1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ቬልት ሁንገር ሂልፈ» ርዳታ ለሕንድ

ሐሙስ፣ መስከረም 20 2008

«ቬልት ሁንገር ሂልፈ» (Welthungerhilfe) የተሰኘው የጀርመኑ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በተለይ ሕንድ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ያከናወነው ተግባር ለብዙዎች አብነት ሊሆን የሚችል ነው። ሣርዋን በተሰኘው የሕንድ ግዛት ውስጥ በሚገኙ የዓመአቱ መንደሮች የሚል ስያሜ በተሰጣቸው አምስት አካባቢዎች የተከናወነውን ስኬታማ ሥራ ተወድሷል።

https://p.dw.com/p/1GgFU
Logo der Welthungerhilfe
ምስል picture-alliance/dpa/Oliver Berg

[No title]

ካላ በሚል ስያሜ የሚታወቀው የአካባቢው የሙዚቃ ቡድን ሚሊዮኖች ከሚኖሩባት የካልኩታ ከተማ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሣርዋን ግዛት መንደሮች ውስጥ ሙዚቃውን ለማሰማት ብቅ ብሏል።

ጋኔሽ ሲንግ ይህን ዜማ «ሁሉም ገበሬዎች መሆን ይገባቸዋል» የሚል ስያሜ ሰጥቶታል። ጋኔሽ ከሙዚቃ ጓዱ ጋር በመሆን በከፋ የድህነት አረንቋ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ይዘዋወራል። አዲሱ የአመራረት ስልትም በሙዚቃው መልእክት ያስተላልፋል። የጀርመኑ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ያስተዋወቀው አዲሱ የአመራረት ስልት ድሆች በሚበዙበት ጃርካንድ በሚባለው ክፍለ-ሀገር የነዋሪውን ሕይወት የቀየረ ነው። ጋኔሽ ራሱ በሙያው ገበሬ ነው።

«የቀን አበል እየተቀበሉ ሌላ ቦታ በቀን ሥራ ከመቀጠር በአዲሱ የአመራረት ስልት መሠረት ሰፋፊ መሬቶችን እያረስን በምናገኘው ሕይወታችንን በአግባቡ እንመራለን።»

የሕንድ ሴቶችን ሣርዋን ግዛት ሕንድ
የሕንድ ሴቶችን ሣርዋን ግዛት ሕንድምስል DW

ሣርዋን ግዛት ውስጥ የሚገኙ በጥቅሉ 75 የሚደርሱ መንደሮች እና የሠፈራ ጣቢያዎች በ«ቬልት ሁንገር ሂልፈ» የዓመአቱ መንደሮች ፕሮጄክት ተካፍለዋል። ይህ ፕሮጄክት የተባበሩት መንግሥታት ተግባራዊ ለማድረግ ከነደፋቸው የዓመአቱ ስምንት ግቦች ውስጥ የሚመደብ ነው።

የውኃ ተፋሰስ እና የጉድጓድ ውኃ ግንባታዎችን በተመለከተ የተከናወኑት ሥራዎች ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት አካባቢውን ለማጠጣት አስችለዋል። በአካባቢዎቹ ዘላቂነት ያላው የአመራረት ስልትን በመከተልም ምርታማ መሆን ተችሏል።
የጤና ዘርፉም መሻሻል አሳይቷል። ወደ 5,300 የሚጠጉ የመንደሮቹ ነዋሪዎች ቀደም ሲል ከነበረው «እጅግ መጥፎ» የተሰኘ የጤና አገልግሎት «ጥሩ» ወደሚል ለማሸጋገር ተችሏል። በዚሁ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ-ሰናይ ድርጅት መርሐ-ግብር። በአሁኑ ወቅት ከመንደሮቹ 80% ነዋሪዎች በቂ ምግብ ማግኘት ይችላሉ። በመንደሮቹ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፤ ሁሉም የመንደሩ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ይሄዳሉ።

በየአካባቢው የሚገኙ ተባባሪ ድርጅቶችን በማነቃቃት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጉ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓመአቱ ግቦች መካከል አንዱ ነበር። የ«ቬልት ሁንገር ሂልፈ» ባልደረባ ጃኔት ቬለር።

«በየአንዳንዱ መንደር ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመሆን የዓመአቱን የልማት ግቦች ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው፤ ምን አይነት መርሐ-ግብሮችስ አሉ የሚል ጥናት ተከናውኗል።»

ሕንዳውያን ሕፃናት በሣርዋን ግዛት ሕንድ
ሕንዳውያን ሕፃናት በሣርዋን ግዛት ሕንድምስል DW

የመንደሩ ነዋሪዎችን በመርሐ-ግብሩ ተሳታፊ ከማድረግም ባሻገር ንቃተ-ኅሊናቸው ዳብሮ በበርካታ ጉዳዮች ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል። ነዋሪዎቹ ስለመብታቸው መጠየቅም ችለዋል። ለአብነት ያህልም የ«ማሕተመ ጋንዲ ብሔራዊ የገጠር ቅጥር ማስተማመኛ አዋጅ» በሚል የሕንድ መንግሥት እያንዳንዱ ድጋፍ የሚያሻው ነዋሪ በዓመት 100 ቀን እየተከፈለው መሥራቱ ዋስትና ሊሰጠው ይገባል በሚል ተግባራዊ ባደረገው መርሐ-ግብር ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።

የጀርመኑ «ቬልት ሁንገር ሂልፈ» የዓመአቱ ግቦች በሣራዋን እና በሕንድ ሌሎች የዓመአቱ መንደሮች የሚባሉ አካባቢዎች በታቀፉበት ግዛቶች ተጠናቋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2017 ድረስ የጀርመኑ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ያከናወናቸውን ሥራዎች ይቆጣጠራል። እናም ቀደም ሲል ያካበተውን ልምድ በማሰባሰብ በሌሎች የዓመአቱ መንደሮች ውስጥ ለሚከወኑ ሥራዎች እንደመንደርደሪያ ይጠቀምበታል።

ሔለ ዬፕሰን/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ