1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ

ሐሙስ፣ የካቲት 9 2009

የቡድን 20 አባል ሀገራት የዉጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጉባኤ በጀርመን ቦን ከተማ በዛሬዉ እለት ተጀመረ። ለሁለት ቀናት የሚዘልቀዉ የአባል ሀገራቱ ጉባኤ በዋናነት በአለም አቀፋዊ ዘላቂ ልማት ላይ የሚመክር ሲሆን፤ ለአፍሪካ የሚደረገዉ ድጋፍም ከአጀንዳወቹ መካካል አንዱ ነዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2Xi28
Deutschland G 20 Außenministertreffen in Bonn Gabriel und Boris Johnson
ምስል Getty Images/AFP/S. Schuermann

G20 diplomats to discuss development crises prevention - MP3-Stereo


ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀን የሚነጋገረዉ የ20ዎቹ ሐገራት የዉጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር እስከ 2030 ድረስ ገቢር ይሆናል የተባለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግብ ፍጥነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ማድረግ እንዲሁም የአፍሪካ የድጋፍ አሰጣጥ ጉዳይ ከአጀንዳወቹ መካከል መሆናቸዉ ታዉቋል።
በአለማችን የሚከሰቱ ቀዉሶችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮችም  ሌላዉ የተሰብሳቢዎቹ የመወያያ ነጥብ ነዉ ተብሏል። አለማችን ለሚገጥማት  ችግር ዉይይቱ አስፈላጊ ነዉ የሚሉት ስብሰባዉን በቅርብ የሚከታተሉት ጀርመናዊዉ ተደራዳሪ ላርስ ሄንድሪክ ሮለ ናቸዉ።
«በአለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ችግሮች አሉብን ። እንደማስበዉ፣ ለአለም አቀፍ ችግሮች አለም አቀፍ መፍትሄ ያስፈልጋል። እናም የቡድን 20 ጉባኤ ይህን የሚያግዝ መሆን አለበት። ንግድን በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ፣ ከሃገራት ጋር አብሮ መስራት፣  የጀርመን መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ ይሆናል።»

የቡድን 20 የወቅቱ ሊቀመንበር ጀርመን በበኩሏ ንግድ፤ የገንዘብ ገበያ ቁጥጥር ፣የአየር ንብረት ለዉጥ፣አለም አቀፍ ወረርሽኝ፣ሽብርተኝነት፣ ፍልሰትና  በተለይ በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር 2 ቢሊዮን ይደርሳል የተባለዉን አፍሪካን ህዝብ ዘላቂ የልማት እድገት ላይ በማተኮር አህጉሪቱን መደገፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ ይበልጥ ዉይይት እንዲረግበት ትጠይቃለች ተብሏል። በቡድን 20 የአፍሪካ አጋርነት ላይም  በመጭዉ ሰኔ  ልዩ ጉባኤ ታዘጋጃለች ሲሉ ሮለ ይገልጻሉ።

«በበርሊን ከተማ በመጭዉ እጎአ ሰኔ 12 እና 13፣ 2017 አፍሪካን  የተመለከተ ጉባኤ እናካሂዳለን።  ጉባኤው ከአፍሪካ ጋር የሚኖረውን አጋርነት በማስተዋወቅ ላይ ያተኩራል። የቡድን 20 የአፍሪካ አጋርነት፤  በአለም አቀፍ የልማት ተቋማት፣ የፋይናንስ እና የልማት ሚንስትሮች ፤ በቡድን 20 ሀገሮች አዉድ የሚዘጋጅ፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን፣ በተለይም፣ የመሰረተ ልማትን የሚያነቃቃ ይሆናል።»

Deutschland G 20 Außenministertreffen in Bonn Gabriel und Guterres
ምስል Getty Images/AFP/S. Schuermann

ዉሳኔወችን በማስተላለፍ ረገድ የሚታማዉ የቡድን 20 ጉባኤ ፤በጀርመን የሊቀመንበርነት ዘመንም ጠቃሚ ዉሳኔወችን ለማሳለፍ አስቸጋሪ እንደሆነ ከጀርመን የዉጭ ጉዳይ ማህበረሰብ ክላዉዲያ ሽሙከር ይናገራሉ። 
«የጀርመን የቡድን 20 መሪነት በአንጻራዊነት ሲታይ ጥላ ያጠላበት ነዉ። የአለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጥሩ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ከእያንዳንዱ ጉዳይ በስተጀርባ የቆመ አዲስ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ስላለ፣ ከዩኤስ አሜሪካ ጋር በአጋርነት እንዴት መስራት እንደሚቻል እንኳ አይታወቅም። ምርጫ በመጠባበቅ ለይ ነን፣ የቡድን 20 ጉባኤንም በጣም ቀደም ብለን  በሰኔ ወር እናካሂዳለን። እናም ይህ ሁሉ ጠቃሚ ዉሳኔዎችን ማስተላለፍን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል።»

የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ አቅማቸዉ ጠንካራ የሆኑ ሃገራት ስብስብ የሆነዉ ቡድን 20 መደበኛ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ፤የአባል ሀገራቱ ዲፕሎማቶችና ሌሎች የጉባኤዉ ተካፋዮች የሁለትዮሽ ዉይይት አካሂደዋል።በመሆኑ ይህን መሰሉ ዉይይት ለአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር  ለሪክስ ቴለርሰን  እንደ ሩሲያ፣ታላቋ ብሪታንያና ቱርክ የመሳሰሉ ቁልፍ ዲፕሎማሲያዊ ቦታ ያላቸዉን ሀገሮች የዉጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ለማግኘት ትልቅ እድል የሚከፍት መሆኑ  ተገልጿል።
ቡድን 20 በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር በ1999 የተመሰረተ ሲሆን 80 በመቶ የሚሆነዉ የአለም ጠቅላላ ምርትና ንግድ በአባል ሀገራቱ የተያዘ መሆኑን የተለያዩ መረጃወች ያመለክታሉ።

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ