1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ መንግስትና የአማፅያኑ ስምምነት

ሰኞ፣ ሰኔ 12 1998

በቡሩንዲ መንግስት እና በመካከለኛ አፍሪካ የሚንቀሳቀሰዉ አማጺ ቡድን መካከል ግጭትን የማብረድ ስምምነት ተፈረመ።

https://p.dw.com/p/E0ia
ፕሬዝደንት ፒየር እንኩሪንዚዛ
ፕሬዝደንት ፒየር እንኩሪንዚዛምስል AP

ይህም ዉል በአካባቢዉ ለ13 ዓመታት ሲካሄድ የኖረዉን የእርስ በርስ ጦርነት እልባት ወደሚያገኝበት የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያመራ እንደሚሆን ተገምቷል።
በታንዛንያ ርዕሰ መዲና ስምምነቱን የተፈራረሙት የቡሩንዲ መንግስትና የብሄራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር ማለትም በምህፃሩ FNL ናቸዉ።

ቅዳሜ ዕለት ይፈረማል ተብሎ የታሰበዉ ይህ ስምምነት የተፈረመዉ ትናንት ነዉ፤ በጉዳዩ ላይ ግን ወደፊርማ የሚያደርሳቸዉ ነጥብ ላይ ደረሱት በዚያዉ እለት ነበር።

እነዚህ ወገኖች በመካከላቸዉ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚደርሱበትን ድርድር በሚያደርጉበት በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታትም አንዳቸዉ ሌላቸዉን ሳይተነኩሱ ለመቆየትም ተስማምተዋል።

የሁለት ሳምንቱ ድርድራቸዉም በመካከላቸዉ ፀብን ዘርቶ ከ300,000 በላይ ሰዎችን ህይወት የጨረሰዉን የእርስ በእርስ ጦርነት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያበቃበትን መንገድ ይፈልጋሉ።

የመጨረሻዉ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም የFNL አባላት የህግ ከለላ የሚደረግላቸዉ ሲሆን በእስር ላይ የሚገኙትን የፖለቲካና የጦር እስረኞችም የሚለቀቁበት ሁኔታ ይመቻቻል።

ከFNL ወገን የተገኘዉ የስምምነቱ ሰነድ እንደሚያትተዉ ወታደራዊዉና ፖለቲካዊዉ ዘርፍ በአግባቡ ከተለየ በኋላም የአማጺ ቡድኑ በዉሉና በህጉ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲነት እዉቅና ይሰጠዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በሚፈጥሩት ጤናማ ግንኙነት አካባቢዉን በማረጋጋት የተናቀሉና የተሰደዱ ዜጎች ወደቤታቸዉ የሚመለሱበትን መንገድ ለመፈለግ ተስማምተዋል።

በዚያም ላይ የተባበሩት መንግስታት፤ የአፍሪካ ህብረትና የአካባቢዉ መንግስታት ከስደት የተመለሱት ወገኖች በአገሪቱ መንግስት እንዳይከሰሱ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

የቡሩንዲ ስደተኞች ጥገኝነት ካገኙባቸዉ ሀገራት ወደአገራቸዉ ሲመለሱም ዓለም ዓቀፉን የስደተኞች መመለስ ህግ በተከተለ መልኩ እንደሆነ የመቆጣጠር ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

ዉሉንም የቡሩንዲዉ የአገር ዉስጥ ሚኒስትር ኢቫረስት ንዴሺሚየና የFNL የበላይ የሆኑት አጋቶን ራዋሳ ናቸዉ የፈረሙት። ሂደቱንም የቡሩንዲዉ ፕሬዝደንት ፒየር እንኩሪንዚዛና የደቡብ አፍሪካዉ ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ ተከታትለዋል።

ድርድሩን ካለፈዉ ግንቦት መጨረሻ ጀምሮ ያዘጋጁት ዓለም ዓቀፍ አስታራቂዎች ሲሆኑ ካለፈዉ ዓመት የቡሩንዲ ምርጫ ወዲህ በአማጺዉ ቡድንና በቡሩንዲ መንግስት መካከል የተደረገ የመጀመሪያ ዉይይት ነዉ።

ድርድሩን ያስተናገደችዉ አፍሪካዊት አገር የታንዛንያዉ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴ ከስምምነቱ በኋላ ሰላምን ለማስፈን ጥቃቅን ነገሮችን በአግባቡ ለማየት በመቻላቸዉ እንኳን ደስ አላችሁ እንላቸዋለን ብለዋል።

«ጦርነት ካለ ለሰላም የሚሰጥ ዕድል የለም፣ ሆኖም የተደረሰዉ ይህ ስምምነት ድርድሩ በሚካሄድባቸዉ ቀናት በቡሩንዲ የሚታየዉን አለመግባባትና ግጭት በዘላቂነት ለማቆምና ወደተኩስ አቁም ለማምራት ሰላምን የሚያሰፍን መንገድ ነዉ።»

ራሳቸዉ የቀድሞዉ የአማጺ ቡድን መሪ የነበሩት ፕሬዝደንት እንኩሩንዚዛ አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ደስታቸዉ ግማሽ መሆኑን ነዉ ቃል አቀባያቸዉ ሃፋሳ ሞሲ የተናገሩት።

ሆኖም አሉ ቃል አቀባይዋ ስምምነቱ መፈረሙ ራሱ አንድ እርምጃ ነዉ። ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ደግሞ ስምምነቱን ጥርጣሬ ላይ የሚጥለዉ ነገር የቡሩንዲ ጦር ሃይል አደረጃጀት ነዉ።

FNL ከአገሪቱ ዜጎች 14በመቶ ብቻ በሚሆነዉ የቱትሲ ጎሳ የተሞላ ነዉ የሚለዉን የቡሩንዲ ጦር ከሁቱና ቱትሲ በተዉጣጣ የሰዉ ኃይል እንደገና እንዲደራጅ ይፈልጋል።

ዉይይቱ ከተጀመረ ወዲህም ጥቃት አድራሾች ቡጁምቡራ ከተማ ላይ ባደረሱት የሞርታር ቦምብ ጥቃት አንድ ሰዉ ገድለዉ 14 አቁስለዋል።

በቡሩንዲ በዲሞክራሲ መንገድ የተመረጡት የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ከተገደሉ ከአዉሮፓዉያኑ 1993ዓ.ም ወዲህ ነዉ ጦርነትና ግጭት የተቀሰቀሰዉ።

በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል በርካቶችም ወደአጎራባች ሀገራት ለመሰደድ ተገደዋል።