1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ ውዝግብ እና የሰላም ማፈላለጉ ጥረት

ረቡዕ፣ የካቲት 16 2008

10 ወራት የዘለቀዉን የቡሩንዲን ውዝግብ ለማብቃት ዲፕሎማሲያዊው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሎዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙን ትናንት በመዲናይቱ ቡጁምቡራ ከፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ጋር ያካሄዱት ውይይት ተስፋ ሰጪ ውጤት አስገኝቶዋል።

https://p.dw.com/p/1I1Ap
Burundi Ban Ki-moon & Präsident Pierre Nkurunziza
ምስል picture-alliance/AP Photo

[No title]

በዚሁ መሰረት፣ ንኩሩንዚዛ ከተቃዋሚ ቡድን ፖለቲከኞች ጋር ውይይት በማካሄድ በሀገሪቱ የቀጠለውን ውዝግብ ለማብቃት ተስማምተዋል። አንድ የአፍሪቃ ህብረት የልዑካን ቡድን የቡሩንዲን ተቀናቃኝ ወገኖች ማቀራረብ ስለሚቻልበት ጉዳይ ለመምከር በነገው ዕለት ወደዚችው ሀገር እንደሚያመራ ተሰምቶዋል።

በቡሩንዲ ለቀጠለው ውዝግብ መፍትሔ ለማፈላለግ ባለፉት ሁለት ቀናት በዚችው የማዕከላይ አፍሪቃ ሀገር መዲና ቡጁምቡራ ጉብኝት ያደረጉት የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙን በዚያ ከፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ እና ከመንግሥቱ ተቃዋሚዎች ጋር ያደረጉት ውይይት አበረታቺ መሆኑን አስታውቀዋል። ፓን ኪ ሙን ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ተቀናቃኞቹ ወገኖች 10 ወራት የሆነውን እና ቡሩንዲን ወደከፋ ቀውስ ያስገባውን ውዝግብ ለማብቃት አስፈላጊ ነው ያሉትን ውይይት ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸውን አሞግሰዋል።
« የቡሩንዲ መንግሥት ወይም የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እና የተቃዋሚው ወገን ፖለቲካ መሪዎች ሁሉን በሚያሳትፍ ውይይት ለመደራደር ቃል መግባታቸውን አበረታቺ ርምጃ ሆኖ አግንቼዋለሁ። ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ይህን አረጋግጠውልኛል። ተቀናቃኞቹ ወገኖች የሀገራቸውን የወደፊት ዕጣ የሚመለከተውን ይህንኑ ጎዳና ከመከተል የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም። »


የቡሩንዲ መንግሥት ባለፉት ወራት በሁከቱ ሰበብ በቁጥጥር የዋሉ 2,000 እስረኞችን ለመፍታት፣ በ15 የተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የሲቭል ማህበረሰብ እና የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ላይ ያሳለፈውን ዓለም አቀፍ የእስር ትዕዛዝን ለመሻር እና ተዘግተው የነበሩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትንም መልሶ ለመክፈት በወሰደው ውሳኔ መደሰታቸውን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል። እንደሚታወሰው፣ የቡሩንዲ መንግሥት ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በ40 የእስር ማዘዣ አውጥቶዋል።
« ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ ያረፈውን እገዳ ለማንሳት፣ የእስር ማዘዣዎችን ለመሻር እና እስረኞችን ለመፍታት የወሰዱትን ውሳኔ በደስታ ተቀብያለሁ። ፕሬዚደንቱ የ12,000 እስረኞችን ስም ዝርዝር እንደሚያወጡ እና ተጨማሪ ርምጃዎችም እንደሚወስዱ ገልጸውልኛል። ይህን ቃላቸውን በተግባር እንደሚተረጉሙትም ተስፋ አደርጋለሁ። »

በሀገራቸው እና በተመድ መካከል ያለውን ትብብር ያሞገሱት የቡሩንዲ ፕሬዚደንት መንግሥታቸው አሸባሪ ከሚላቸው ወገኖች ጋር እንደማይደራደር በግልጽ አስታውቀው፣ የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ለውይይቱ ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
« በቡሩንዲ ዜጎች መካከል በሚካሄደው ውይይት ወቅት የተመድ እንዲተባበር ጠይቀናል። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔ አንቀጽ 2248 እንደሚለው፣ ውይይቱ በሀገሪቱ አለመረጋጋት ለመፍጠር ከሚሰሩት በስተቀር ሁሉን የቡሩንዲ ዜጎችን ለማቀራረብ የሚረዳ እንዲሆን ቡሩንዲ እና የተመድ ተስማምተዋል። »
ይሁንና፣ እንደ ቡሩንዲ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ በምህፃሩ «ፍሮዴቢዩ» የተባለው የተቃዋሚው ፓርቲ ሊቀ መንበር ሌዎንስ ንጌንዳኩማና አስተያየት፣ ባለፈው ግንቦት ወር የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ግለሰቦችም በውይይቱ መሳተፍ ይገባቸዋል።
« በቡሩንዲ ሕዝብ መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ እና ሀገሪቱ መልሳ እንድትረጋጋ ዕድል ለመስጠት ከተፈለገ የተመድ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት በውይይቱ የሚሳተፉበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚኖርበት፣ ድርድሩም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ ለፓን ኪ ሙን ነግረናቸዋል። »
ከዋና ጸሐፊው ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጎረቤት ርዋንዳ በቡሩንዲ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች ሲሉ ወቀሳ ቢያሰሚሙም፣ ርዋንዳ ወቀሳውን ሀሰት ስትል አስተባብላለች።
ለቡሩንዲ ሰላም ለማውረድ የተጀመረውን ጥረት ለማነቃቃት በደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ የሚመራ አንድ የአፍሪቃ ህብረት የልዑካን ቡድን በነገው ዕለት ነገ ሀሙስ፣ የካቲት 17፣ 2008 ዓም ቡጁምቡራ ይገባል። የሞሪታንያ ፣ የሴኔጋል እና የጋቦ ፕሬዚደንቶች መሀመድ ኡልድ አብደልአዚዝ፣ ማኪ ሳል እና አሊ ቦንጎ ኦንዲምባ፣ እንዲሁም፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚጠቃለሉበት የልዑካኑ ቡድን በቡጁምቡራ በሚቆይባቸው ሁለት ቀናት የቡሩንዲን ተቀናቃኝ ወገኖች ማቀራረብ ስለሚቻልበት ጉዳይ ይመክራል።

አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ

08.09.2014 DW online Karte Burundi Bujumbura
Burundi Ban Ki-moon & Präsident Pierre Nkurunziza
ምስል Reuters/E. Ngendakumana