1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ ውዝግብ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2007

ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ፣ ለ3ኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ቆርጠው በተነሱባት የቡሩንዲ ባለፈው ሰኞ የተካሄደው አወዛጋቢ ብሔራዊ እና የከተሞች አስተዳደር ምክር ቤታዊ ምርጫ ነፃ እና ትክክለኛ አይደለም ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣጣለው።

https://p.dw.com/p/1FsfM
Burundi Imbonerakure Miliz
ምስል Getty Images/AFP/C. de Souza

ተቃዋሚዎች ያልተሳተፉበት የሰኞው የቡሩንዲ ምርጫ ፍርሀት የሰፈነበት እና የመንግሥቱ ተቃዋሚዎችም ላይ ብርቱ ክትትል ያረፈበት እና በነፃ የምርጫ ዘመቻ ማካሄድ ያልቻሉበት እንደነበረ ነው ያለሙ መንግሥታት ታዛቢ ቡድን ያስታወቀው። እንደ ታዛቢው ቡድን ግምት፣ በፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ የሚመራው በምህፃሩ «ሲኤንዲዲ-ኤፍዲዲ» የተባለው ገዢው ፓርቲ የብዙኃኑን ድምፅ በማግኘት እንደሚያሸንፍ ይጠበቃል። የተመድ ዋና ጸሀፊ ፓን ኪ ሙን የቡሩንዲ ምርጫ በጠቅላላ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ያቀረቡትን ጥያቄ የቡሩንዲ መንግሥት ሳይቀበለው መቅረቱ ይታወሳል።

Burundi Sicherheitsmaßnahmen
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

ባለፈው ረቡዕ ከመዲናይቱ ቡጁምቡራ አቅራቢያ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛን የሚቃወሙ ወገኖች በብዛት በሚገኙበት በሲቢቶኬ ቀበሌ በፖሊስ እና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ቢያንስ ስድስት ሲቭሎችን እና አንድ ፖሊስ ከተገደሉ ወዲህ በመዲናዋ ጭንቀት ያልተለየው ፀጥታ ሰፍኗል።

ቡሩንዲ ውስጥ የፕሬዚደንቱ ለ3ኛ ጊዜ የመወዳደር እቅድ ካለፉት ብዙ ወራት ወዲህ በሲቭሉ ሕዝብ ዘንድ ፍርሀት እና የኃይሉን ተግባር ያስፋፋ ሲሆን፣ ወደ 130,000 የቡሩንዲ ዜጎች የኃይሉን ተግባር በመሸሽ ሀገር ለቀው ተሰደዋል። የተመድ ፣ የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ህብረት እንደ ምክር ቤታዊውን ምርጫ እንዳወገዙ ሁሉ፣ እአአ የፊታችን ሀምሌ 15፣ 2015 ዓም የሚደረገውን አወዛጋቢውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫም ሆነ ውጤቱን እንደማይቀበሉ ከወዲሁ አስታውቀዋል።

ተቃውሞው ከያግጣጫው ቢያይልም፣ በፀጥታ ኃይላቸው እና ባስታጠቁዋቸው « ኢምቦኔራኩሬ» በሚል መጠሪያ በሚታወቁት ሚሊሺያዎቻቸው የሚተማመኑት ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ምርጫውን ማካሄዳቸው እንደማይቀር የተቃዋሚ ቡድን መሪ ሻርል ንዲቲጄ አስታውቀዋል።

የተመድ ቀደም ሲል ከቡሩንዲ የሸሹ ስደተኞችን በመጥቀስ ባወጣው ዘገባው፣ ይኸው ለመንግሥቱ ቅርብ የሆነው ቡድን በሀገሪቱ ለሚፈፀመው ግድያ፣ እገታ እና ቁም ስቅል ተጠያቂ መሆኑን አመልክቶዋል። በቡሩንዲ አዲስ የርስበርስ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲልም ስጋቱን ገልጾዋል። የገዢው ፓርቲ በሥልጣን የመቆየትን ዓላማ እውን ለማድረግ ተቋቋመ የሚባለው የ« ኢምቦኔራኩሬ» የኃይል ተግባር ሰለባ ከሆኑት እና አሁን በስደት ከሚገኑት መካከል አንዷ የሆነችው የራድዮ ጋዜጠኛ ዶሚቲል ኪራምቩ የሚሊሺያዎቹን ግፍ እንዲህ ታስታውሳለች።

Domitille Kiramvu
የራድዮ ጋዜጠኛ ዶሚቲል ኪራምቩምስል DW

« ሀገሬን ጥዬ እንድሸሽ ያስገደዱኝ የፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ መንግሥት እና የ« ኢምቦኔራኩሬ» ሚሊሺያዎች ናቸው። ባንዳንዶቹ ሚሊሺያዎች እና ባንዳንድ ፖሊሶች ብዙ ጊዜ የሞት ዛቻ ቀርቦብኛል። »
በተለይ ባለፉት ወራት የሽብር ጥቃቱን ያስፋፋውን የ« ኢምቦኔራኩሬ» ሚሊሺያ ቡድን የሚያስታጥቀው መንግሥት መሆኑን የተቃዋሚ ቡድኖች ቢያስታውቁም፣ የቡድኑ ተወካይ ዴኒ ካሬራ ቡድናቸው ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ መሆኑን በማመልከት ወቀሳውን ውድቅ አድርገዋል።

« መሆን ያለበት የሰነዘሩት ወቀሳ እውነት መሆን አለመሆኑን ማጣራትይገባቸዋል፣ እኔ የኃይሉን ተግባር እቃወማለሁ። የኃይሉን ተግባር የሚፈፅም ማንንም ሰው ደግሞ በፍፁም አልደግፍም። »

« ኢምቦኔራኩሬ» የተቃዋሚ ቡድኖች የገዢውን ፓርቲ እንዲቀላቀሉ ያስገድዳል በሚል ተቃዋሚዎች የሚያሰሙትንም ወቀሳ ዴኒ መሠረተ ቢስ ብለውታል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ