1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባራክ ኦባማ እና የአውሮጳውያን መሪዎች ምክክር

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2008

ዓለም አቀፍ ውዝግቦችን ለመታገል ዩኤስ አሜሪካ አንድነቷን እና ጥንካሬዋን የጠበቀች አውሮጳ እንደምታስፈልጋት የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/1IcRJ
Hannover Gespräch Staatspräsidenten Obama Renzi Hollande mit Bundeskanzlerin Merkel vor Beginn US-Europa Gipfeltreffen
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ለጉብኝት ከትናንት ጀምረው ሀኖፈር ከተማ ጀርመን የተገኙት ባራክ ኦባማ በሶርያ እና በኢራቅ በሚንቀሳቀሰው ራሱን እስላማዊ መንግሥት ወይም «አይስል» ብሎ በሚጠራው ቡድን እና በሌሎች የፀጥታ ስጋቶች አንፃር ለሚደረገው ትግል መሳካትም አውሮጳውያን መንግሥታት ለመከላከያ የመደቡትን ወጪ እንዲያሳድጉ አክለው አሳስበዋል።
« በሶርያ እና በኢራቅ ለሚካሄደው ያየር ጥቃት ድርሻቸውን የሚወጡ ተጨማሪ መንግሥታት ያስፈልጉናል። በኢራቅ የሀገሪቱን ፀጥታ ኃይላት የሚያሰለጥኑ ተጨማሪ መንግሥታትም ያስፈልጉናል። ኢራቅ ከ«አይስል» ነፃ የወጡ አካባቢዎችን ማረጋጋት እና የ«አይስል» ተዋጊዎችም እንደገና ወደነዚሁ አካባቢዎች እንዳይሄዱ ለማከላከል ትችል ዘንድ ተጨማሪ መንግሥታት ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ ሊሰጡዋት ይገባል። አሸባሪዎች ከተሞቻችን ለማጥቃት እና ዜጎቻችንን ለመግደል ባላቸው አቅም ሁሉ እየሞከሩ ነው። ስለዚህ እኛም ባለን ኃይል ተጠቅመን ልናስቆማቸው ይገባል። ይህ ርምጃችንም፣ አሸባሪዎች በፓሪስ እና በብራስልስ የሰነዘሩዋቸውን ዓይነት ጥቃቶች እንዳይጥሉ፣ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን መዝጋትን ጭምር ያጠቃልላል። »
ዩኤስ አሜሪካ ተጨማሪ 250 ልዩ ኃይላት ወደ ሶርያ እንደምትልክ አሜሪካዊው ፕሬዚደንት አስታውቀዋል። ኦባማ የሀኖፈሩን ጉብኝታቸው ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከብሪታንያ እና ከኢጣልያ መሪዎች ጋር በፀጥታ ጉዳይ ላይ ይፋ ያልሆነ ስብሰባ በማድረግ ያጠናቅቃሉ።
ፕሬዚደንት ኦባማ በዩኤስ አሜሪካ እና በጀርመን፣ እንዲሁም፣ በአውሮጳ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት በማሳደጉ ጉዳይ ላይ ባተኮረው የሀኖፈር ጉብኝታቸው ዛሬ ከቀትር በፊት ትልቁን የኢንዱስትሪ ትርዒት ለሁለት ሰዓት ያህል ጎብኝተዋል። አሜሪካዊው ፕሬዚደንት በሀኖፈሩ ቆይታቸው ሀገራቸው ከአውሮጳ ህብረት ጋር ስለጀመረችው እና ብዙ እክሎች ተደቅነውበታል ስለሚባለው የትራንስ አትላንቲክ የንግድና መዋዕለ ንዋይ ትብብር ድርድር ከመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር በሰፊው መክረዋል።

Hannover Messe US-Präsident Obama und Kanzlerin Merkel bei Harting
ምስል Harting

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ