1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያና የአውሮጳ ኅብረት ስምምነት

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2008

የአውሮጳ ኅብረት እና ብሪታንያ ባለፈው ሳምንት ፣ ብሪታንያን በኅብረቱ ልዩ ቦታ ያሰጣታል የተባለ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ብሪታንያ ከኅብረቱ ጋር የደረሰችበት ይህ ስምምነት ፣ህዝባቸው ሃገሪቱ በአዉሮጳ ኅብረት አባልነት እንድትቀጥል እንዲወስን ለማሳመን እንደሚረዳቸው ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/1I0T0
Brüssel EU Gipfel - Tusk & Juncker & Cameron
ምስል Reuters/Y. Herman

የብሪታንያና የአውሮፓ ህብረት ስምምነት

ካሜሩን ብሪታንያ የኅብረቱ አባል ከሆነች ከ43 ዓመት በኋላ በአዉሮጳ ኅብረት አባልነት ትቆይ ወይስ ከኅብረቱ ትውጣ በሚለው ምርጫ ላይ i,ዛሬ 4 ወር ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ባለፈው ቅዳሜ ጥሪ አስተላልፈዋል ። የብሪታንያ ህዝብ ከአዉሮጳ ኅብረት ጋር አብሮ በመዝለቅ ወይም አባልነትን በማቋረጥ ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ሲጠየቅ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም ። ሃገሪቱ የያኔው የአዉሮጳ የጋራ ገበያ አባል በሆነች በሁለት ዓመቱ ማለትም የዛሬ 41 ዓመትም በማህበሩ አባልነት በመቆየትና በመውጣት ምርጫ ላይ ህዝበ ውሳኔ አካሂዳለች ።በውጤቱም ህዝቡ ከጋራው ማህበር ጋር ለመቀጠል ቢወስንም ባለፉት 40 ዓመታት «ሃገሪቱ በማህበሩ ውስጥ ሊኖራት የሚገባውን ተገቢ ቦታ ተነፍጋለች ፣ ሉዓላዊነትዋንም አሳልፋ እየሰጠች ነው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ፓውንድ ፣ ለአባልነት ክፍያ የማውጣቷን ያህል ተጠቃሚ አይደለችም የሚሉና የመሳሰሉ ተቃውሞዎች ከህዝቡና ከፖለቲከኞች ተደጋግመው መነሳታቸው ዳግም ህዝበ ውሳኔ እንዲጠራ አብቅቷል ። የብሪታኒያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ዴቪድ ካሜሩን በጉዳዩ ላይ ህዝቡ ድምፅ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ ያሳወቁት የዛሬ 3 ዓመት ነበር ።ከዚያን ጊዜ አንስቶ ብሪታንያ በኅብረቱ ውስጥ እንድትቆይ ኅብረቱ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ሲጠይቁ የቆዩት ካሜሩን በተለያዩ የኅብረቱ አባል ሃገራት እየተዘዋወሩ ላቀረቧቸው የማሻሻያ ሃሳቦች ድጋፍ ሲያሰባስቡ ከርመዋል ። ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኅብረቱ አባል ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባካሄዱት ድርድርም ብሪታንያ በኅብረቱ ልዩ ቦታ ያሰጣታል የተባለ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የቆየው የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ሉዓላዊነትን የዩሮና የፓውንድን ግንኙነትን እንዲሁም ማህበራዊ ድጎማዎች የሚመለከቱት ማሻሻያዎች ይገኙበታል ።

ብሪታንያ በአባልነት እንድትቆይ ከአዉሮጳ ኅብረት በኩል ሊደረጉ ይገባቸዋል ሲሉ ባቀረቧቸው የማሻሻያ ሃሳቦች ላይ ተደራድረው ስምምነት ላይ መድረስ የቻሉት ካሜሩን ሃገራቸው ማሻሻያ በተደረገበት የአዉሮጳ ኅብረት ማህበር ውስጥ በመቆየትዋ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆን ያስረዳሉ ። በርሳቸው አባባል ሃገሪቱ በኅብረቱ አባልነት በመቀጠልዋ ደህንነትዋ አስተማማኝ ጠንካራ ና የተሻለች ሃገር ነው የምትሆነው ።ይሁንና ስምምነቱ አጥጋቢ አይደለም የሚሉ አንዳንድ ተሰሚነት ያላቸው ፖለቲከኞች ብሪታንያ ከኅብረቱ እንድትወጣ ዘመቻቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እያሳወቁ ነው ። ይህን ካሳወቁት ውስጥ የወግ አጥባቂው ፓርቲ አባል የሆኑት የለንደን ከንቲባ ቦሪስ ጆንሰን አንዱ ናቸው ። እርሳቸው እንደሚሉት ማሻሻያ የተባለው የአዉሮጳ ኅብረትና የብሪታንያ ግንኙነቶች ማሻሻያ ተብሎ ሊወስድ የሚችል አይደለም ። በዚህ የተነሳም ህዝቡ ሃገሪቱ በአዉሮጳ ኅብረት አባልነት መቀጧሏን ተቃውሞ ድምጹን እንዲሰጥ ለመቀስቀስ ተነስተዋል ።
« ከከባድ የልብ ሕመም በኋላ ነው ውሳኔ ላይ የደረስኩት። ምክንያቱም ምንም ማድረግ አልፈልግም ነበር ። ማድረግ የማልፈልገው ነገር ቢኖር የብሪታኒያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንን ወይም መንግሥታቸውን መቃወም ነበር ። ሆኖም ከከባድ የልብ ህመም በኋላ ሌላ ማድረግ የምችለው ነገር ያለ አልመሰለኝም ።እናም ህዝቡ ከኅብረቱ አባልነት ለመውጣት ድም|ፁን እንዲሰጥ ማበረታታቴን እቀጥላለሁ ። ይህን የሚደግፉ ብዙዎች እንዳሉ እረዳለሁ ። ምክንያቱም እኔ ለዚህች ሃገር ህዝብ ገንዘብ ለመቆጠብ እና የቀድሞውን ተቆጣጣሪነቱን እንዲረከብ እፈልጋለሁ ።»
ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት እንድትወጣ ዘመቻ ከሚያካሂዱት ውስጥ የታላቋ ብሪታንያ ነፃ ፓርቲ በምህፃሩ UKIP የተባለው ፓርቲ አንዱ ነው ። ፓርቲው ወደ 4 ሚሊዮን ድምፅ በማግኘት ያለፈውን የአዉሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ አሸንፏል ። የUKIP ሊቀ መንበር ኒግል ፋራገ ስምምነቱን ዋጋ ቢስ ሲሉ አጣጥለውታል ።
«የዴቪድ ካሜሩን ስምምነት ፣ ስምምነቱ የተፃፈበት ወረቀት የሚያወጣውን ዋጋ ያህል እንኳን የለውም ። የአዉሮጳ ኅብረት የሚያሳልፋቸውን መጥፎ ህጎች ፓርላማችን መሻር ያለመቻሉን ጉዳይ አላየም ። »
5 የካቢኔ አባላትን ጨምሮ ከገዥው የወግ አጥባቂ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግምሽ ያህሉ እንዲሁም የተወሰኑ የሌበር ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ብሪታንያ ከኅብረቱ እንድትወጣ ይፈልጋሉ ። ፀረ አዉሮጳ ኅብረት አቋም የሚያራምዱት የግራ ክንፉ ጆርጅ ጋሎዌይም እንዲሁ ።ካሜሩን ግን ማሻሻያው ተቃውሞ ቢነሳበትም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ለሚቃወሙት ደግመው የተናገሩት ።
«ለቦሪስ የምለው ለማንኛውም ሰው የምለውን ነው ። በአዉሮጳ ኅብረት ውስጥ ብንቆይ ደህንነታችን እንደሚጠበቅ ፣ ጠንካራ እንደምንሆን እንዲሁም የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምንደርስ። እንደሚመስለኝ ከኒግል ፋራገ እና ጆርጅ ጋሎዌይ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ወደ ጭለማ ዘሎ መግባት የተሳሳተ እርምጃ ነው ።እናም ቦሪስ እና ሌሎች ፣ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ማድረግ ስለመቻል ከምር የሚጨነቁ ከሆነ ይህን ልናደርግ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ የአዉሮጳ ኅብረት ነው ። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሃገር ነን ። የተመድ አባል ነን ። የዓለም የገንዘብ ድርጅትም አባል ነን ። »
ከሃገር ውስጥ ፖለቲከኞች በኩል ጠንካራ ተቃውሞ የተነሳበት ባለፈው ሳምንት ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት ጋር የደረሰችበት ስምምነት በሌሎች የኅብረቱ አባል ሃገራት ላይ ሊያስከትል ይችላል በተባለው ተፅእኖም መተቸቱ አልቀረም ። ገበያው
ያም ሆኖ ስምምነቱ ከሃገር ውስጥም ደጋፊዎች አላጣም ። ብሪታንያ ከኅብረቱ አለመውጣቷን የሚደግፉ ኃይሎች ሃገሪቱ ከማህበሩ ብትወጣ የምታጣው ጥቅም ጥቂት የሚባል እንዳይደለ በማስረዳት ይከራከራሉ ።
በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 23 ፣20016 የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ውጤት ብሪታንያ ከኅብረቱ ጋር እንድትቆይ የሚያደርግ ቢሆንም እንኳን ገበያው እንደሚለው የአዉሮጳ ኅብረትና የብሪታኒያን ውዝግብ የሚያስቆም አይሆንም ።ውጤቱ ከኅብረቱ እንድትወጣ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ ሌላ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ።

Symbolbild EU Großbritannien
ምስል picture-alliance/ EPA/F. Arrizabalaga
Großbritannien Cameron und Johnson beim Parteitag in Blackpool
ምስል Getty Images/C. Furlong
Brüssel EU Gipfel - David Cameron
ምስል Reuters/D. Martinez

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ