1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክሱ ይቀጥላል ተብሏል

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2009

በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ አመጽ ምክንያት ከስልጣናቸው የተነሱት እና በስተኋላም በሙስና ወንጀል የታሰሩት አቶ ዘላለም ጀማነህ የክስ ሂደታቸው ለጊዜው እንዲቆም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዝዟል፡፡ የክልሉ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ግን በመስሪያ ቤቱ አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያቀረበው ይግባኝ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ክሱ ይቀጥላል ብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/2UYb2
Symbolbild Justiz Richter Gericht Richterhammer
ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

Former Oromia Official Court case suspened - MP3-Stereo

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ የነበሩት የአቶ ዘላለም ጀማነህ ክስ ለጊዜው እንዲቆም ያዘዘው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው አርብ ታህሳስ 7 በነበረው የችሎት ውሎ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው በክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የቀረበለትን ይግባኝ ከተመለከተ በኋላ ነበር፡፡

የፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ ‘የታች ፍርድ ቤት ተገቢውን ብይን አልሰጠም’ በሚል ነበር ይግባኙን ያቀረበው፡፡ የአቶ ዘላለምን ጉዳይ እየተመለከተ ያለው በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኃላፊው መዝገብ ከተከሰሱ ተከሳሾች ውስጥ ገሚሱ ሳይገኙ ክሱ ለብቻው ይቀጥል ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡ የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ግን በቀሪዎቹ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ወደ ክርክር መገባት የለበትም በሚል ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል፡፡

ይግባኙን ባለፈው አርብ ታህሳስ 7 የተመለከተው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ “ጉዳዩ ያስቀርባል” ሲል ውሳኔ መሰጥቱን የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሂሩት ቢራሳ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡ 

“ከአቶ ዘላለም ጋር አብረው የተከሰሱ ሰዎች አሉ፡፡ ግማሾቹ ታስረዋል፤ ግማሾቹ አልታሰሩም፡፡ ያልታሰሩ ሰዎች ላይ መጀመሪያ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ ያንን ባለመስጠቱ አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል፡፡ በዚያ መሰረት ውሳኔ እንዲሰጠጥበት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ውሳኔ እንዳገኘ ወዲያውኑ ወደ ዋናው ክስ ክርክር ይገባል ማለት ነው፡፡ በተቀሩት ላይ ጉዳዩ ያስቀርባል የሚለው ባለፈው ታይቷል፡፡ በሚቀጥለው ችሎት ደግሞ እነዚህ ያልቀረቡ ሰዎች እንዴት እንደሚኬድበት ውሳኔ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ በእነርሱ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ አብሮ የተከሰሱ ሰዎች ጉዳይ በአንድ ላይ የሚታይበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በጋራ መግባባት ያልቀረቡትም ጉዳያቸው ምን ላይ እንዳለ እንዲያውቁት ተደርጎ ማለት ነው” ሲሉ ጉዳዩ አሁን ያለበትን ደረጃ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ዘላላም በሙስና እና ስልጣንን አላግባብ በመገልገል ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ሰኔ ወር ነበር፡፡ ከእስራቸው አራት ወር አስቀድሞ ደግሞ የስራ አስፈጻሚ አባል የነበሩበት የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በክልሉ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በአመራር ድክመት ከኃላፊነታቸው አንስቷቸዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው አንድ ቀን አስቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ደግሞ ያለመከሰስ መብታቸው አንስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡      

የቀድሞው የቢሮ ኃላፊ የተከሰሱት የቤተሰባቸውን አባላት ጨምሮ ከሌሎች 11 ግለሰቦች ጋር ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ብቻ ናቸው ፍርድ ቤት በአካል መቅረብ የቻሉት፡፡ ቀሪዎቹን ተከሳሾች ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ትዕዛዝ ቢሰጥም ተከሳሾቹ በችሎት አልተገኙም፡፡

የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ  ባልተገኙ ተከሳሾች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ባለው መሰረት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ብይን እስኪሰጥ ድረስ ክሱ ለጊዜው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ይህ አይነት አካሄድ ህጉን የተከተለ መሆን አለመሆኑን የተጠየቁት የህግ ባለሙያ አቶ ዘላለም ብርሃኑ ይህ በህግ ስነ-ስርዓት እንደሚቻል ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡

“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ገዢ ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ ቤቱን ‘ይህን ጉዳይ መርምሬ ጉዳዩ ይቀጥል አይቀጥል እስክል ድረስ እንዳታይ’ ብሎ የሰጠው ትዕዛዝ ካለ ይቆማል በቃ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አቃቤ ህግ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ክስ አስፍቶ፣ ክሱን አሻሽሎም ሆነ ወይም አስተካክሎ አሊያም ለሚመለከተው ፍርድ ቤት የማቅረብ ስልጣን ስላለው እነዚህ ነገሮች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው ብዬ ነው የማስበው” ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወ/ሮ ሂሩት በቀድሞው የኦሮሚያ ከፍተኛ ኃላፊ ላይ የተመሰረተው ክስ ለጊዜው ቆመ እንጂ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቋረጠ ያስረዳሉ፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ላቀረቡት ይግባኝ ውሳኔ እንደሰጠ ወደ ዋናው ክርክር በአፋጣኝ እንደሚገቡና የክስ ሂደቱም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ