1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን-20 የመሪዎች ጉባዔ ስምምነት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 6 2007

አውስትራሊያ - ብሪስባን በተካሄደው እና ኹለት ቀናት በፈጀው የቡድን-20 የመሪዎችጉባኤ ላይ ተሳታፊዎቹ መሪዎች የዓለም አቀፉን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ መወሰድ በሚገባቸው ርምጃዎች ላይ ተስማሙ። ፑቲን ጉባኤው ሳይጠናቀቅ እስከ ሩስያ ረዥም ጉዞ ነው የሚፈጀው በሚል ምክንያት ጉባኤውን ጥለው መሄዳቸውም ይፋ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/1Do8n
ምስል Alain Jocard/AFP/Getty Images

እኢአ እስከ 2018 ዓም ድረስ ተጨማሪ 2, 1 በመቶ የሆነ እድገት የማስመዝገብ ግብ ማስቀመጣቸውም ተገልጿል። ከዚህም ሌላ የበለፀጉ እና በመበልፀግ ላይ ያሉት ሃገራት መሪዎች የግዙፍ ኩባንያዎች የግብር አከፋፈልን በተመለከተ ተወያይተዋል። በዚህም መሰረት በዓለም ዙሪያ ተሰራጭተው የሚገኙት ትላልቅ ድርጅቶች ግብር የሚከፍሉት ትርፉን ባገኙበት ሀገር ይሆናል። የጉባኤው ተሳታፊዎች የበርካታ ሚሊዮኖች ገንዘብ ባለቤት የሆኑ ግዙፍ ኩባንያዎች የግብር ማጭበርበርንም ለመዋጋት መቁረጣቸውን ገልፀዋል። የመሪዎቹም ቡድን በዚህ ጉባኤ ላይ የከባቢ አየር ብክለትን እንዴት በአግባቡ መከላከል ይቻላል የሚለው ነጥብ ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

G20 Gipfel in Brisbane Obama Abbott Abe
ምስል Reuters/K. Lamarque

በቡድን 20 አባል ሃገራት ጉባኤ የዩክሬይን ቀውስን አስመልክቶ በደረሰባቸው ብርቱ ወቀሳ የተነሳ የሩስያው ፕሬዚዳንት ጉባኤው ሳይጠናቀቅ አቋረጥው ሊወጡ እንደሚችሉ ትናንት ዝተው ነበር። ፑቲን እንደዛቱትም አልቀረ ጉባኤው ሳይጠናቀቅ አቋርጠው መሄዳቸው ተገልጿል።

በኢንዱስትሪ የበለፀጉት የቡድን-20 ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ የተከፈተው ትናንት በአውስትራሊያዋ የወደብ ከተማ ብሪስባን ነበር። የጉባዔው አብይ አጀንዳ ዓለም-አቀፉን የምጣኔ ሀብት ማጠናከር ሲሆን፤ G-20 ሃገራት መሪዎች ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል። የኤቦላ ወረርሽኝ እና ለራሱ «እስላማዊ መንግስት» የሚል ስያሜ የሰጠው ታጣቂ ቡድን ጉዳይ የጉባዔው መነጋገሪያ አጀንዳዎች ናቸው። በጉባዔው ተሳታፊ የሆኑት የጀርመን መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ከሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በግል ተገናኝተው መነጋገራቸውም ታውቋል። በሁለቱ መሪዎች መካከል ንግግሩ ያጠነጠነው የዩክሬይን ቀውስ የሚወገድበትን መፍትኄ በማፈላለግ ዙሪያ እንደነበረም ተጠቅሷል። አንጌላ ሜርክል የዩክሬይን ቀውስን በተመለከተ ድንገተኛ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማይጠብቁ ቀደም ሲል ገልጸዋል። የአውሮጳ ኅብረት ሩስያ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል ከጉባኤው ቀደም ብሎ መዛቱ ይታወቃል።

በዩክሬይን ቀውስ የተነሳ ምዕራባውያን ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር በመጨቃጨቃቸውም ጉባኤው ጥላ አጥልቶበት እንደነበር ተነግሯል። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፑቲን በዩክሬይን ላይ የሚያራምዱት ፖለቲካ ለዓለም ጦስ እንደሆነ በመግለፅ ተችተዋቸዋል። የሩሲያው አመራር ግን ይህንን ትችት አውግዘዋል። የአውሮጳ ኅብረት ሩስያ ላይ ዳግም ጠንከር ያለ ማዕቀብ እንደሚጥል ዝቷል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ