1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡርኪና ፋሶ ምርጫ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 5 2007

ከ27 አመታት መንበረ ስልጣናቸው ብሌዝ ኮምፓዎሬን በአደባባይ ተቃውሞ ያባረሩት የቡርኪና ፋሶ ዜጎች ከሁለት ወራት በኋላ አዲስ ፕሬዝዳንት ይመርጣሉ። ከዓለም ደሐ አገሮች ተርታ የምትመደበው ቡርኪና ፋሶ ግን ምርጫ ማካሄድ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ለውጥም እንደሚያስፈልጋት የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያምናሉ።

https://p.dw.com/p/1GDa8
Burkina Faso Jubel nach dem Rücktritt des Präsidenten Compaore 31.10.2014
ምስል AFP/Getty Images/I. Sanogo

[No title]

ከአንድ አመት በፊት የቡርኪና ፋሶ ዜጎች አደባባይ ሲወጡ ተቃውሟቸው ተራማጅ ነበሩ የሚባልላቸውን ቶማስ ሳንካራን እአአ በ1987 ዓም በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደው ለ27 አመታት በስልጣን በቆዩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ ላይ ብቻ አልነበረም። የአገሪቱ ድህነት እና ከ17 ሚሊዮን ህዝብ ስድሳ በመቶ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለትን ወጣት የሚፈትነው ስራ አጥነት ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች ነበሩ። የወደብ አልባዋ ቡርኪና ፋሶ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ ጥገኛ ሲሆን፣ እንደ የዓለም ባንክ መረጃ፣ አመታዊ እድገቷ ሶስት በመቶ ብቻ ሆኖ ለአመታት ቆይቷል። እናም ለቡርኪና ፋሶ ወጣቶች የብሌዝ ኮምፓዎሬ ከስልጣን መልቀቅ ብቻ በቂ አይደለም። ለውጥ ይናፍቃሉ። ለውጥ ይፈልጋሉ።

ብዙዎች ከሁለት ወራት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ይዞ የሚመጣው አዲስ መሪ ብቻ ሳይሆን የአዲስ ዘመን ብስራት ጭምር ነው ብለው ተስፋ አድርገዋል። ለቡርኪና ፋሶ ዜጎች ብሌዝ ኮምፓዎሬና ትናንት እንዳይመለሱ ሆነው አልፈዋል። እንመለስ ቢሉም አይፈቅዱላቸውም።

Burkina Faso - Demonstrationen gegen den Präsidenten.
ምስል Getty Images/I. Sanogo

የቡርኪና ፋሶ ዜጎች በጉጉት የሚጠብቁት አገራዊ ምርጫ ለፕሬዝዳንታዊው መንበረ ስልጣን አስራ አንድ እጩዎች ይወዳደሩበታል። ምናልባትም ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሳያስፈልገው አይቀርም። አብረውት ግን ስጋቶች መምጣታቸው እንደማይቀር ነው አሊ ሳኑ የቡርኪናቤ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ዋና ጸሃፊ የሚገምቱት።
«ፖለቲከኞቻችን ራሳቸውን ዴሞክራት እንደሆኑ ይገልጻሉ። አተያያቸው ግን ዴሞክራሲያዊ አይደለም። ዴሞክራት ሽንፈቱን ይቀበላል። ዛሬ ሁሉም ባለድርሻዎች ሽንፈትን ይቀበላሉ ማለት አልችልም። ሲቪል ድርጅቶች ወገንተኛ ሳይሆኑ፣ ሰላምና መረጋጋት ለአገሪቱ እጅግ ጠቃሚ ነገሮች መሆናቸውን የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው። »

ብሌዝ ኮምፓዎሬን ከስልጣን ካወረደው የአደባባይ ተቃውሞ በኋላ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚሼል ካፋንዶ የሽግግር ፕሬዝዳንት ሆነው ቢሾሙም ቁልፉ ስልጣን በፕሬዝዳንታዊ የደህንነት ጥበቃ ክፍለ ጦር እጅ እንደሆነ ይነገራል። እጅጉን የሰለጠኑ ወታደሮች እና ዘመናዊ ትጥቆች ያሉት ይህ ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሎኔል ኢሳክ ዚዳ ከመንግስታዊ መዋቅር እንዲባረሩ እስከ መጠየቅ ደርሷል። ኮምፓዎሬ ከስልጣን ሲባረሩ ለአጭር ጊዜ በመሪነት የቆዩት ኮሎኔል ኢሳክ ዚዳም ለቡርኪና ፋሶ ደህንነት ሲባል መፈንቅለ መንግስት ሞክሮብኛል ያሉት ክፍለ ጦር ከማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲታገድ ጠይቀው ነበር። በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ትንቅንቅ የሚሼል ካፋንዶን ስልጣን ገድቦታል። ክፍለ ጦሩ ከአንድ ኦመት በፊት በብሌዝ ኮምፓዎሬ ላይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለሞቱት 24 ሰዎች እና 600 ቁስለኞች ተጠያቂ ሆኖዋል።

Blaise Compaoré Präsident Burkina Faso
ምስል AP

በቡርኪና ፋሶ የሽግግር መንግስት ከብሌዝ ኮምፓዎሬ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ከምርጫው ታግደው የነበሩት ግለሰቦችና ተቋማት፣ እግዱ በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፣ ኤኮዋስ ውሳኔ ተነስቶላቸዋል። ይሁንና፣ እንደ አሊ ሳኑ ከሆነ፣ የቡርኪና ፋሶ ምርጫ ማካሄድ ብቻውን ካለ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ዋጋ አይኖረውም።።
«በዚህ ምርጫ ከሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዳቸውም ቡርኪና ፋሶ የምትገኝበትን ኋላ ቀርነት ለመታገል የሚያስችል እቅድ የላቸውም። አገሪቱ በበቂ ሁኔታ እስካላደገች እና ደሐ እስከሆነች ድረስ፣ ከምርጫውም በኋላ ተዓምር ይፈጠራል ብዬ አልጠብቅም።»

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ