1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሽ ጀምበር ጠለቀች-የኦባማ በረቀች

ሰኞ፣ ጥር 11 2001

ታሊባን-አልቃኢዳዎች ዛሬም በሰባት አመታቸዉ ሊጠፉ ቀርቶ-እራሳቸዉ ቡሽ እንዳሉት ለሌላ ጥቃት ያሰጋሉ።

https://p.dw.com/p/GbWE
"Good bye-Bush"ምስል AP

19 01 09

ከነገ-ጀምሮ የሐያሎች-ሐያል፣ የክቡሮች-ክቡርነታቸዉ ሥልጣን-«የቀድሞዉ በሚል ቀዳሚ ቅፅል የሚገፈፈዉ ጆርጅ ዎከር ቡሽ የከንግዲሕ መዘከሪያቸዉን ባለፈዉ ሐሙስ ሲዘክሩ ከዚያች ቀን ጀመሩ።

ድምፅ (ቡሽ)

«በዚሕ ምሽት እዚሕ ቤት ሳገኛችሁ፥ ከዚሁ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ለናንተ ንግግር ያደረኩባትን ዕለት ታስታዉሰኛለች።መስከረም አንድ -1994።

Good bye-Bush ይላል አሜሪካ

ድምፅ ኦባማ

«ወደ ዋሽንግተን እንኳን ደሕና መጣችሁ።ለአሜሪካ ተሐድሶ በሚደረገዉ በአል ለመካፈል እንኳን ደሕና መጣችሁ።»

Barack Obama Rede an der Uni Fairfax USA
Welcome-Obamaምስል AP

ዋይት ሐዉስት ለአርባ-አራተኛ ጊዜ ተቀየረ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።አሜሪካ-አለም ይቀየሩ ይሆን።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ድምፅ (ቡሽ)

«በዚያች እለት ጧት ከፐርል ወደብ ጥቃት ጥቃት ወዲሕ በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸባሪዎች ባደረሱት ጥቃት የሰወስት ሺሕ ያሕል ሰዎች ሕይወት አጥፍተዋል።»

በርግጥም የጃፓን ጦር ፐርል ወደብ ሰፍሮ የነበረዉን የዩናይትድ ስቴትስን ባሕር ወለድ ጦር ድንገት ሳይታሰብ ዶጋ-አመድ ካደረገበት ጊዜ ወዲሕ የትልቂቱ ሐገር፣ ትልቅ ሐብታም፣ ደግ ሕዝብ፣ በታላቅ ምድሩ፣ ሲሸበር-ሲገደል የመጀመሪያዉ-ቢያንስ እስካሁን የመጨረሻዉም ነዉ።

ናይን-ኢለቨን እንደነሱዉ።

ከ1939 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ አዉሮጳን ያነድ በነበረዉ ጦርነት ብሪታንያንና መሰል ወዳጆችዋን ከመርዳት በስተቀር በቀጥታ መሳተፉን ያልፈቀደችዉ ትልቅ ሐገር ከትልቁ ጦርነት የመግባትዋ-ሰበብ ምክንያት ታሕሳስ-ሰባት 1941 በጃፓን ጦር መደብደቧ ነበር።

ፕሬዝዳት ፍራንክሊን ሩዝቬልትና ተከታዮቻቸዉ ከጦርነቱ ሲገቡ የተከተሉት ሥልት ሐገራቸዉንና ተከታዮችዋን ባጭር ጊዜ ለድል አብቅቷቸዋል።በድል ማግስት አለም እስከዚያ ዘመን እንደምታዉቀዉ የተሸናፊዎችን ሐገር ከመግዛት፤ ሕዝቡን ከማስገበር ተቃርኖ የአሜሪካን ገንዘብ፤ እዉቀት፤ የፖለቲካ ሥልት ሲያካፍሉ የሐገራቸዉን ታላቅነት አስመከሩ።ታላቅ ሐገራቸዉን ተገድደዉ-ፈርተዉ፤ ሳይሆን ወደዉ-አፍቅረዋት-የሚወዳጇት ታላላቅ ሕዝብ መንግሥታን አተረፉ።የአለምን ሁለንተናዊ ሒደት ለወጡ።

የተለወጠችዉ አለም ሕዝብ ኒኮሌር በሚያሚያማዝዝ፣ የኮሚንስት ካፒታሊስቶች ፍጥጫ መሸማቀቀቁ፣ በጦርነት፤ በረሐብ፤ በበሽታ ማለቁ፣ በፍትሕ እጦት መንገላታቱ በርግጥ አልቀረም።ከቅኝ ተገዢዎች ነፃ መዉጣት፣ እስከ ዘር-እኩልነት፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመስረት፣ እስከ ሰብአዊ መብት ፅንሰ ሐሳብ ስርፀት አለም ያየችዉ ለዉጥ-በጎ ከሆነ የለዉጡ ሰበብ-የፐርል ሐርበር መደብደብ፤ የበጎነቱ መሠረት የነ-ሩዝቬልት መርሕ መሆኑ አያጠያይቅም።

ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በሁለት ሺሕ አራት ለሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን ከመመረጣቸዉ ከሁለት ወራት በፊት ያነገራቸዉ የታይም መፅሔት ዘጋቢ እንደሚለዉ ታሪክ ማንበብ ይወዳሉ። የቀዳሚዎቻቸዉን ድል፣ገድል፤ ምግባር ዉጤት እንደ ሥልጣን ወራሽ፣ እንደ ሐገር ልጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ታሪክ አንባቢም ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት ቡሽ የጃፖኖች ጥቃት-ለነሩዝቬልት እንደነበረ ሁሉ የመስከረም-ሁለት ሺ አንዱ የአሸባሪዎች ጥቃት የሳቸዉ አደራ መሆኑን አላጡም።

በርግጥም የፐርል ወደቡ ጥቃት አለምን ለዉጦ እንደነበረ ሁሉ የመስከረም-1994ቱ የሸባሪዎች ጥቃት አለምን መለዉጡ አያነጋግርም።የለዉጡ ልዩነት ከዘመኑ ርዝመት በሰፋ ርቀት መቃረኑ እንጂ ድንቀቱ።

ድምፅ (ሙዚቃ)

ከነገ-ጀምሮ ሴናተር ወይም ተመራጭ የሚለዉን ቀዳሚ ቅፅል ጥለዉ-የሐያሊቱን ሐገር ሐያል ሥልጣን የሚይዙት ባራክ ሁሴይን ኦባማ ገና ከነሳሳቸዉ ለዉጥ-ይቻላልም ብለዉ ነዉ የተነሱት።ትናንት ዋሽንግተን ሲገቡ እንዳሉት ግን ያሉ ያቀዱ-ቃል የገቡትን ገቢር ለማድረግ ጉዞዉ ቀላል እንደማይሆን አላጡም።ተስፋም አላቸዉ።

ድምፅ (ኦባማ)

«የሚገጥመን ፈተና እጅግ ከባድ ቢሆንም ዛሬ እዚሕ የቆሙኩት ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ፈተናዉን ትቋቋመዋለች፥ ታልፈዋለች፥የመስራቾቻችን ሕልም አለማ በኛም ይሰርፃል በሚል ከመቼዉም ጊዜ በላቀ ሙሉ ተስፋ ነዉ።»

ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊ ቡሽ ታሪክ አንባቢነታቸዉን ለዘገበላቸዉ ጋዜጠኛ ያኔዉኑ እንደነገሩት እሳቸዉ ታሪክ አዋቂ አይደለም።ታሪክ ሰሪ እንጂ።የሰሩትን ታሪክ ባለፈዉ ባለፈዉ ሐሙስ ዘከሩት።

ድምፅ (ቡሽ)

«አፍቃኒስታን ታሊባን አል-ቃኢዳን ከሚያስተናግድባት፥ ሴቶች በአደባባይ ከሚወገሩባት ሐገርነት ወደ ወጣት ዲሞክራሲያዊነት ተሻግራለች።አሸባሪዎችን የምትዋጋ፥ ልጃገረዶች እንዲማሩ የምታበረታታ ሐገር ሆናለች።»

ፕሬዝዳንት ፍራክሊን ዲ ሩዘቬልትና ተከታዮቻቸዉ ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ሲገቡ ጨፍጫፊ፣ አረመኔ ከሚባሉት ከጆሴፍ ስታሊን ጋር ሳይቀር ተደራድረዉ፣ ጠላት የምትባለዋን የስታሊኗን ሶቬት ሕብረትን ከጎናቸዉ አሰልፈዉ ሥለነበረ ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ አራት አመት አልፈጀባቸዉም ነበር።

በሁለት ሺሕ አንድ ለፀረ-ሽብር ዘመቻ ሲዘመት ፕሬዝዳት ቡሽ የቅርቡን ትልቅ ጠላት ለማጥፋት ከሩቁ ትንሽ የማበሩን የነሩዘቬልትን አስተምሕሮት፥ ድፍን አለምን «አንድም ከኛ አለያም ከጠላቶቻቸዉን»-በሚል ዛቻ ነበር-የቀየሩት።እስካፍንጫቸዉ የታጠቁትን የናትሴ ጀርመንን፣ የፋሺስት ኢጣሊያን፣ የወታደራዊት የጃፓንን ለማሸነፍ-አራት አመት የፈጀዉ።

ከክላሺንኮቭ፣ ከእጅ ቦምብ ሮኬት ያለፈ ብዙ መሳሪያ ያልታጠቁት ታሊባን-አልቃኢዳዎች ዛሬም በሰባት አመታቸዉ ሊጠፉ ቀርቶ-እራሳቸዉ ቡሽ እንዳሉት ለሌላ ጥቃት ያሰጋሉ።

ድምፅ (ቡሽ)

«ጠላቶቻችን ታጋሾች ናቸዉ።ዳግም ለማጥቃትም ቁርጠኞች ናቸዉ።»

የቡሹ-ኻርዛይ የኻርዛይዋ አፍቃኒስታን ባለፉት ሰባት አመታት ከሐምሳ-ሺ በላይ ዜጎችዋ አልቀዉባታል።ከስድስት መቶ-የሚበልጡ የአሜሪካ፣ ከሰወስት መቶ ሰማንያ በላይ የተባባሪዎችዋ ሐገራት ወታደሮች ተገድለዉባታል።ከሰወስት ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ቆስለዉባታል።ለጦርነት በየወሩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይከሰከስባታል።አደንዛዥ እፅ በገፍ ይዛቅባታል።በኦፕየም አምራችነት ከአለም አንደኛ ናት።

ድምፅ (ቡሽ)

«ኢራቅ በአረመኔ አምባገነን፥ በአሜሪካ ቀንደኛ ጠላት ከመመራት በመካከለኛዉ ምሥራቅ እምብርት ወደሚገኝ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፥ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ወዳጅነት ተጉዛለች።»

የኢራቅ ከሳዳም-ሁሴን አረመኔያዊ አገዛዝ በርግጥ ተገላግሏል።በሁለት ሺሕ ሰወስት ከሳዳም ከተገላገለበት ቡሽን እስከሚሰናበት ዘንድሮ-ወታደር፤ ፖሊስ ደፈጣ ተዋጊ የነበሩ ከአርባ-ሺሕ የሚበልጡ ወገኖቹ ተገድለዉበታል።አርባ-ሁለት ሺሕ ታስረዉበታል።የተገደለዉ ሰላማዊዉ ኢራቃዊ ቁጥር ቁጥር ካንድ ሚሊዮን በልጧል።

የአምስት ሚሊዮን ሕፃናት እናት አባት ተገድለዋል።4.7 ሚሊዮን ኢራቃዊ ቡሽን የሚሰናበተዉ በከሚናፍቃት ሐገሩ ዉጪ ከየስተደኛዉ ጣቢያ ነዉ።ለዚሕ ዉጤት ከአራት ሺሕ ሁለት መቶ የሚበልጥ-የአሜሪካ፣ አንድ መቶ ሰባ-ስምንት የብሪታንያ፤ አንድ መቶ ሰላሳ ዘጠኝ የተባባሪዎቻቸዉ ሐገራት ወታደሮች ሕወታቸዉን፣ ከአርባ ሺሕ የሚበልጡ አካላቸዉን ገብረዋል።ከሰላሳ-ሺሕ በላይ አዕምሮ ጤናቸዉን አጥተዋል።

የአሜሪካ ሕዝብ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ከስክሷል።ፕሬዝዳት ቡሽ የሚሰናበቷት አሜሪካ በሁለት ጦርነት የተጠመደች፥ ምጣኔ ሐብቷ የደቀቀ፥ በሰባአዊ መብት ረጋጭነት የተወቀሰች፥የተፈጥሮ ጥበቃ ደንብን የጣሰች ሐገር ናት።ይሕ ነዉ የኦባማዋ-አሜሪካ የአሜሪካዋ-አለም የከንግዲሕ ታላቅ ፈተና።

ድምፅ (ኦባማ

«በታሪካችን አሁን እኛ ያጋጠመንን ፈተና አይነት ከባድ ፈተና ያጋጠማቸዉ ትዉልዶች በጣም ጥቂቶች ናቸዉ።ሐገራችን ጦርነት ዉስጥ ናት።ምጣኔ ሐብታችን ደቅቋል።በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዉያን ሥራቸዉን፥ ቤታቸዉን እያጡ ነዉ።ለልጆቻቸዉ የትምሕርት ቤት ወጪ መክፈል አይችሉም።»

ድምፅ (ሙዚቃ)

ብዙዎች እንደሚሉት ፕሬዝዳት ቡሽ አለምን-የሚሰናበቱት በአሜሪካ ታሪክ እጅግ የሚጠሉ መሪ ሆነዉ ነዉ።በቅርቡ የተሰባሰበ የሕዝብ አስተያየት እንደሚጠቁመዉ ከአሜሪካ ሕዝብ የቡሽን አመራር ጥሩነት የሚቀበለዉ ሃያ-ሁለት ከመቶዉ ብቻ ነዉ።ጥሩዉ ነገር-አሜሪካ፥ አለምም Good Bye አላቸዉ።አሉትም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Negash Mohammed

Quellen:- DW,Time Megazin September (6?)2004,Wikipedia,ZPR 160109 usa bosh &190109 obama 2 lincoln memorial (nur ö-Töne)