የብሪክስ ጉባኤ ፍፃሜና ተቃውሞው
ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2005ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ የሚገኙት በእንግሊዘኛው ምህፃር ብሪክስ በመባል የሚጠሩት 5 ሃገራት ደቡብ አፍሪቃ ደርባን ውስጥ ለ2 ቀናት ያካሄዱት ጉባኤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቋል ። የአባል ሃገራቱ መሪዎች በአሁኑ ጉባኤ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች አንዱ ምዕራቡ አለም ተፅእኖ የማያደርግበት የጋራ የልማት ባንክ ማቋቋም ነው ። 5 ቱ የብሪክስ አባላት ብራዚል ሩስያ ህንድ ቻያናና ደቡብ አፍሪቃ ለባንኩ ለታቀደው መነሻ ካፒታል 50 ቢሊዮን ዶላር እኩል ድርሻ እንደሚያዋጡ ተገልጿል ።
ይሁንና የብሪክስ ጉባኤን በመቃወም በተጓዳኝ በተካሄደ ሌላ ጉባኤ ደቡብ አፍሪቃ በብሪክስ ቡድን ውስጥ የምትጫወተውን ሚናና የጋራ ባንኩን የማቋቋሙ እቅድ ተተችቷል ።የብሪክስ ጉባኤ ተቃዋሚዎች ከተነጋገሩበት ጉዳይ አንዱ የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ባንክ ያጋጠመው የ40 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራ ነበር ። በባንኩ ሃላፊ በፅሁፍ በወጣው መግለጫ መሰረት ባንኩ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል ። ደቡብ አፍሪቃ አባል የሆነችበት ብሪክስ ሃገሪቱን ይበልጥ ጎዳ እንጂ አልጠቀመም ሲሉ የብሪክስተቃዋሚዎች ይከራከራሉ ። ትናንት ተጀምሮ ዛሬ በተጠናቀቀው የመሪዎች ጉባኤ የብሪክስ መንግሥታት የራሳቸውን ዓለም ዓቀፍ የልማት ባንክ ለማቋቋም ተስማምተዋል ። 2 ቀናት ደርባን ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ
የብራዚል የሩስያ የህንድ የቻይናና የደቡብ አፍሪቃ ርዕሳነ ብሄርና መራህያነ መንግሥት ቡድኑ ይበልጥ ከምዕራቡ አለም የኤኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ ፍላጎት እንዳለቸው ገልፀዋል ። የብሪክ አባላት የፋይናንስ ቀውስ መከላከያ ገንዘብ ለማዘጋጀትና ለብሪክስ መንግሥታት የመበደር አቅምን የሚመዝን የራሳቸው የሆነ ድርጅት ለማቋቋም አቅድዋል ። ቻይና በአሁኑ ጊዜ የደቡብ አፍሪቃ ዋነኛ የንግድ አጋር ናት ። ሁለቱ አገሮች በሚያካሂዲት የጋራ የንግድ ልውውጥ የደቡብ አፍሪቃ ድርሻ ዝቅተኛ በመሆኑ መስተካከል እንደሚኖርበት የደቡብ አፍሪቃን የፖለቲካው ሂደት በጥሞና የሚከታተሉት ፓትሪክ ቦንድ አሳስበዋል ። ቦንድ እንደሚሉት በዚህ የንግድ ልውውጥ ደቡብ አፍሪቃ አልተጠቀመችም ።
« ከ1990ዎቹ ወዲህ ደቡብ አፍሪቃ የምታካሂዳቸው ንግዶች ፤ የጨርቃ ጨርቅ ፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና የቆዳ አምራች የሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን እድሎች አቃጥለውብናል ። በከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ፣ በዝቅተኛ ዋጋ ተመርተው በርካሽ በሚገቡ እቃዎች ምክንያት እነዚህ ን በመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች በርካታ የሥራ እድሎችንና ገበያዎችን አጥተናል ። »
የቦንድን ትችት የደቡብ አፍሪቃ የሠራተኞች ማህበር በምህፃሩ COSATU ም ይጋራል ። የኮሳቱ ሃላፊ ስቬሊንዚማ ቫቪ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ SABC በተባለው የደቡብ አፍሪቃ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የብሪክስ አገሮች ለማቋቋም ያሰቡትን ባንክ በጥርጣሬ ነው የሚያዩት ።
ባንክ ከአለም የገንዘብ ድርጅትና ከአለም ባንክ አሠራር በመሰረቱ የተለየ እንዲሆን ግፊት እናደርጋለን ።»
« ሂደቱን በጥንቃቄ ነው የምንከታተለው ምክንያቱም ማንኛውም ለወደፊቱ በብሪክስ አገሮች የሚቋቋም ባንክ ከአለም የገንዘብ ድርጅትና ከአለም ባንክ አሠራር በመሰረቱ የተለየ እንዲሆን ግፊት እናደርጋለን ።»
ሃያስያን የጋራው ባንክ ጥሬ እቃዎችን ለማጋበስና ገበያም ለማግኘት ርስበርስ መፎካከራቸው የሚነገርላቸውን አባል ሃገራት በትክክልና ፣ ባልተወሳሰበ ሁኔታ መርዳት መቻሉን ይጠይቃሉ ። በጎርደን የኤኮኖሚ ተቋም የብሪክስ ጉዳዮች አዋቂ አብዱላ ፈራችያ የባንኩ አሠራር ዘመናዊ ከሆነ ይህ አያሳስብም ይላሉ ።
«የብሪክስ የልማት ባንክ በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት መሰረታዊ ለውጥ የሚያደርግ ይመስለኛል ። አሠራሩ ዘመናዊ አቅድን ከተከለ በብሪክስ አገሮች ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃም ዋና ዋና መሰረተ ልማቶችንና ሌሎችም ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚያስችለውን አቅም ያዳብራል ። »
ሉድገር ሻዶምስኪ
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ