የባሊው የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2000የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በቦታው ላይ ተገኝተዋል።የፓትሮል መኪኖች አብረዋቸው የሉም።በአራት ጠባቂዎቻቸው ብቻ ታጅበው በእግራቸው ወደ አዳራሹ አቀኑ።አሜሪካዊው የአካባቢ ጥበቃ የዘንድሮ የኖቤል ተሸላሚ አል ጎር።አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰበው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ ታዳሚ ሞቅ ባለ መንፈስ ተቀበላቸው።
አልጎር ንግግር ከማድረጋቸው በፊት ሰኞ ኖርዌይ ኦስሎ ላይ የሠላም ኖቤል ተሸላሚና የዓለም አካባቢ ጥበቃ ኃላፊ ለሆኑት ህንዳዊው ራሼንድራ ፓሳውሪን ሠላምታ አቀረቡ።ከዚያም የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ አገራቸው የያዘችውን አቓም በመንቀፍ ንግግራቸውን ጀመሩ።
በመሰረቱ አልጎር ለዓለም የአካባቢ ጥበቃ አንግበው የተነሱትን የተቀደሰ ዓላማ እንዲገፉበት የሚያበረታቱ አራት መቶ ሺህ የኤሌክትሮኒክስ መልዕክቶች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ ደርሷቸዋል።በእርግጥም አሁን ዓለም ትኩሳት ላይ ነው ያለችው።እናም ከባሊው የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ አንዳች ማረጋገጫ ይጠበቃል።
የአውሮጳ ህብረት እ.ኤ.አ. እስከ ሁለት ሺህ ሃያ ዓ.ም. ድረስ የአካባቢ አየር በካይ ጋዞችን ከሃያ አምስት እስከ አርባ በመቶ መቀነስ የሚያስችል ዕቅድ ለጉባኤው አቅርቧል።አሜሪካ በዋናነት ከግዙፍ ኢንዱስትሪዎችዋ የሚለቀቁትና አካባቢን የሚበክሉ አደገኛ ጋዞቹዋን በተባለው መጠንና ግዜ ለመቀነስ ፍላጎት የላትም።ይህም በመሆኑ ጉባኤው በውጥረት ተይዟል።ሆኖም አንዳንድ ምንጮች እንደገለጹት የአሜሪካና የአውሮጳ የአከባቢ ጥበቃን አስመልክቶ የገቡበት ፍጥጫ በሰከነ መልኩ በመልካም ውጤት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።