1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበረሃማነት መስፋፋት ስጋት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2005

በበረሃ መስፋፋትና በድርቅ ምክንያት የሚከሰተዉ የመሬት ለምነት ማጣት በየዓመቱ ከእርሻ ምርት ከሚገኘዉ 349 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያሳጣ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጥናት አመለከተ። በዚህ ምክንያትም ከስምንት መቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለከፋ የረሃብ አደጋ እንደሚጋለጥ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/18GLB
ምስል FAO

ስዊዘርላንድ የቆዳ ስፋቷ ከሰሜን ወደደቡብ 220ኪሎ ሜትር፤ ከምስራቅ እስከምዕራብ 350 ኪሎ ሜትር እንደሚሆን መረጃዎች ያመለክታሉ። የሰሞኑ የባለሙያዎች ጥናት በየዓመቱ የዚህን መጠን ሶስት እጅ የሚያህል መሬት በድርቅና የበረሃ መስፋፋት ምክንያት ለምነቱን እንደሚያጣ ነዉ የጠቆመዉ። የባለሙያዎቹ ጥናት ከመሬት ስፋት አኳያ በበረሃ መስፋፋትና በመሬት ለምነት ማጣት አፍሪቃ ግንባር ቀደም ተጠቂ ክፍለ ዓለም መሆኗን ሲያመለክት፤ በመሬት ለምነት ማጣት ምክንያት በሚከተለዉ ድርቅና ርሃብ ግን እስያ ዉስጥ የሚገኘዉ ህዝብ ከአፍሪቃዉ በላቀዉ ቁጥሩ ምክንያት ዋነኛ ለችግር ተጋላጭ ነዉ ይላሉ ቦን የሚገኘዉ በተመድ በረሃማነትን የማስወገድ ስምምነት የትብብር ጉዳይ ዘርፍ አማካሪ ሉዊ ቤካ። ስለጥናቱ ዉጤት ሲገልፁም፤

«ጥናቱ የሚያሳየዉ መሬትን በአግባቡ ለመጠቀም የተፈጥሮ ሀብቶችን ማለትም መሬትና አፈሩን በጥንቃቄ ለመጠበቅ የሚወጣ ወጪ ባለን መሬት ላይ ብዙ ለማምረት እንድንችል ይረዳል። ይህ ደግሞ ለሰዎች የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣል፤ በዚያ ላይ ለወደፊትም የማምረት አቅምን አጠናክሮ የመቀጠል ሁኔታን አስተማማኝ ያደርጋል። በጥናቱ እንደታየዉ በዚህ ረገድ የተጎዱ አካባቢዎች በመሬት ቆዳ ስፋት ደረጃ ስናየዉ ለመሬት ለምነት ማጣትና በረሃማነት መስፋፋት አፍሪቃ ግንባር ቀደሟ ለችግር ተጋላጭ ስትሆን፤ በተቃራኒዉ በሚጎዱ ሰዎችን ብዛት ስንመለከት ግን የእስያ ኅብረተሰብ ይሰፋል። ይህ ደግሞ ህንድና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገሮችን ሁሉ ያጠቃልላል።»

preventing desertification
ምስል CC / Bert van Dijk

ባለፈዉ ሳምንት እዚህ ጀርመን ቦን ከተማ የተካሄደዉ ድርቅ እና የበረሃማነት መስፋፋት ላይ የተወያየዉ ጉባኤ ያወጣዉ መግለጫ እንደሚለዉ ድርቅና በረሃማነት በመተባበር የሚያስከትሉት የመሬት ለምነት መቀነስ 870 ሚሊዮን ህዝብን ለከፋ ረሃብ አጋልጧል። መሬት ለምነቱን እንዳያጣ የሚደረገዉ የመከላከል ጥረት ለምነቱን ያጣ መሬት ከችግሩ እንዲያገግም ለማድረግ የሚዉለዉ ወጪ እጅግ እንደሚልቅ ነዉ ባለሙያዎቹ ያካሄዷቸዉን ጥናቶች ተንተርሰዉ ለማሳየት የሞከሩት። የመሬትን ለምነት የሚያሳጡ ምክንያቶች ሰዉ ሰራሽም ተፈጥሯዊም ሊሆኑ እንደሚችሉ ነዉ ቤካ የሚናገሩት፤

«የመሬትን ለምነት ለማሳጣት ምክንያቶቹ ተፈጥሯዊም ሊሆን ይችላል ሰዉ ሰራሽም ሊሆን ይችላል። ተፈጥሯዊ ስባል የአየር ንብረት መለወጥ ሊሆን ይችላል፤ በሰዎች እንቅስቃሴም እንዲሁ ይሆናል። ለምሳሌ ከገደብ ያለፈ ግጦሽ፤ ሳያሰልሱ በተከታታይ ማረስ፤ ያለቦታዉ የማይሆን ዘር መዝራት፤ አለያም ብዙ ማምረት በሚችል መሬት ላይ ህንፃ መገንባት ሊሆን ይችላል። እናም የመሬትን ለምነት ለመቀነስ እጅግ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ። በዚያ ላይ ሁኔታዉ እንደሚከሰትበት አካባቢ ምክንያቱም እንዲሁ ሊለያይ ይችላል።»     

በአራት ቀናቱ የተመድ በረሃማነትን የመከላከል ጉባኤ የቀረበዉ ጥናት ከጎርጎሮሳዊዉ 1992ዓ,ም ጀምሮ የተሰባሰቡ መረጃዎችን ማካተቱ ነዉ የተገለፀዉ። በወቅቱ 42 ቢሊዮን ዶላር ያሳጣ እንደነበር የተነገረለት የመሬት ለምነት መቀነስ ዛሬ በየዓመቱ 450 ቢሊዮን ዶላር እያከሰረ እንደሚገኝ ነዉ የተጠቆመዉ። ለምሳሌ ባንግላዴሽ በየዓመቱ ከለም መሬቷ ሁለት በመቶ የሚሆነዉ ይራቆታ። ይህ በሃምሳ ዓመት ቢሰላ ከሚቀጥሉት አምስት አስርት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ አንድም ለም የሚባል መሬት እንደማይኖራት ነዉ ዋልተር አማን የግሎባል ሪስክ ፎረም ዳይሬክተር የጠቆሙት። ሉዊ ቤካ ባግላዴሽ በምሳሌነት ብትጠቀስም ችግሩ በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ አይደለም ይላሉ፤

Logo UNCCD Wüstensekretariat
ምስል UNCCD

«የመሬት ለምነት ማጣት መላ ዓለምን የሚነካ ሰፊ ችግር ነዉ። በተለይ ዝቅተኛ የዝናብ መጠን ባለባቸዉ እና ደረቅ አካባቢዎች። ሂደቱ በግልፅ የሚታይና የሚታወቅ እንደመሆኑ በመላዉ ዓለም የሚታይ እና የሚካሄድ ጉዳይ ነዉ።»

አፍሪቃ በዓመት ከአራት እስከ 12 በመቶ የሚሆን ለእርሻ የሚዉል ለም መሬት በበረሃ መስፋፋት ምክንያት ታጣለች። የዑዝቤኪስታን የእህል ምርት በመሬቱ ለምነት መቀነስ ሰበብ በ20 እና 30 በመቶ እጅ ዝቅ ብሏል። በምስራቅ አፍሪቃ በሚገኙ ሀገሮች በጎርጎሮሳዊዉ 2011ዓ,ም በተከሰተዉ ድርቅ ምክንያት 3,7 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ ርዳታ እንደሚፈልግ ጥናቱ በዝርዝር አመልክቷል። በረሃማነትን ለመከላከል ይበጃል ያሉትን የመፍትሄ ሃሳብ የሰነዘሩት ወገኖች ለደረሱበት መነሻ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰበዉ መረጃ መሆኑን ነዉ ሉዊ ቤካ ያመለከቱት፤

«ከባለፈዉ ሳምንት ሳይንሳዊ ጉባኤ የተገኘዉ ዉጤት ከተለያዩ አካባቢዎች የቀረቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነዉ። ማጠቃለያዉ መነሻ ያደረገዉ ከመላዉ ዓለም ጉባኤዉ ላይ የቀረቡ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ግኝት ነዉ። እንደዉም የጥናቶቹ ጭማቂ ነዉ ማለት ይቻላል። እናም ሁኔታዉ ከአንዱ አካባቢ ከሌላዉ የተለየ ነዉ። በአንዳንድ አካባቢ መሬቱ በአግባቡ መጠበቁ  ይታያል፤ መሬቱን ዘላቂነት ባለዉ አካሄድ የሚጠቀሙ ወገኖች ምርታቸዉና የሚያገኙት ጥቅም መጨመሩ ይታያል። በሌላኛዉ የዓለም ክፍል ደግሞ መሬቱ ክፉኛ ለምነቱን አጥቷል። እናም እዚህ ጋ ለማለት የምንፈልገዉ የመሬቱ ለምነት እንዳይቀንስ በሚደረገዉ ጥረት የዉሃ እጥረትን ተቋቁሞ ምርታማነቱ ሳይጓደል ለመዝለቅ የሚችል ንቃት ያለዉ ኅብረተሰብ መገንባት እንደሚቻል ነዉ። ይህን በማድረግ የሚደርሱበት የአየር ንብረት ለዉጥ ስጋቶች እና የገበያ ዉጣ ዉረዶችን መቋቋም የሚችል  የአካባቢዉ ተፈጥሮ ራሱ መከላከል እንዲችል ማመቻቸት ይቻላል ነዉ። በጥቅሉ ማንኛዉንም አሉታዊ ተፅዕኖ መቋቋም የሚችል ኅብረተሰብና የተፈጥሮ አካባቢ ማጠናከር ይቻላል የሚል ነዉ።»

Bildergalerie Libyen und seine Traditionen
ምስል DW/G. Anderson

በጉባኤዉ የተወያዩት ባለሙያዎች መሬት ለምነቱን እንዳያጣ መደረግ ይኖርበታል ያሉትን በተመድ በረሃማነትን የማስወገድ ስምምነት የትብብር ጉዳይ ዘርፍ አማካሪ ሉዊ ቤካ ዘርዝረዉታል፤

«ይህን ለመከላከል ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ያቀረበዉ የመፍትሄ ሃሳብ ዘላቂነት ያለዉ የመሬት አጠቃቀም ነዉ፤ ይኸዉም ያለዉ የእርሻ ስልትና የመሬቱ የማምረት አቅም መጣጣም እንደሚኖርበት የሚያስገነዝብ ነዉ። ይህም ማለት መሬቱ አለመጋለጡ ማለትም መሸፈኑን ማረጋገጥ ይህም አፈሩን ከመከላት ያድናል፤ ስለዚህ ለማዳበሪያ የሚሆኑ ዛፎችን ማብቀል፤ ይህም ደንና እርሻን ማጣመር እንደማለት ነዉ፤ ማለትም በእርሻዉ አካባቢ ዛፎችን መትከል መቻል ይመለከታል። አፈሩ እንዳይከላ መርዳት ማለት ደግሞ ምርትን ከፍ ለማድረግ አልፎ የመሬቱን ለምነት ይዘት ያሻሽላል። ከዚህም ሌላ በደረቅ አካባቢዎች አፈሩ ያለዉ ዉሃ በትነት እንዳይባክንም ይረዳል። ሌላዉ እርከን መስራትም ይረዳል ይህ ደግሞ ከባድ ዝናብና ጎርፍ በሚኖርበት ጊዜ አፈሩ በቀላሉ እንዳይሸረሸርና ለማምረት የሚጠቅመዉ ማዕድን በቀላሉ ታጥቦ ወደሌላ እንዳይጠረግ ይከላከላል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ