1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህር ላይ ዉንብድናን ለመቅረፍ የትምህርት ስልጠና

ማክሰኞ፣ ኅዳር 2 2007

የባህር ላይ ዉንብድናን ለማስቀረት የጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር ጅቡቲ ላይ በተቋቋመ የትምህርት ማሰልጠኛ ማዕከል ወጣቶችን በኮምፒዉተር የተደገፈ የትምርትና ስልጠና መስጠት ጀመረ።

https://p.dw.com/p/1DlMU
Eröffnung des E-Learning-Zentrums in Balbala, Dschibuti
ምስል SOS-Kinderdörfer weltweit

643ሺ ይሮ የሚያወጣዉና ጅቡቲ ላይ የተቋቋመዉ የማሰልጠኛ ማዕከል በጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር፤ በSOS የህጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲሁም በጀርመን የልማት ትብብር ተራድኦ ድርጅት በጋራ የተገነባ ነዉ። በማዕከሉ ስልጠናን ያገኙት ወጣቶች መርከብ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ስራ ላይ መሰማራትና ግልጋሎት መስጠት እንደሚችሉም ተገልፆአል። ዋና ጽ/ቤቱን ጀርመን ሃንቡርግ ላይ ያደረገዉ የጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር ቃል አቀባይን አነጋግረናል።
በአፍሪቃ ቀንድ የሚታየዉ የባህር ላይ ዉንብድና ባለፍት ጥቂት ዓመታት ሰከን ቢልም ችግሩ አሁንም አልተቀረፈም። የትምርት ስልጠናን እንደ መከላከያ መሳርያ በመዉሰድ የጀርመን የባለመርከቦች ማህበር «VDR» እና SOS የህጻናት ማሳደጊያ ድርጅት የባህር ላይ ወንብድናን ለመግታት አንድ የትምህርት ማዕከል ጅቡቲ ላይ አቋቁመዋል። ጅቡቲ ዉስጥ በተለይ ከሶማልያ የተሰደዱ ሰዎች በሚኖሩበት «ባልባላ» በተሰኘዉ የጅቡቲ ክፍለ ከተማ የተቋቋመዉ ማዕከል ባንድ ጊዜ 200 ታዳጊ ወጣቶችን የማሰልጠን አቅም እንዳለዉም ተነግሮለታል። የሶማልያ የባህር ላይ ወንበዴዎች ይህን ዉንብድና የሚፈጽሙት ተስፋ በመቁረጥ ነዉ ያሉት የጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር ቃል አቀባይ ክሪስቶቭ ሽቫነር ማሕበራቸዉ የትምህርት ስልጠናን የባሕር ላይ ዘረፋን ለማስቀረት እንደ አንድ መፍትሄ ይወስዳል።
« ስልጠና ለማድረግ ያነሳሳን የመጀመርያ ነገር በአፍሪቃ ቀንድ ባለፉት 10 ዓመታት ከ200 በላይ የንግድ መርከቦች በመጠለፋቸዉና በመዘረፋቸዉ ምክንያት ነዉ። በዚህ ዘረፋ ከ4000 በላይ የመርከብ ሰራተኞች እየታገቱ ተለቀዋል። እነዚህ ታጋቾች በእገታቸዉ ወቅት ከፍተኛ የአካልና የህሊና ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህም ምክንያት በአፍሪቃ ቀንድ ይህን የባህር ላይ ዉንብድና ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ለመቅረፍ የሆነ ነገር ማድረግ አለብን ብለን ተነሳን።»

በባህር ላይ የሚታየዉን ዉንብድና ለመቅረፍ፤ የችግሩን መነሻ የብስ ላይ እንዋጋለን ያሉት ክሪስቶቭ ሽቫነር፤ የስልጠና ማዕከሉ ባለፈዉ ወር ወጣቶችን በኮንፒዉተር በመደገፍ የሞያ ሥልጠና መጀመሩን ተናግረዋል። በጦርነት ከተመሳቀለችዉ ከሶማልያ ሸሽተዉ ጅቡቲ ለሚኖሩት አብዛኛ ሰዎች ይህ ማዕከል « የብሩኅ ተስፋ ምልክት » መሆኑንም ክሪስቶቭ ተናግረዋል። በሶማልያ የባህር ዳርቻ የሚታየዉ የባህር ላይ ዉንብድና በግል የባህር ላይ ጠባቂዎችና አካባቢዉን በሚቆጣጠረዉ በዓለም አቀፉ የጦር መርከብ የጥበቃ ስምሪት ሰከን ያለ ይመስላል። ይህ ጥበቃ መደረግ ከጀመረ ከሁለት ዓመት ወዲህ በሶማልያ የባህር ዳርቻ አካባቢ ምንም አይነት መርከብ ዘረፋ አልተከሰተም። ቢሆንም ይላሉ ክሪስቶቭ ሽቫነር በአፍሪቃ ቀንድ አሁንም ችግሩ አልተቀረፈም።

E-Learning-Zentrum vom VDR in Dschibuti eröffnet
የጅቡቲ የባህር ወደብምስል Christof Alexander Schwaner_VDR
E-Learning-Zentrum vom VDR in Dschibuti eröffnet
ጅቡቲ ባልባላ ክፍለከተማ የተቋቋመዉ የማሰልጠኛ ማዕከልምስል Christof Alexander Schwaner_VDR


« የባህር ላይ ዉንብድና በዓለማችን ከፍተኛ ችግር ነዉ፤ በአፍሪቃ ቀንድም አሁንም እጅግ አሳሳቢ ችግር ነዉ። በአፍሪቃዉ ቀንድ በዚህ ዓመት መርከቦች ላይ በርካታ ጥቃቶች ደርሰዋል። በባህር ላይ ወንበዴዎች ተኩስ ከፍተዉ ለመዝረፍ ሞክረዋል፤ ግን አልተሳካላቸዉም፤ ማፈንና ማገትም አልቻሉም። እንዲያም ሆኖ ግን ሁኔታዉ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ተጠናክረዉ እቦታዉ ላይ አሁንም እንደሚገኙ ያመላክታል። አካባቢዉ ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙት የባህር ላይ ጠባቂዎች ተልኮአቸዉን ሲያጠናቅቁ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ወድያዉ ጥቃታቸዉን እንደሚቀጥሉ እሙን ነዉ። ስለዚህም የባህር ላይ ዉንብድናን መዋጋት የሚቻለዉ፤ በአካባቢዉ ሃገራት ለሚገኙ ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታን በማስተካከል ነዉ»
የሶማልያ ጎረቤት በሆነችዉ የጅቡቲ መዲና ጅቡቲ ዉስጥ 570,000 የሶማሊያ ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል። የጅቡቲ ወደብ ኢትዮጵያን ከተቀረዉ ዓለም ጋር የሚያገናኝ ትልቅ በርም ነዉ። በቅርቡ በዚህ የወደብ ከተማ አዲስ የግዙፍ የባህር ጭነት ማራገፍያ ተገንቦታል። በዚህ ቦታ ላይ የመርከብ ሥራና የመርከብ ጥገና እንዲሁም የመርከብ ጭነት ሥራ መቆጣጠርያ ቢሮም ይገኛል። በፈጣን እድገት ላይ ባለችዉ በጅቡቲ በርካታ ወጣቶች በከተማዋ በሚገኘዉ ወደብ የስራ ቦታ ይፈልጋሉ። እናም ይላሉ የጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር ቃል አቀባይ ክሪስቶቭ ሽቫነር፤ ይህ የተቋቋመዉ የትምህርት ማዕከል ለነዚህ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት አካባቢዉ ላይ ስራ እንዲያገኙ እገዛን ይሰጣል።
« በጅቡቲ በተቋቋመዉ በኮምፒዉተር የተደገፈ ስልጠና በሚሰጥበት ማዕከል የ SOS የህጻናት ማሳደጊያ ድርጅትና ማኅበራችንን በጋራ በቀየስነዉ መረሃ-ግብር ስልጠና የሚያገኙት ወጣቶች ለረጅም ግዜ የሥራ ቦታን እንዲያገኙ የሚረዳ ስልጠናን እንዲያገኙ ነዉ። በጅቡቲ ከሶማልያ የፈለሱ በርካታ ስደተኞች ይኖራሉ። ይህ ተቋም በሚገኝበት በጅቡቲ ክፍለ ከተማ በ« ባልባላ» ከሶማልያ የተሰደዱ በርካታ ወጣቶች ይገኛሉ። አካባቢዉ ላይ ለሚኖረዉ ማኅበረሰብ በተቋሙ የትምህርት ሥልጠናን በመስጠት በባህር ወደብ ሥራ ላይ መሰማራት የሚችል ኃይል መገንባት እንደምንችል ማሳየት እንፈልጋለን። እደሚታወቀዉ የጅቡቲ የባህር ወደብ በአፍሪቃ ግዙፍ የእቃ ማመላለሻ ወደብ በመሆኑና በርካታ የስራ ቦታ ያለበት በመሆኑ እዚህ አካባቢ ላይ ሊሰማሩ የሚችሉ ወጣቶች ተቋማችን ስልጠና ሰጥቶ በቅርቡ በዚሁ በባህር ወደብ ላይ ስራ እንደሚጀምሩ ተስፋ አለን»
ጅቡቲ ላይ በተቋቋመዉ በዚህ ማዕከል ታዳጊ ወጣቶቹ የኮምፒዉተር አጠቃቀም መሰረታዊ እዉቀቶች ስልጠና ፤ የስራ ማመልከቻ አፃፃፍ እንዲሁም ስልጠናቸዉን መከታተል እንዲችሉ ትምህርት ይሰጣል። ከዝያ በተጨማሪ ወጣቶቹ ስራቸዉን በተመለከተ ለስልጠና የሚያስፈልጋቸዉን የኮምፒዉተር አጠቃቀም ፤ በኮምፒዉተር የሂሳብ ስራ እንዲሁም ቋንቋን እንደሚማሩ ተመልክቶአል። ይህ የሞያ ስልጠና አካባቢዉ ላይ በሥራ ለመሰማራት የሚያስፈልጋቸዉን ስልጠና እዉቀት ያገኛሉ።
ማዕከሉ ለሥራ ማስኬጃ በየዓመቱ የሚያስፈልገዉን 125.000 ይሮ የጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር እንደሚሸፍንና እስከ 2017 ዓ,ም ማዕከሉ የሥራ ማስኬጅያ የሚሆነዉ ወጭ የተሟላ መሆኑ ተመልክቶአል። እንደ የጀርመን የባለመርከቦች ማኅበር ጅቡቲ የስልጠና ማዕከሉ በተጠናከረ መልኩ በርካታ ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት በቀጣይ ሥራዉን ረዘም ላሉ ዓመታ ይቀጥላል።

E-Learning-Zentrum vom VDR in Dschibuti eröffnet
በጅቡቲ ወጣቶች በኮንፒዉተር ሥልጠና ላይምስል Christof Alexander Schwaner_VDR


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ