1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦልቲሞሩ ብጥብጥ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 21 2007

በዩናይትድ ስቴትስዋ የሜሪላንድ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ በባልቲሞር የ25 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ፍሬዲ ግሬይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሳለ የጀርባ አጥንቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ከሞተ በኋላ የተነሳው ረብሻ ዛሬ ጋብ ማለቱ ተሰምቷል ።

https://p.dw.com/p/1FHeL
Baltimore / Ausgangssperre / Polizei
ምስል Reuters

በከተማይቱ ግርግሩና ጥፋቱ ሲባባስ ትናንት ለሊት የተጣለውን ሰዓት እላፊ በርካቶች መጣሳቸው ተዘግቧል ።ለሊቱን አልፎ አልፎ ከፖሊስ ጋር ግጭቶች ቢከሰቱም ያን ያህል የከፋ እንዳልነበረ ነው የዶቼቤለዋ ዛብሪነ ፍሪትዝ የዘገበችው ።
ትናንት ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት የተጣለውን ሰዓት እላፊ ለማስከበር ቦልቲሞር ውስጥ ከ3ሺህ በላይ ፖሊሶችና ብሔራዊ ዘቦች ነበሩ የተሰማሩት ። ሄሊኮፕተሮችም ከአየር ጥበቃ ያደርጉ ነበር ።ሆኖም ትናንት ለተቃውሞ የተሰበሰቡ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች እንዲበተኑ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም ።ተቃዋሚዎቹ የፖሊስ መኮንንኖች የሰጡትን ማስጠንቀቂያና የአካባቢው የመብት ተሟጋቾችን ልመና ወደ ጎን በማለት ውሃ የያዙ ላስቲኮችን ሲወረውሩ አንዳንዶቹ ደግሞ መሪት ላይ ሲተኙ ነበር ።ፖሊስ አስለቃሽ ጢስ በመተኮስ ሰልፈኞቹን ለመበተን ሲሞክር ተቃዋሚዎቹ አስለቃሽ ጢሱን መልሰው በፖሊስ ላይ ሲወረውሩም ታይተዋል ።ሆኖም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የተቃዋሚዎቹ ቁጥር እየተመናመነ ሄዷል ።ከተማይቱም ሰላማዊ ለሊት ነው ያሳለፈችው ። ይህ ሊሆን የቻለው ርያንን የመሳሰሉ በጎ ፈቃደኖች ባደረጉት ጥረት መሆኑን ዛብሪነ ዘግባለች ። ርያን አመፁን በመቃወም ከተሰለፉት 300 ሰዎች አንዱ ናቸው ።
« ሰዎቹ መረበሻቸው እንረዳለን ። በደህንንነት እንዲቆዩ ለማበረታታት እንሞክራለን ። የሆነው በጣም ያሳዝናል ፤ ግን ባልቲሞር ማገገምዋ ችግሩን መወጣትዋ አይቀርም ። ጥሩ ና ብርቱ ሰዎች ያሏት ጠንካራ ከተማ ናት »
ትናንት ቀኑን ሙሉ በከተማይቱ ነዋሪ የሆኑ ቄሶች ና የማህበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች እንዲሁም በጎ ፈቃደኞች በየጎዳናው እየተዘዋወሩ ሰላም እንዲሰፍን ህዝቡም ማታ ከቤቱ እንዳይወጣ ሲመክሩ ነበር የዋሉት ። ከተማዋ ራስዋ በአመፁ የተደናገጠች ነበር የምትመስለው ። ከከተማዋ አስከፊ ገፅታ በኋላ አሁን ጥሩ ጎንዋ ጎልቶ እየታየ ነው ።የቦልቲሞር ወደብ የብዙ ሃገር ጎብኝዎች መስህብ ነው ። እዚያ ባለው ብሔራዊ ሰው ሠራሽ ገንዳ ውስጥ የሚዋኙት ሻርኮችና የወሃ ኤሊዎች የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው ።ይህ ስፍራ አሁን እንደቀድሞው በካሜራ ብቻ አይደለም የሚጠበቀው ። የብረት ቆብ ያጠለቁና አውቶማቲክ ጠመንጃ ያነገቱ 3 ወታደሮች አካባቢውን ይጠብቃሉ ። አንዲት የከተማዋ ነዋሪ ወጣት በምታየው ማዘኗን ትናገራለች ።
« ይህን ሳይ አዝናለሁ ።ይህ ትክክለኛው ቦልቲሞር አይደለም ።ረብሻው የተወሰኑ ሰዎችን እንጂ ብዙሃኑን አይወክልም ።»
ቦልቲሞር የ650 ሺህ ሰዎች መኖሪያ ናት ። በከተማይቱ ያሉ አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ህይወታቸውን በተለመደው መንገድ ነው የሚመሩት ። በከተማይቱ የጥቁርና ነጭ ልዩነት የጠብ ምክንያት አይሆንም ።የቦልቲሞር ከንቲባ አፍሪቃዊ አሜሪካዊ ናቸው ።የፖሊስ ሃላፊውም ጥቁር አሜሪካዊ ናቸው ። ሆኖም በከተማይቱ በርካታ ማህበራዊ ችግሮች አሉ ። ከፍተኛ ሥራ አጥነት ወሮበሎች አደንዛዥ እፅ የከተማይቱ ዐብይ ችግሮች ናቸው ። እያንዳንዱ ሰው ማለት ይቻላል ሽጉጥ ታጥቋል ። የከተማዋ ፖሊስ አንዳንዴ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመውሰድና ከከተማዋ ወጣ ባሉ ስፍራዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ከልብ ባለመከታተል ይተቻል ።25 የከተማዋ ወጣቶች ይህን ለመቀየር እየሰሩ ነው ። ወጣቶቹ በፖሊስና በማህበረሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ይረዳል ያሉትን ፕሮጀክት ጀምረዋል ።ወጣቶቹ ፕሮጀክቱ ችግሮቹን ያቃልላሉ የሚል እምነት አላቸው ።

USA Baltimore nach Ausschreitungen
ምስል Mark Makela/Getty Images
USA Baltimore Ausschreitungen Bildergalerie Bild 12
ምስል DW/J. Karl

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ