አፍሪቃ የውጭ ባለሃብቶች ውረታ በእጥፍ ጨምሯል ። ባለሃብቶች በይበልጥ የተሰማሩትም በደቡብ አፍሪቃ ና በዚምባብዌ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ነበር ። በተቀሩት የአፍሪቃ ሃገራት አነስተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ነው የተመዘገበው ። ለዚህም UNCTAD ፖለቲካዊ አለመረጋጋትንና በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ቀውሶችን በምክንያትነት አስቀምጧል ።
በዚህ ረገድ ድርጅቱ የሰሜን አፍሪቃው ቀውስ በምዕራብ አፍሪቃዋ በናይጀሪያ የተፈጠረው አስተማማኝ ያልሆነ ሁኔታ እንዲሁም የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን የርስ በርስ ጦርነት ጠቅሷል ። የጀርመኑ የዓለም ዓቀፍና አካባቢያዊ ጥናቶች ተቋም በምህፃሩ GIGA ባልደረባ ሮቤርት ካፕል የውጭ ባለወረቶችን የሚገፉና የሚስቡ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ይገልፃሉ።
«ባለወረቶች የርስ በርስ ጦርነት ወይም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወዳለበት ሃገር አይመጡም ። ሁኔታዎች ሲረጋጉ ግን ይሄዳሉ ። ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ሃገራት በጣም የተሳኩ ተግባራት አከናውነዋል ። በምሥራቅ አፍሪቃ በአንዳንድ የታላላቅ ኃይቆች ሃገራት ለምሳሌ በሩዋንዳ በኡጋንዳ ብዙ ተከናውኗል ። ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ባሉበት በኢትዮጵያና በአንጎላ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ባለወረቶችን ለማማለልና በኢንዱስትሪው ልማት እንዲሰለፉ ለማድረግ አብቅተዋል። »
አፍሪቃ ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ና አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ላቅ ያለ ትርጉም እየተሰጣቸው ነው ። በሌላ በኩል በጥሬ ሃብት ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ግን ያን ያህል አይደለም ። ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ግን በአፍሪቃ በዘርፉ የተካሄደው የመዋእለ ንዋይ ፍሰት ከአጠቃላዩ ውረታ ከግማሽ በላይ ነበር ። በአሁኑ የUNCTAD ዘገባ እንደተመለከተው ግን አንድ አስረኛውን ድርሻ ብቻ ነው የሚይዘው ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ