1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ የ«ኤች አይ ቪ»ን ስርጭት የመግታት ግብ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14 2007

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም አንስቶ በHIV ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 35 በመቶ መቀነሱን የተመድ ያመለክታል። ከኤድስ ጋ በተያያዘ የሚያልፈዉ የሰዎች ሕይወትም በ41 በመቶ መቀነሱ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/1G2Hz
UN melden Erfolge im Kampf gegen Aids
ምስል picture-alliance/dpa/J. Hrusa

የተመድ የHIVን ስርጭት የመግታት ግብ

ያም ቢሆን ግን ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጨረሻ የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ እንዳደረገዉ አሁንም 36,9 ሚሊዮን ሕዝብ ተሐዋሲዉ በደሙ ዉስጥ ይገኛል። የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊ ሙን ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ይፋ አደረጉት የተባለዉ መረጃ ነዉ ይህን ስኬት ያበሰረዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች አዎንታዊ ለዉጥ መመዝገቡ እዉነት መሆኑን ቢያረጋግጡም፤ ከዚህ ቀደም ይከናወን የነበረዉ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ አሁን እየረገበ መምጣቱ አደጋ እንዳለዉ ያስገነዝባሉ።

Uganda Gesundheitszentrum in Kyetume - HIV-Patientin
ምስል picture-alliance/dpa/H. Wasswa

የተመድ ለአምዓቱ ካቀዳቸዉ የልማት ግቦች በስድስተኝነት ደረጃ የሚገኘዉ የHIV ተሐዋሲ ስርጭትን እንዲሁም በAIDS ምክንያት የሚደርሰዉን የሚሞተዉን ሕዝብ ቁጥር የመቀነስ ጥረት አንዱ ነዉ። ድህነትና ረሀብን ከማጥፋት አንስቶ ዓለም አቀፍ የልማት ትስስርን የመዘርጋትን ሁሉ የሚያካትቱ የልማት እቅዶቹ በአጠቃላይ ስምንት ሲሆኑ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም ነበር ለ15 ዓመታት ተግባራዊ ሆነዉ ዉጤት ለማስመዝገብ የታቀዱት። ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተለይ በንግሥት ዘዉዲቱ መታሰቢያ ሀኪም ቤት ይፋ የሆነዉ የተመድ ዘገባ የHIV ስርጭትና ከኤይድስ ጋ በተያያዘ የጤና እክል የሚቀጠፈዉን የሰዉ ሕይወት የመቀነሱ ጥረት ከታቀደለት የእቅዱ የመጨረሻ ጊዜ ከመድረሱ ዘጠኝ ወራት አስቀድሞ በመላዉ ዓለም ለዉጡ መታየቱን ያመለክታል። የHIV ወረርሽኝ እጅግ ከተስፋፋባቸዉ እና የበርካቶችን ሕይወት ከቀማባቸዉ አካባቢዎች ደግሞ ከሰሀራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ዋነኞቹ መሆናቸዉም በየጊዜ ይነገራል። አሁን ደግሞ መሻሻልና ስኬቱ ከታየባቸዉ ሃገራትም እንዲሁ ተጠቃሽ የሆኑት በዚህ አካባቢ የሚገኙት ናቸዉ። ናሚቢያ፤ ሴኔጋል፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለአብነት ተጠቅሰዋል።

Symbolbild Aids
ምስል Colourbox

ወ/ሮ ወይንሸት ሙሉሰዉ በግርድፍ ትርጉሙ HIV በደማቸዉ ዉስጥ ለሚገኝ አካል ጉዳተኛ ሴቶች እኩል እድል የተሰኘዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ ናቸዉ። በበሽታዉ የተያዙና የተጎዱትን ወገኖች በየግዜዉና በቅርብ የሚከታተሉ እንደመሆናቸዉ HIV AIDSን በተመለከተ በተጨባጭ አለ የሚሉትን እንዲህ ያስረዳሉ።

ይህ የHIV ስርጭት ቀንሷን ወሬ አንዳንዶችን ማዘናጋቱን የሚያመለክቱት ወ/ሮ ወይንሸት፤ የግንዛቤ ማስጨበጫና ማንቂያ እንቅስቃሴዎች መቀዝቀዝን ማስከተሉንም ታዝበዋል። የእሳቸዉን ትዝብት በኢትዮጵያ የክሊንተን ፋሽንዴሽን ተጠሪ ዶክተር ይገረሙ አበበም ይጋሩታል፤

ሙሉዉን ቅንብር ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ