1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበረሃዋ አበባ

Azeb Tadesse ቅዳሜ፣ መስከረም 9 2002

ሰሞኑን በጀርመን የበረሃዋ አበባ በተሰኘ አንድ በእዉነት ታሪክ ላይ የተመሰረተ ፊልም ለተመልካች ይቀርባል። ፊልሙ በተለይ በአፍሪቃችን በሴቶች እህቶች ላይ የሚፈጸመዉ ግርዛት ጎጂ ልማዳዊ ባህል መሆኑን ለማሳየት የቀረበ ሲሆን ፊልሙ የተቀናበረዉ በአንድ የጀርመን

https://p.dw.com/p/Jkgd
ዋሪስ ዳሪምስል picture-alliance/ dpa

እና የአሜሪካ ዜግነት ባላት የፊልም ስራ አዋቂ መሆኑ ታዉቋል። የፊልሙ ተዋናይ ደግሞ ዉቢቷ ኢትዮጽያዊት ሞዲል ሊያ ከበደ ናት።
የበረሃዋ አበባ በእንጊሊዘኛዉ Desert Flower ይሰኛል። እ.አ 1998 አ.ም በምእራባዉያኑ ዘንድ ታዋቂ በሆነች አንዲት ሞዴል ሶማልያዊት ለአንባቢያን የቀረበዉ መጽሃፍ። ደራሲዋ ሶማሊያዊት Waris Dirie የጻፈችዉ መጽሃፍ የግል ህይወትዋን ሲሆን፣ በአዉሮጻ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጎሞ በተለያዩ አገሮች ዉስጥ በከፍተኛ ቁጥር የተሸጠ መጽሃፍ እንደሆነም ይነገርለታል። ደራሲዋ Waris Dirie እ.አ 1965 ግድም ላይ እንደተወለደች በመላምት ነዉ የምታዉቀዉ። በሶማልያ ገጠር ከተማ ያደገችዉ Waris 13 አመት ሲሞላት ቤተሰቦችዋ ሊድርዋት እንዳሰቡ በማወቅዋ፣ ካለችበት ገጠር ከተማ ተነስታ በረሃዉን በግርዋ በመቋረጥ ከቤተሰቦችዋ ጠፍታ አክስትዋ ጋር ወደ ሶማልያ ዋና ከተማ መቅድሾ ትገባለች። አክስትዋ ጋር ስትኖር ሳለ በዝያን ግዜ በለንደን አንባሰደር የነበሩት አጎትዋ የቤት ሰራተኛ ስላስፈለጋቻዉ Waris አጎትዋ ጋር በቤት ሰራተኛነት እንድታገለግል ተነግሮዋት ወደ ለንደን ከተማ ትመጣለች። ብዙም ሳታገለግል በመሶማልያ የሲአድባሪ መንግስት ተገልብጦ በአገሪትዋ ጦርነት እና ዉጥረት በመጀመሩ በለንደንም ያለዉ ኤንባሲ ይዘጋል። ዋሪስ በመቀጠል በለንደን YMCA ተብሎ በሚጠራዉ የክርስትያን ወጣቶች መርጃ ድርጅት ዉስጥ ጥገኝነት እና እርዳታ ጠይቃ መኖርን ትጀምራለች። በዝያም ስትኖር በምግብ መሸጫ ሱቆች ዉስጥ ስታገለግል ሳለ አስራ ስምንት አመት እንደሞላት ነበር አንድ እንጊሊዛዊ ፎቶ ቀራጭ ያገኛት። ፎቶ ቀራጩ ቁመናዋን አፍሪካዊ ዉበትዋን ቁመናዋን አይቶ በፎቶዉ ወደ አለም መድረክ ይዝዋት ገባ። ትንሽ ሳትቆይ ማለት እንደ አዉሮጻዉያኑ 1987 አ.ም ታዋቂ ለሆኑት በምእራባዉያኑ ዘንድ እጅግ ዘመናዊ ልብስ እና ጌጣ ጌጥ ያቀርባሉ ለሚባሉት እንደ Chanel , L’Oréal , Versace ድርጅቶች መስራትን ጀመረች። ተፈላጊነትዋ እየጨመረ በለንደን በማይላንድ ፓሪስ እና ኒዉዮርክ የዘመናዊ ልብስና ጌጣጌጥ ትርኢት ላይ መቅረብ ጀመረች ምንም እንኳ በዘመኑ ጥቁር ሞዴል ያልተለመደ ቢሆንም። በዚሁ በመድረክ በዉበትዋና በቁመናዋ የምእራባዉያኑን አለም ወደ አፍሪቃ መለስ በማድረግዋ፣ የመገናኛ ብዙሃንም ስለስዋ ምንነት እንዲሁም ከየት ወድየት መድረስ ለማወቅ ፍላጎትን አነሳሳ። የብሪታንያዉ የብዙሃን መገናኛ BBC ሞዲልዋን አፍሪቃዊት ጠየቀ ከየት መጣሽ እንዴት እዚህ ደረሽ ማነሽ በማለት። በመልስዋ ዋሪስ እ.አ 1997 አ.ም ነዉ ሶማልያዊትዋ ዉቢት Waris Dirie የሶማልያን በረሃ በባዶ እግርዋ አቋርጣ ተጠምታና ተርባ መቅዲሾ መድረስዋን ከዝያም ወደ ለንደን በቤት ሰራተኝነት መምጣትዋን ፣ በተለይ ደግሞ ለማታዉቀዉ ወንድ ቤተሰቦችዋ ሊድሯት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ እና ለዝግጅቱም መገረዝዋን ገለጸች። ይህ ያልተለመደ ባህል በምእራባዉያኑ ዘንድ ትልቅ ርእስ ሆነ፣ በዚሁ አመት ከሞዴልነት ተግባርዋ ጎን ለጎን የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወም እና ጎጂ ባህል መሆኑ በመግለጽ የተባበሩት መንግስታት ልዩ አንባሳደር በመሆን ተሾመች። በመቀጠል አንድ አመት ቆየት ብላ Desert Flower የበረሃዋ አበባ በተሰኘ የግል ህይወት ታሪክዋን እና ገጠመኝዋን በተለይም በአገርዋ በሶማልያ የደረሰባትን ጎጂ የመገረዝ ባህል በመጻፍ በተለያዩ የአዉሮጻ አገራት አንባብያን በሽምያ የገዙትን ተወዳጅ መጽሃፍዋን አቀረበች። በዚሁ አመት ለመጀመርያ ግዜ ሶማልያ ተመልሳ ያደገችበትን ገጠር ጎበኘች በመቀጠል የአርብቶ አዳሪዉ ልጅ በተሰኘ ሁለተኛ ታሪክዋን በመቀጠል ለአንባብያን አቀረበች። በጀርመን ተደናቂ እና በብዛት የተሸጠ ያመቱ መጽሃፍ በሚል ሽልማትን አግኝታለች። ይህንኑ መጽሃፍዋን በመያዝ በአዉሮጻ በተለያዩ አገሮች በመዞር በተለይ በአፍሪቃ ያለዉን የሴት ልጅ ግርዛት ጎጂ ባህልነቱ ታዉቆ እንዲቆም በሚል ቅስቀሳዋን ጀመረች።
የደራሲ እና የዉቢት ሶማሊያት ታዋቂ ሞዴል ታሪክን የያዘዉ ሰሞኑን በጀርመን እና በሌሎች የአዉሮጻ አገሮች ለመጀመርያ ግዜ የሚታየዉን ፊልም ዋና ተዋናይ ኢትዮጽያዊትዋ ታዋቂ ሞዴል ሊያ ከበደ ትባላለች። በጀርመናዊት ፊልም ቀራጭ የተቀናበረዉ ፊልም የሁለት ሰአት ርዝመት ሲኖረዉ በጅቡቲ በኒዮርክ በኮለኝ እንዲሁም እዚሁ በሙኒክ ከተማ እንደተቀረጸ ተነግሮአል።
ፊልሙ አንደ ሰንደሪላ ታሪክ እልም ካለ ገጠር ወጥታ በረሃን አቋርጣ፣ ለህይወት ታግላ፣ በአለም ታዋቂነትን ስላገኘች ሴት ታሪክ ይተርካል። በተለይ ፊልሙ በታዳጊ አገር በተለይም በአፍሪቃ በሚታየዉ በሴት ልጅ ግርዛት ሰበብ በርካታ ህጻናቶች በደም በመፍሰስ እንዲሁም በንጽህና ጉድለት ምክንያት ህይወታቸዉን እንደሚያጡ ይተርካል። የበረሃዋ አበባ የተሰኘዉ ፊልም እንዲሁም መጽሃፍ እስካሁን ድረስ በአዉሮጻ የመጻህፍት መደብር በጣም የሚሸጥ መጽሃፍ እንደሆነ ይነገርለታል። በፊልሙ መጨረሻ እንደ ጥናታዊ መዘርዝሮች ዘገባ ይላል፣ በቀን 6000 ህጻናት ሴትች እንደሚገረዙ ሲያሳይ ይህም አጉል ባህል በመሆኑ መቅረት እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጠዋል።
በነገራችን ላይ ታዋቂዋ ሶማልያዊት ደራሲ ከበረሃዋ አበባ ለጥቃ፣ የአርብቶ አደሩ ልጅ፣ ህመምተኞቹ ህጻናቶች እንዲሁም ለእናቴ ደብዳቤ፣ የሚል መጽሃፍን ለአንባብያን አቅርባለች። ዋሪስ የሞዴልነት ስራዋን ወደ ጎን አድርጋ የሴት ልጅ እንዳትገረዝ በሚለዉ መርሆዋ ጸንታ በአለም ዙርያ ቅስቀሳዋን በማካሄድ ላይ ትገኛለች። በአዉሮጻዉ ህብረት ለበርካታ ግዜ በመጋበዝ ንግግር አድርጋለች የፈረንሳዩ ኒኮላ ሳርኮዚ፣ ሚሃኤል ጎርባቾቭ፣ የቀድሞዋ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮንደሊዛ ራይስ ሽልማትን ተቀብላች። ዋሪስ የሁለት ወንዶች እናት እንደሆነችም ይነገራል።

Nicolas Sarkozy und Waris Dirie Genitalverstümmelung
ምስል AP
Wüstenblume Flucht
ምስል Majestic