1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርሊኑ ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 2 2003

ቴሌቭዥንና ኢንተርኔት እየተዋኻዱ ነው፤ ፊልሞች ለ 3 ማዕዘናዊ እይታ እንዲበቁ እየተደረገ ነው። አንድ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪዎች አምራች ኢንዱስትሪ እንዲያውም ፤ ባለ 3 ማዕዘናዊ ፊልሞች፤ ያለ ልዩ መነጽር እንዲታዩ ማድረግ መቻሉን፤ በበርሊኑ ትርዒት አሳይቷል።

https://p.dw.com/p/RkUy
አዲሱ «አይፎን 4»፣ምስል AP

ኮምፑዩተሮች፤ ከሞላ ጎደል የአጅ መዳፍ ያህል መጠን እንዲኖራቸው ተደርጎ ተሠርተዋል። (SMARTPHONES)አሪፍ የእጅ ስልኮች እንበላቸው፣ የተለያየ ጨዋታ መጨዋቻዎች ፤ ፎቶግራፍ ማንሻ፣ የአቅጣጫም ሆነ አድራሻ ጠቋሚ፤ ኮምፒዩተርም፣ ስልክም ይህንና የመሳሰለ አገልግሎት እንዲሰጡ ሆነው ተሠርተዋል።

ከዚሁ የመረጃ ማግኛና የመዝናኛ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሌላ፤ ኤሌክትሪክ ቆጣቢ የልብስ ማጠቢያን የመሳሰሉ መሣሪያዎችም ለትርዒቱ ቀርበው ነበር። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ ዛሬ የተደመደመውን ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየውን ፤ የበርሊኑ ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት የሚመለከት ዝግጅት ይሆናል የማናሰማችሁ።

51ኛው የበርሊኑ ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት

በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገሮች በበጀት ጉድለትም ሆነ በከፍተኛ ዕዳ ተውጠው፣ ገንዝቦቻቸው፤ ዶላርና ዩውሮ፣ የመዳከም ምልክት እየታየባቸው፤ የአክሲዮን ገበያዎችም፤ በዓለም ዙሪያ ሲዋዥቁ በሚታይበት በአሁኑ ወቅት፤ የዓለም የኤኮኖሚ ቀውስ ይከተል ይሆን የሚለው ሥጋት በአሁኑ ወቅት፤እንቅልፍ ቢነሣም ፤ በበርሊን የተካሄደው ዓለም አቀፍ ትርዒት ፍጹም ደንታም እንዳልነበረው ነው የታየው።

በያመቱ ፤ ለአንድ ሳምንት የሚካሄደው፤ የኤሌክትሮኒክስ ፣ በተለይም የመረጃና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ትርዒት ፣ ዘንድሮም ባለፈው ሐሙስ ማታ ፤ ነሐሴ 26 ቀን በኤኮኖሚ ሚንስትሩ ፊሊፕ ሮዖስለር ፣ በልዩ ሥነ ሥርዓት ተመርቆ ከተከፈተ ወዲህ ፤ ከማግሥቱ ዓርብ አንስቶ፣ ዛሬ እስኪደመደም ድረስ ፤ ትርዒቱ 6 ቀናት ለህዝብ ሲታይ ሰንብቷል። «ሰፊ ዕድል» ይፈጥራል ያሉትንም ትርዒት በማወደስ፣ ሮዖስለር፤ ብዙ ነገሮችን ወደ ዲጂታል መለወጡ፣ ሰላምና ነጻነት እንዲሁም ብልፅግና ያስገኝልናል!» ነው ያሉት። ዓለም በመረጃ መረቦች ይበልጥ መተሣሠሩ ህዝብ በተቀላጠፈ ሁኔታ አገልግሎት የሚያገኝበትን፤ ምቾትና ፀጥታ ይፈጥርለታልም ሲሉ መናገራቸው ታውቋል።

140,000 እስኩዬር ሜትር ስፋት ባለው ቦታ በተሠሩ አዳራሾችና በተተከሉ ጊዜያዊ ድንኳኖች ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ከ 1 300 በላይ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያዎች ያቀረቡአቸው የኢንዱስትሪ ውጤቶቻቸው፤ የትርዒቱ አዘጋጆች እንዳሉት ብሩኅ ተስፋን አሳድሯል። ዘንድሮ ከ 235,000 በላይ የሚሆን ህዝብ ሳይመለከተው እንዳልቀረ ሲገመት አምና 230,000 የዘርፉ ባለሙያዎችና ተመልካቾች ነበሩ ትርዒቱን የተመለከቱት።

ከመጀመሪያውም አዝማሚያው ብሩኅ ተስፋ ያሳደረባቸው፤ የበርሊኑ ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ሄር ሃንስ ዮአኺም ካምፕ እንዲህ ነበረ ያሉት፤

«የገበያዎች አለመረጋጋት በሚታይበት ወቅት፤ ኢንዱስትሪው በበኩሉ፤ ካለፈው ዓመት በላቀ ሁኔታ ለዚህ ለበርሊኑ ትርዒት ገንዘብ ይበልጥ ሥራ ላይ ማዋሉ፤ መመደቡ፤ ጠንካራ ምልክት ማሳየቱን ነው የምንገነዘበው።ይህም ማለት፤ ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት (IFA )ለቀጣዩ መንፈቅ፣ ተፋላጊውን የማነቃቂያ ተግባር አከናውኗል ማለት ነው።»

የመረጃና የመዝናኛ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ገበያ፣ ዘንድሮ ፣ ሄር ካምፕ እንደገለጡት የሚያስገኘው ትርፍ 4% ፣ ማለትም ወደ 27 ቢሊዮን ዩውሮ ከፍ ማለቱ አይቀርም። ዋናውን ስንጥቅ ትርፍ የሚያስገኙት አሪፎቹ የእጅ ስልኮች (እስማርትፎንስ) እና ንዑሳን ኮምፒዩተሮች ናቸው። ጠፍጣፋው ቴሌቭዥን ግን ከዚህ ቀደም እንደነበረው፣ ደህና ገቢ አላስገኘም። ከፍተኛ የምስል ጥራት እንዳለው የሚነገርለት HDTV (ሃይ ደፍኒሽን ቴሌቭዥን) የሚሰኘው መሆኑ ነው፣ ያን ያህል በገበያ አላገኘም ነው የተባለው።

አምና ተጋኖ የተነገረለት በ 3 ማዕዘን ምስል የሚያሳየው ቴሌቭዥንም በማስታወቂያ ብዙ የተባለለትን ያህል እምብዛም ገዢ አላገኘም። በዚህ በጀርመን ሀገር ፣ጠፍጣፋ መስታውት ያለው ቴሌቭዥን በአማካዩ ፤ ዋጋው ወደ 610 ዩውሮ ዝቅ ብሏል። 82 ሚሊዮን ገደማ ኑዋሪዎች ባሏት ጀርመን፣ ሰፋ ያለ ቦታ የሚወስደው ጠፍጣፋ ያልሆነው ቴሌብዥን ብዛት ከ 20 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ነው የሚነገረው። አሁን አማላይ የሆነው፤ በአንድ መሣሪያ ውስጥ፤ የቴሌብዥንና የኢንተርኔት ቅንጅት፣ እስከ መጪው ታኅሳስ ወር 3ኛ ሳምንት ገደማ 5 ሚሊዮን ሳይሸጥና ብዙ ትርፍ ሳያስገኝ እንደማይቀር ነው የተገለጠው። የመረጃና የመዝናኛ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የ IFA ዋና ሥራ አስኪያጅ ሄር ሃንስ ዮአኺም እንደሚሉት በጀርመናውያን ዘንድ ላቅ ያለ ግምት ነው የሚሰጣቸው።

«የመዝናኛ ኤሌክትሮኒክ እና ልዩ- ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ የቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች ፤ በዕቃ ገዥዎች ዘንድ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛሉ። በቅርቡ በተካሄደ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ መጠይቅ፤ ጀርመናውያን ኑሮ ይበልጥ ቢወደድባቸው፤ በመጀመሪያ አገር የመጎብኘት አቅዳቸውን ይሰርዛሉ፤ ሁለተኛ፣ በባንክ የሚያስቀምጡትን ገንዘብ መጠን ይቀንሳሉ፤ የመዝናኛ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች ከሆኑ ግን ፣ያወጣ ዋጋ ያውጡ፣ ጀርመናውያን ዓይናቸውን አያሹም። »

ዛሬ ከቀትር በኋላ በተደመደመው ትርዒት፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ጭምር የሚሰጥ ቴሌቭዥን ፣ የተለያየ ሰፊ አገልግሎት ያላቸው የአጅ ስልኮች፤ ንዑስ ጠፍጣፋ ኮምፒዩተር፤ (Tablet Computer) የአቅጣጫ መሪ መሣሪያዎች፤ ለዲጂታል ሥነ-ጽሑፍ ማንበቢያ የሚረዱ መሣሪያዎች፤ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀንሱ የቤት ውስጥ የተለያዩ መሳሪያዎች ተመልካቾችን ትኩረት ሳይስቡ እንዳልቀሩ ተነግሯል።

በበርሊኑ 51ኛ ዓለም አቀፍ የመረጃና መዝናኛ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ትርዓት፣ ሰፋ ያሉ መድረኮች ይዘው ሲያስተዋውቁ ከሰነበቱት ኩባንያዎች አንዱ ንዑሳን ኮምፒዩተሮችና አሪፍ የአጅ ስልኮች ዋጋ ላይ የላቀ ትኩረት ያደረገው የደቡብ ኮሪያው «ሳምሱንግ» ነው። የሳምሱንግ ሥራ አስኪያጆች፤ እንደሚያሰላስሉት፤ በሚመጡት 4 ዓመታት በዓለም ዙሪያ፣ የአሪፍ የአጅ ስልክ ከ 200 ዶላር በታች፣ ዝቅ ማለቱ አይቀርም። ስለሆነም በሚደራው በዚህ ገበያ ዋና ተሳታፊ ሆኖ ለመገኘት፣ ነው እቅዱ! ከአስያ ቀጥሎ የአጅ ስልክ አገልግሎት በተፋጠነ ሁኔታ የሚስፋፋበት ክፍለ ዓለም አፍሪቃ ነው። እ ጎ አ በ 2010 (አምና) አፍሪቃ ውስጥ ከ 400 ሚሊዮን በላይ የአጅ ስልክ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደነበረ ተደርሶበታል። ከተከተሞች ፈንጠር ብለው በሚገኙ ቦታዎች፤ በተለይ የእጅ ስልክ አገልግሎት ተፈላጊነት የሚያጠራጥር አይደለም። የተጠቃሚው ፍላጎትም እንዲሁ ከፍ ያለ ነው። የእጅ ስልክ መስፋፋት ዕድገት በሚያሳይባቸው ኬንያን ፤ ጋናን ፤ ናይጀሪያን፤ ታንዛንያንና ዩጋንዳን በመሳሰሉ አገሮች፤ አገልግሎት ከሚሰጡት ስልኮች መካከል 80% የኢንተርኔት መስመር ጭምር ያላቸው ናቸው። ይህም፤በ ዓለም አቀፍ የሞባይል የመገናኛ ሥርዓት፥ GSM (Global System for Mobile Communications )

መረብ ፤ ማለት በዲጂታል የአጅ ስልክ መረብ በኩል የሚከናወን ሲሆን ከአውሮፓው የፈጣን አገልግሎት ሰጪ መረብ ጋር የሚስተካካል አለመሆኑ ይታወቃል። በአፍሪቃ የአጅ ስልክ አገልግሎት፤ መረጃ ለመለዋወጫ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ባንክ፤ ገንዘብ ፤ ደመወዝ ማስተላለፊያ ፤ ኪራይን የመሳሰሉ ወጪዎችንም መክፈያ እንዲሆን፤ ይህንና የመሳሰሉ አገልግሎቶች እንዲሠጥም በመደረግ ላይ ሲሆን፤ በዚህ ዓይነት አገልግሎት ሰጪ የአጅ ስልኮች ገበያ በትጋት ለመንቀሳቀስ ከተዘጋጁት ኩብንያዎች አንዱ የአሜሪካው ግዙፍ ኮምፒዩተር ኩባንያ «አፕል» ይገኝበታል። እርሱም የአሁኑን iPhone 4 የመሰለ ሆኖም ረከስ ያለ፣ ገበያ ላይ የማቅረብ እቅድ እንዳለው ተነግሯል።

በ Nokia በኩል የንግድ ጉዳይ ም/ፕሬዚድንት

ወ/ሮ ሜሪ ማክ ዱዌል ባለፈው ወር መጨረሻ ገደማ ኬንያ ውስጥ በ 2 SIM ካርድ(የደንበኛ ማንነት መለያ መሣሪያ)( Subscriber Identity Module)

አገልግሎት የሚሰጡ ለአካባቢው የታሰቡ ሞዴሎችን አዘጋጅተዋል። በአንድ

በኩል፤ ዋጋ የሚቀንሱ ካርዶችን በመጠቀም፤ መጥፎ የመገናኛ መረብ ባለበት ፤ ከሁለት አንዱን አማራጭ ፣ ሥራ ላይ ማዋል የሚገድ አይሆንም ይላሉ።

«ኖኪያ ፤ መረጀዎች የማግኘት ዕድልን በማስፋት፣ ኢንተርኔት በተጨማሪ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲዳረስ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። ይህም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ለሚገዙ ወይም ስልክ ኖሮአቸው፤ አዲስ የሚገጣጠም መሣሪያ

ለሚገዙና የኢንተርኔት መሥመር ለሚያገኙ ይሆናል፤ የመጀመሪያው አገልግሎት የሚቀርበው። የኢንተርኔት አገልግሎቱም በኮምፒዩተር ሳይሆን ፣ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ አማካኝነት ነው የሚቀርበው።»

በጀርመን ሀገር ካለፈው ሐምሌ 25,2003 አንስቶ፣ ባገሪቱ በመላ ህዝቡ በዲጂታል ራዲዮ በመጠቀም ላይ ነው። Digital Audio Broadcast በሚሰኘው መሆኑ ነው። በአዲሱ ሥነ-ቴክኒክ በመጠቀም፣ በአገሪቱ በመላ 14 ዲጂታል ፕሮግራሞች፤ መሳ-ለመሳ ይሠራጫሉ። ሌላው፤ ከመጪው ዓመት ሚያዝያ 22 ቀን 2004 ጀምሮ የጀርመን አሮጌው የሳቴላይት ቴሌቭዥን ፕሮጋራም ሥርጭት ይቋረጥና የዲጂታል መርኀ-ግብር ተግባራዊ ይሆናል። በተጠቀሰው ሳቴላይት የሚገለገሉ 2 ሚሊዮን ጀርመናውያን ፤ የሚገለገሉበት ዘዴም ሆነ መንገድ ካልተለወጠ፣ በቴሌቭዥናቸው ጥቁርና ነጭ እንጂ ባለቀለም ተንቀሳቃሽ ምስል ማየት አይችሉም።

ተክሌ የኋላ፣

ሸዋዬ ለገሰ